ፈልግ

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት  

የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ፣ ከጥር 10-25/2013 ዓ. ም. ሊደረግ የታቀደውን የጸሎት ሳምንት በማስመልከት በጣሊያን የሚገኙ ሦስቱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች የጋራ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል። መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሬአፊኮ፣ በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የክርስቲያኖች አንድነት እና የጋራ ውይይት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ፖሊካርፖስ ስታቭሮፖሎስ፣ የጣሊያን እና የማልታ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ፓትርያርክ ረዳት እና መጋቢ ሉቃስ ማርያ ኔግሮ፣ በጣሊያን የወንጌላዊያን ኅብረት ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሦስቱ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በመልዕክታቸው፣ በጣሊያን የሚገኙ ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ከምዕመናኖቻቸው ጋር በመሆን እርስ በእርስ ለመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ሁሉ ነገር ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ይመለሳል ተብሎ ይታሰብ እንጂ፣ በዓለማችን የተስፋፋው አመጽ፣ ኢ-ፍትሃዊነት እና ጭካኔ ተለውጦ የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ባለፉት ወራት ሕዝቡን ያጋጠመው ስቃይ እና የዕርዳታ ጥያቄ ብዙ መሆኑ ሲታወቅ፣ ነገር ግን በሕዝቡ መካከል የታየው ኅብረት እና አንድነት በልጦ መገኘቱን አስረድተዋል። ሦስቱም የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጨምረውም ምዕመናኖቻቸው በመተባበር ዕርዳታቸውን ለማድረስ፣ የተራቡትን በመመገብ እና ወዳጅነታቸውን በመግልጽ የተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም በምዕመናን መካከል እያደገ ለመጣው አንድነት እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል ብለዋል። ከእግዚአብሔር የተሰጠን የአንድነት ስጦታ፣ የክርስትና ሕይወት ቀጣይነት ያለው ሀብት እና ውበት መሆኑን እንደገና እንድንገነዘብ ረድቶናል ብለው፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ብዛት፣ ልግስናን ለሌሎች ልናሳይ መጠራታችንን ያስታውሰናል ብለዋል።

በቸርነት የሚገኝ አንድነት

ሦስቱ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በጋራ ባጸደቁት መልዕክታቸው፣ ባለፉት ወራት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ማኅበራዊ ጤና ችግሮች ቢኖሩም፣ ፍርሃት ሳያግዳቸው ድሆችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አረጋዊያንን፣ ቤተሰቦችን እና ወዳጆችን መርዳት መቻላቸውን አስረድተዋል። በእነዚህ የቸርነት ተግባራት የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናቱ ምዕመናን አንድነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ መቻላቸውን ገልጸው፣ ይህ ኅብረታችን ከበጎ ሥነ-ምግባራት መካከል ትልቁ እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሠረተው ኅብረታችን ዋና ምልክት ሆኖ ይኖራል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ አምብሮጆ ስፕሬአፊኮ፣ ብጹዕ አቡነ ፖሊካርፖስ ስታቭሮፖሎስ እና መጋቢ ሉቃስ ማርያ ኔግሮ በኅብረት ሆነው በላኩት መልዕክታቸው፣ በሕመም ለሚሰቃዩት፣ የሕክምና እርዳትን በመስጠት ላይ ለሚገኙት፣ ረዳት ለሌላቸው እና በመጠለያ ማዕከል ለሚገኙ አረጋዊያን፣ ለስደተኞች እና በተለያዩ ምክንያቶች ባሁኑ ጊዜ በችግር ውስጥ የሚገኙትን በሙሉ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። ለክርስቲያኖች አንድነት የታቀደውን የጸሎት ሳምንት አስመልክተው በጻፉት በዚህ መልዕክታቸው፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከክፉ ነገር ጠብቆ ከሕመም እንዲፈውስ፣ ከኢ-ፍትሃዊነት እና ከአመጽ ጠብቆ ወደ ሰላም እና ወደ አንድነት እንዲያደርሳቸው በማለት በጸሎታቸው ጠይቀዋል። በመጨረሻም ሦስቱ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች በጋራ በላኩት መልዕክታቸው፣ በጣሊያን የሚገኝ ክርስቲያን ማህበረሰብ ከጥር 10-25/2013 ዓ. ም. በሚቆየው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመካፈል፣ አንድነታቸውን ለማሳደግ እና በተግባርም ጭምር ለመኖር ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

16 January 2021, 15:51