ፈልግ

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ  

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ እውነት፣ ፍትህ እና ነጻነት እንዲኖር ያስፈልጋል ተባለ

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በዋና ከተማ ባንጊ በሚገኝ ጽነሰታ ማርያም ካቴድራል ስብሰባ ማካሄዳቸው ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤያቸው መዝጊያ ላይ በማስተላለፉት መልዕክት፣ ሕዝባቸው አገራቸውን እንዲወዱ እና ሃላፊነት እንዲኖራቸው፣ የአገሪቱን ሃብት በጋራ እንዲጠቀሙ አሳስበው፣ ለእውነት እና ለፍትህ በመገዛት፣ አመጽን እና ልዩነትን ሲያስከትሉ የቆዩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲቃወሙ ጥሪአቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአገሪቱ ላይ የደረሰውን መከራ እና ጭንቀት ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ለአገራቸው መጽናናትን እና ተስፋን ተመኝተዋል። በአገሪቱ ውስጥ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከተካሄደ ወዲህ፣ የጦር መሣሪያ የታጠቁ አማጺ ቡድን ወደ ዋና ከተማይቱ ባንጊ ለመግባት ባደረጉት ሙከራ የተለያዩ ጥቃቶችን ማካሄዳቸው ታውቋል። ከዚህ በፊት መኖሪያቸውን እንዲለቁ የተገደዱ ሰዎች ቁጥር ሰላሳ ሺህ ሲሆን፣ በቅርቡ በተካሄደው ጥቃት የተፈናቀሉት ደግሞ ከስልሳ ሺህ በላይ መሆናቸው ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ሕዝብ በላይ፣ ይህም 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ከመኖሪያው የተፈናቀለ መሆኑን ገልጾ፣ በያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. አገሪቱ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የምትጋለጥ መሆኗን አስታውቋል።

አፈሪቱ በፍርሃት ውስጥ ትገኛለች

ብጹዓን ጳጳሳቱ “በቃላት ሊገለጽ የማይችል የሕዝብ ቁጣ እና መከራ” ባሉት መልዕክታቸው፣ መሣሪያ ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት እና ዝርፊያ ምክንያት ነዋሪዎቹ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲሸሹ መገደዳቸውን ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥትም የፖለቲካ ስልጣንን መከታ በማድረግ እና የግል ጥቅምን በማስቀደም ነዋሪዎችን ለስቃይ መዳረጉን አስረድተዋል። ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን እና ትምህርት ቤቶችም ለአንድ ዓመት ያህል መዘጋታቸውን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ምንም ዓይነት ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አስታውቀዋል። በጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ዕርዳታ በመታገዝ በተፈናቃይ ሕዝብ መካከል መረዳዳት መኖሩን ገልጸው “ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እገዛ ብቻችን መጓዝ አንችልም” ብለዋል። የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክን በርካታ እንቅፋቶች ወደ ፊት እንዳትጓዝ ከልክለዋታል ብለው ከእነዚህም መካከል ቁጣ፣ ምቀኝነት፣ ክፋት ፣ ውሸት ፣ ማጭበርበር ፣ ዓመፅ ፣ ግድያ እና ጦርነት ታላቅ የወንድማማችነት፣ የፍትህ እና የሰላም እሴቶች እንዳይገለጡ ተደርገዋል ብለዋል።

አገሪቱ እንደገና ለመነሳቱ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ብርታት ያስፈልጋታል

“ከደረሰብን ቁስል ለመዳን፣ ከአዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ይኖርብናል” ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ አገሪቱን ከወደቀችበት እንደገና ለማንሳት የእግዚአብሔር ፍቅር እና ብርታት የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። የአፍሪካን አህጉር ከችግር ለማላቀቅ ብዙ ጥረቶች መደረግ እንዳለባቸው ገልጸው፣ “ቤተክርስቲያንም የተጠራችው የኢየሱስ ክርስቶስን አለኝታነት ለመመስከር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም አገሪቱ የምትገኝበትን ሐቅ በመናገር፣ ቁጣዋንም በመግለጽ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን የተጋረጠባትን ስቃይ እና አመጽ መዋጋት ያስፈልጋል” ብለዋል። 

ጥፋትን በጋራ ውይይት እንከላከል

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው እንደገለጹት በአገራቸው ውስጥ የሚታየው ዓመጽ፣ ጥላቻ እና የበቀል መንፈስ ተወግዶ ትክክለኛ እና ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ለማድረግ ቅን እና ግልጽ መንገድን የተከተለ ወንድማዊ ውይይት ሊኖር ይገባል ብለዋል። የእርስ በእርስ መጎዳዳትን በመተው፣ ክፍፍልን እና የአገሪቱን ሃብት ለተወሰኑ የጎሳ አባላት እና የፖለቲካ ባለስልጣናት ማከፋፈልን ማቆም ይገባል ብለዋል።

የአዕምሮ፣ የመንፈስ እና ልብን ለውጥ እናድርግ

በአገሪቱ ወጥ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ “በአገሪቱ ላይ የሚያንዣብበው ትልቁ አደጋ የአገር ፍቅር መጥፋት መሆኑን ገልጸው፣ ዘረኝነት እና ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም እና ስግብግብነት፣ የወንድማማችነት መንፈስ መጥፋት አገሪቱን በቅጥረኞች እና ሽፍቶች እጅ እንድትወድቅ አድርጓታል” ብለዋል። በመሆኑም የመንግሥት ባለ ስልጣንን ወደ ትክክለኛ ተግባራቸው ለመመለስ እና ሁሉንም ተቋማት ለማጠናከር፣ ቅን የሆነ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንደሚያስፈልግ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።    

19 January 2021, 14:11