ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የተደነገጉ አራት የእምነት እውነቶች
ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት፣ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ማንነትና በሰው ልጅ ደኀንነት ታሪክ ስላላት ሚና በነገረ መለኮት ሰፋ ያለ ትምህርት ይሰጣል፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን ሁሉ የተለየ ክብር እንዳላት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታምናለች፤ ታስተምራለች፡፡ ይኸውም ያለ አዳም ኃጢያት የተፀነሰች በመሆኗ ከቅዱሳን ሁሉ የበለጠ አክብሮት ይገባታል፡፡ ስለዚህ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚደረገው ጥናት የሚመለከተው ስለ ሕይወት ታሪኳ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ እርሷን ለማክበር በጸሎት፣ በመዝሙር፣ በኪነጥበብ፣ በሙዚቃና በሕንፃ ንድፍ ጥበብም በጥንታዊና በዘመናዊ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታሪክ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የተጻፈውን ሁሉ በማጤን ጭምር ነው፡፡
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ አክብሮትና ልዩ መብት በተመለከተ እስከ ዛሬ ድረስ የደነገገቻቸው የእምነት እውነቶች አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፡- “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት”፣ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል”፣ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ወጣች የሚሉት ናቸው።
2.1. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት
እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም “የአምላክ እናት ናት” የተባለው የእምነት እውነት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ማንነት በይፋ ያወጀችው የመጀመሪያው የእምነት እውነት ነው።
"ማርያም፡ የአምላክ እናት" በመባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራችው እ.አ.አ. በ250 ዓ.ም. አከባቢ ሲሆን፣"በጥበቃሽ ሥር እንጠለላለን" በሚለው ጸሎት አማካይነት ነበር እምነቱ የተገለጸው።እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ናት"የተባለውን የእምነት እውነት እናታችን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በይፋ ያወጀችው የመጀመሪያው የእምነት እውነት ሲሆን ይህም የታወጀው በኤፌሶን ጉባኤ እ.አ.አ. በ431.ዓ.ም. ነበር።
ኔስቶርዮስ (እ.አ.አ. ከ381-451 የኖረ) እ.አ.አ. ከ428.ዓ.ም. ጀምሮ የኮንስታንትኖፕል ፓትሪያርክ ነበር። እርሱም ማርያም የአምላክ እናት ተብላ መጠራት በጭራሽ አትችልም እያለ ያስተምር ነበር። በርሱ አመለካከት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው ሰው የሆነውን ኢየሱስ ብቻ ስለሆነ፣ "የክርስቶስ እናት" ተብላ መጠራት ብቻ ነው የምትችለው ይል ነበር። በዚህ ዐይነት በግብፃዊው ቅዱስ ቄርሎስና (እ.አ.አ. ከ385-444 የኖረ) በኔስቶርዮስ መካከል ከፍተኛ የአመለካከት ግጭት ተፈጠረ።
ስለሆነም ቄርሎስ ኔስቶርዮስን በጽሑፉ በኃይል አወገዘው። ጉዳዩንም ለግብፅ ጳጳሳትና መነኮሳት በፋሲካ በዓል እ.አ.አ. በ429 ዓ.ም. በይፋ አመለከተ። የርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ሰሌስቲኖስ ቀዳማዊን (422-432) ሙሉ ድጋፍ ስላገኘ ቅዱስ ቄርሎስ 12 ውግዘቶችን በመጻፍ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስም ለነስቶሪዮስ በመላክ ከስሕተቱ እንዲታረም በጥብቅ አሳሰበው። ኔስቶሪዮስ በበኩሉ ደግሞ 12 ተቃዋሚ ውግዘቶችን በመጻፍ የምሥራቅ ንጉሠ ነገሥት የነበረው የዳግማዊ ቴኦዶሲዮስን (እ.አ.አ. ከ 408 እስከ 450 ዓ.ም. የነገሠ) ድጋፍ ከማግኘቱም በላይ በርሱም አማካይነት የምዕራብ ንጉሥ ነገሥት የነበረውን ቫሌንቲኒያን ዳግማዊን (እ.አ.አ. ከ425 ዓ.ም. እስከ 455 ዓ. ም. የነገሠ) በማስተባበር ስለ ጉዳዩ የቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ እንዲጠራ አደረገ። የካቶሊክ ቤተክርቲያን ጠቅላይ ጉባኤዎች 3ኛው የነበረው የኤፌሶን ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው እ.አ.አ. በሰኔ 22 ቀን በ431 ዓ.ም. በበዓለ ኀምሳ በዓል አጋጣሚ ነበር። በዕለቱም ፓትሪያርክ ኔስቶርዮስና ተከታዮቹ አልተገኙም ነበር። በጉባኤው በነበሩት በ198 ጳጳሳት ፊት ኔስቶሪዮስን በመቃወም ቅዱስ ቄርሎስ የጻፈው የውግዘት ሰነድ ተነበበ። ጳጳሳቱም በሙሉ ድምፅ ሰነዱን አጸደቁ። የነስቶሪዮስንም ውግዘት ያለ ምንም ተቃውሞ ተቀበሉ።
