ፈልግ

ለአውሮፓዊያኑ 2023 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀ አርማ፤ ለአውሮፓዊያኑ 2023 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀ አርማ፤ 

ለዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀ መዝሙር ይፋ ሆነ።

እ.አ.አ በ2023 ዓ. ም. ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀ መዝሙር ጥር 19/2013 ዓ. ም. ይፋ መሆኑ ተገለጸ። መዝሙሩ (www.lisbona.2023.org) በተባለ አውታረ መረብ፣ እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል ይፋ መደረጉን የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታውቋል። መጭው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የሚከበረው በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን፣ እ.አ.አ 2023 ዓ. ም መሆኑ ታውቋል። እ.አ.አ በ2022 ዓ. ም. ሊከበር ታቅዶ የነበረው ይህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት እንዲዘገይ መደረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጥር 19/2013 ዓ. ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል መዝሙርን ከፌስቲቫሉ አውታረ መረብ እና ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማግኘት የሚቻል ሲሆን ከፌስቲቫሉ መዝሙር በተጨማሪ ለፌስቲቫሉ የተዘጋጀ አርማም በዓሉ ወደ ሚከበርበት አገር ፖርቱጋል መድረሱን አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል። በወጣቶች ፌስቲባል ላይ የሚገኙት ቅዱስ መስቀል እና በሮም ከተማ “ሳንታ ማርያ ማጆሬ” ባዚሊካ ውስጥ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ቅጅ ወደ ሊዝቦን ከተማ መድረሳቸውን የፌስቲባሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታውቋል። የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ኮሚቴ እንዳስታወቀው በፌስቲባሉ ላይ የሚገኙት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል እና ቅዱስ መስቀል ለጊዜው በፌስቲባሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚቀመጡ ሲሆን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲወገድ በሁሉም የፖርቱጋል ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች መካከል ንግደት የሚያደርጉ መሆኑ ተገልጿል። 

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት

የፖርቱጋል ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሆሴ ኦርኔላስ እና ምክትል ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ቪርጂሊዮ አንቱኔስ ከቃል አቃባያቸው ከሆኑት ክቡር አባ አማኑኤል ባርቦሳ ጋር ዓርብ ታኅሳስ 30/2013 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል። ልኡካኑ ከቅዱስነታቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ እንዳስታወቁት፣ በፖርቱጋል ሊዝቦን ከተማ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ዝግጅት በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ቅዱስነታቸው የተገነዘቡ መሆኑን ገልጸው፣ በሊዝቦን ከተማ እ.አ.አ. በ2023 ዓ. ም. በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ምኞት ያደረባቸው መሆኑ ቅዱስነታቸው ገልጸውላቸዋል።

የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል አርማ ጉዞ

በዓለም ዙሪያ ወደ ተለያዩ አገሮች መንፈስዊ ጉዞን በማድረግ ላይ የሚገኘው የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል አርማ፥ ቅዱስ መስቀል እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል በዓሉ በመጨረሻ ከተከበረበት ከፓናማ ወደ ሮም መድረሱ ይታወሳል። ኅዳር 13/2013 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በመሩት ክርስቶስ ንጉሥ በዓል የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት፣ አርማውን የፖርቱጋል ልኡካን መረከቡ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በመላው ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት መታሰቢያ እሑድ ዕለት ሲከበር የቆየው ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል፣ ክርስቶስ ንጉሥ በዓል በሚከበርበት እሑድ ዕለት እንዲዛወር ማዘዛቸው ታውቋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ ከ1984 ዓ. ም. ጀምሮ ወጣቶች ቅዱስ መስቀልን በዓለም አቀፍ ፌስቲቫላቸው ይዘው እንዲገኙ ማዘዛቸው ይታወሳል። በኋላም እ.አ.አ 2003 ዓ. ም. ወጣቶቹ በተለየዩ አገራት በሚያከብሩት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ከቅዱስ መስቀል በተጨማሪ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱስ ምስልን ይዘው እንዲገኙ ማዘዛቸውም ይታወሳል።

የአርማው ዝግጅት

እ.አ.አ ያለፈው ጥቅምት 16/2020 ዓ. ም. የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል መስራች የሆኑት፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው የተሰየሙበት 42ኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት መሆኑ ሲታወስ በዕለቱ ለመጭው የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀው አርማ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ይፋ መደረጉ ይታወሳል። አርማው የተዘጋጀው የፖርቱጋል ባንዲራ ቀለሞችን፥ አረንጓዴ፣ ቀይ እና ቢጫ ቀለማትን ያካተተ ሲሆን፣ በስተጀርባውም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመረጡትን መሪ ቃል፥ “ማርያምም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” (ሉቃ. 1፡29 የሚያስታውስ ምስል የሚታይበት አርማ መሆኑ ታውቋል። የአርማው አዘጋጅ የ24 ዓመት ዕድሜ ወጣት ፖርቱጋላዊት ቤያትሪስ ሮሄ አንቱኔዝ መሆኗ ታውቋል።     

27 January 2021, 12:31