ፈልግ

አቡነ ተስፋሥላሴ መድኅን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ አቡነ ተስፋሥላሴ መድኅን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ  

አቡነ ተስፋሥላሴ መድኅን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ የአብሮነት መግለጫ መልዕክቶችን በስልክ ተቀበሉ

አቡነ ተስፋሥላሴ መድኅን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ የአብሮነት መግለጫ መልዕክቶችን በስልክ ተቀብለዋል

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንደገለፁት ረቡዕ ጥር 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ መድኅን የአዲግራት ሀገረስብከት ጳጳስ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። ብፁዕ ካርዲናል እንደገለጹት ብፁዕ ሊቀጳጳሳት አንቷን ካሚሌሪ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር አምባሳደርም እንዲሁ ከብፁዕነታቸው ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገረስብከቶች ጳጳሳት ካህናት፣ ደናግል፣ ምእመናን ለብፁዕነታቸው በመደወል የአብሮነት መግለጫ መልዕክታቸውን አድርሰዋል። በተመሳሳይም በአፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ሃገራት የሚገኙ ጳጳሳት እና የቤተክርስቲያን ወዳጆች በአዲግራት የስልክ ግንኙነት በመጀመሩ ምክንያት ብፁዕነታቸውን እና በሰበካው የሚያገለግሉ መነኮሳትን ለማነጋገር ችለዋል።

ጳጳሳት በስልክ ግንኙነቶቻቸው በአዲግራት ሀገረስብከት ምእመናን እና በመላው የክልሉ ንጹሃን ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ የጤና እና የመሰረታዊ አቅርቦት ችግር  እንደሚያሳዝናቸው ለብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የገለጹላቸው ሲሆን መላይቱ ቤተክርስቲያን ከንጹሃን የትግራይ ሕዝቦች ጋር በመሆን አፋጣኝ ድጋፍ አንዲደርስ የምትሰራ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ጥሪ መግለጫዎችን እና የአብሮነት መልዕክቶችን በማውጣት ላሳዩአቸው ቤተሰባዊነት ምስጋናቸውን በማቅረብ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት የልዑካን ቡድኖችን ወደሀገረስበከታቸው በመላክ እንዲያጽናኗቸው እና በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ተገንዝበው እንዲመለሱ በማድረጋቸው የተሰማቸውን ልባዊ ምስጋና ገልጸውላቸዋል። በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው አፋጣኝ እርዳታ ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ ቤተክርስቲያን ድጋፍ ለማሰባሰብ እና ወደሰበካው በአፋጣኝ ለማድረስ የጀመረችውን እንቅስቃሴ በማበረትታታት የአዲግራት ሀገረስብከት ድጋፉ አስፈላጊ ወደሆነባቸው አካባቢዎች በማሰራጨት ተጎጂ ወገኖች እንዲቋቋሙ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸውላቸዋል።

23 January 2021, 12:45