በዚህ ዐይነት በኤፌሶን ጉባኤ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም "የአምላክ እናት ናት" የተባለው የእምነት እውነት በይፋ ታወጀ። የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን መለኮታዊ እናትነት የሚደግፈው የመጀመሪያው የወንጌል ጥቅስ የተወሰደው ከወንጌላዊው ዮሐንስ ሲሆን እንዲህ ይላል፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ አደረ” (ዮሐ. 1፡14 ተመልከት)። ወንጌላዊው ሉቃስ በበኩሉ ደግሞ ጉዳዩን በተመለከተ እንዲህ ይላል፣ "መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል የልዑልም ኃይል በጥላው ይጋርድሻል ስለዚህ ደግሞ ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል”(ሉቃ.1፡35 ተመልከት)።
የአሕዛብ ብርሃን የሚባለው ትልቁ የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ በበኩሉ ደግሞ በ8ኛው ምዕራፉ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መለኮታዊ እናትነት እንደሚከተለው ይገልጻል፣ “ድንግል ማርያም በመልአኩ ብሥራት የእግዚአብሔርን ቃል በልቡዋና በሰውነቷ በመቀበል ለዓለም ሕይወት ስጥታለች፤ በእርግጥም የአምላክ እናትና የመድኃኔዓለም እናት መሆንዋ ተቀባይነት አለው፤ ክብርም ይገባታል።” ይህም የእምነት እውነት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት መካከል ስላለው ጥብቅ ግንኙነት ከታወጀው የእምነት እውነት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።
2.2. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል
ዘለዓለማዊ ድንግል ወይም ድንግል ማርያም የተባለው አነጋገር ከሁሉም በፊት የሚያመለክተው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና መፅነስዋን ነው፡፡ ከጥንታዊ የእምነት መግለጫዎች በተለይም ደግሞ በጥምቀት ጊዜ ከሚደገመው ጸሎተ ሃይማኖት ለመረዳት እንደሚቻለው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእምነት እውነት ነው፡፡ እ.አ.አ. በ553 ዓ.ም. የተረገው ሁለተኛው የኮንስታንትኖፕል ጉባኤ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና አላት ብሎ በይፋ አወጀ፡፡ በዚህ ዐይነት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመውለዱዋ በፊት ድንግል ነበረች፤ ስትወልደውም ድንግል ነበረች፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግል ነበረች በማለት ታስተምራለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስን ከመውለዱዋ በፊት ድንግል ነበረች ማለት ጌታችን ኢየሱስን የወለደችው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑን ያስረዳል፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ዘለዓለማዊ ድንግልና የሚያመለክተው የግሪክ ቃል ኤይፓርቴኖስ ሲሆን አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ የሁለተኛውን ቫቲካን ጉባኤ “የአሕዛብ ብርሃን” የተባለውን ሰነድ በመጥቀስ÷ “የክርስቶስ ልደት የእናቱን ድንግልና አልቀነሰም፤ ባርኮታል እንጂ” ይላል (የአሕዛብ ብርሃን ቁ. 57 ተመልከት)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስትወልድ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ስለ ነበራት ድንግልና በተመለከተ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስታስተምር እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው አካላዊ ድንግልናዋን ሳታጣ እንደ ነበረ ትገልጻለች፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እንዴት እንደ ተከሠተ በግልጽ አታስረዳም፡፡ በበኩላቸው ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) “መንፈሳዊ አካል” በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው ጉዳዩን በተመለከተ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፤ “በድንግላዊ ማህፀንዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ የመሆንን ማዕረግ ቀድሞውኑ ተቀዳጅቷል፤ በሚደነቅ ልደት የተወለደውን እንደ መለኮታዊ ሕይወት ምንጭ አሳድገዋለች፡፡”
ከላይ በዝርዝር ከቀረበው መግለጫ በተጨማሪ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከወለደች በኋላም ድንግል እንደ ሆነች ታስተምራለች፡፡ ይህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እምነት በጥንታዊ ዘመን ብዙ ጥያቄዎች አጋጥመውት እንደ ነበረም ይታወሳል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ቢሆኑ ስለ ጉዳዩ ብዙ አያስረዱም፡፡ “የኢየሱስ ወንድሞች ከማለት በስተቀር የማርያም ልጆች በጭራሽ አይሉም፡፡ በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ጸሐፊዎች አስተሳሰብ “የኢየሱስ ወንድሞች” ማለት ሰፋ ያለ ቤተሰባዊ ግንኙነትን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ሰፋ ያለ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም አንዲያ ልጅ መሆኑንም ያስረዳል፡፡ “የኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች” ተብለው ይጠሩ የነበሩትም የቅርብ ዘመዶቹ ልጆች እንደ ነበሩም ይገልጻል” (አዲሱን የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቁ. 499-507 ተመልከት)፡፡
2.3. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች
እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት መፀነስዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከደነገገቻቸው የእምነት እውነቶች 3ኛው ነው፡፡ ይህንን የእምነት እውነት እ. አ. አ. በታህሳስ 8 ቀን 1854 ዓ.ም. የደነገጉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፅዕ ፒዮስ 9ኛው (እ.አ.አ. ከ 1846-1878) ነበሩ:: ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፅዕ ፒዮስ 9ኛው ይህ የእምነት እውነት ልዩ መሆኑንና በሰው አንደበት ለመግለጽ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ለማስገንዘብ የእምነት እውነቱን ለመደንገግ “Ineffabilis Deus”፣ እግዚአብሔር ግሩም በማለት በላቲን ቋንቋ ገልጸዋል:: ይኸውም የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በሰው አንደበት በሚገባ አይገለጽም ማለት ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው እግዚአብሔር አምላክ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት እንድትፀነስ ማድረጉ አንዳች እንከን የሌለባት የአምላክ እናት እንድትሆን ብሎ ነው:: እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ቅድስትና ፍጹም ንጽሕት የአምላክ እናት የመሆንዋም ዋናው መሠረት ይህ ነው በማለት አትተዋል::
ይህ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች ናት የሚለው የእምነት እውነት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከተፀነሰችበት ቅጽበት ጀምሮ በልዩ ጸጋና ከአምላክ በታደለችው ልዩ መብት እንዲሁም ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ትሩፋት ምክንያት ከአንዳች የኃጢአት እድፍ ነፃ በመሆን የተጠበቀች ናት በማለት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ፒዮስ 9ኛው በሐዋርያዊ መልእክታቸው አበክረው አስረድተዋል:: ይህም ማለት የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነበር ማለት ነው:: በተጨማሪም ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች ናት ብለው በይፋ ባወጁት ሐዋርያዊ መልእክታቸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ፒዮስ 9ኛው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በከፍተኛ ደረጃ ቅድስት ከመሆንዋም በላይ ከአጽዳቂ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ጋር ዘወትር ልዩ ኅብረት ያላት ነበረች ብለዋል::
ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት መፀነስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ፒዮስ 9ኛው የጻፉት ሐዋርያዊ ድንጋጌ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ ማኅፀን የተፀነሰችው ያለ አዳም ኃጢአት እንደ ነበረና ከሕይወቷም የመጀመሪያ ቅጽበት ጀምሮ በሰው ዘር በሙሉ ላይ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የጸጋ ጉድለት እንዳይደርስባት እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ ጠብቋታል ይላል:: በተጨማሪም ደግሞ ከሕይወቷ መጀመሪያ ጀምሮ ጸጋ የተሞላች መሆንዋንም አበክሮ አትቷል:: በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት ስለ መፀነስዋ የተደነገገው የእምነት እውነት ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ከተደነገገው የእምነት እውነት ጋር መመሰቃቀል የለበትም:: ምክንያቱም ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና የተደነገገው የእምነት እውነት ዋና ዓላማው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ከድንግል እናት መሆኑን ማስረዳትና ማሳመን ሲሆን ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት ስለ መፀነስ የተደነገገው የእምነት እውነት ዋና ዓላማው ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ በቅድስት ሐና ማኅፀን ያለ አዳም ኃጢአት መፀነሱዋን ማስረዳትና ማሳመን ነው::
እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም ኃጢአት ነፃ ሆና እንድትፀነስ ጌታ አምላክ ያደረገው በሰው ደኅንነት ታሪክ የሚኖራትን ሚናም በግምት በመውሰድ መሆኑንም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ፒዮስ 9ኛው ስለ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት መፀነስ የእምነት እውነት እንዲሆን በጻፉት ድንጋጌአቸው ገልጸዋል:: ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በበኩሉ ደግሞ የአሕዛብ ብርሃን በተባለው ሰነዱ እግዚአብሔር አምላክ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በምሥጢረ ሥጋዌ አማካይነት የአምላክ እናት እንድትሆን ከዘለዓለም የወሰነው ጉዳይ ነው ይላል (የአሕዛብ ብርሃን ምዕራፍ 8 ቁ. 61 ተመልከት):: በተጨማሪም ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷ ለ16ኛው ጊዜ በሉርድ ለቅድስት ቤርናዴት ሱብሩ በተገለጸችበት ዕለት ማለትም እ.አ.አ. በመጋቢት 25 ቀን 1858 ዓ.ም. “እኔ ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነስሁ ነኝ” በማለት የእምት እውነቱን ትክክለኛነት በገዛ ራሷ አረጋግጣለች::
2.4. ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ የወጣች
እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣቱዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ ድንግል ማርያም ከደነገገቻቸው የእምነት እውነቶች አራተኛው ነው፡፡ ይህንንም የእምነት እውነት እ.አ.አ. በኅዳር 1 ቀን 1950 ዓ.ም. “Munificentissimus Deus” እግዚአብሔር እጅግ ለጋሽ በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው አማካይነት በይፋ የደነገጉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) ነበሩ፡፡ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሰጠችው እሽታ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ማኅፀንዋ እንዲወርድ ያደረገችው በከበረው ሰውነት የሰማይና የምድር ንግሥት መሆን ምንኛ የተገባ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገትና በፍልሰታ ማርያም መካከል መሠረታዊ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና ከሙታን የተነሣ ጌታ በመሆኑ ወደ ሰማይ ያረገው በአምላካዊ ኃይሉ ነው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከሙታን የተነሣችውና በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ የተወሰደችው በአምላክ ኃይልና ጸጋ ነው፡፡ ፍልሰታ ማርያም የእምነት እውነት እንዲሆን በደነገጉበት እግዚአብሔር እጅግ ለጋሽ በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው እንዲህ ይላሉ፣ “እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች የአምላክ እናት፣ ዘለዓለማዊ ድንግል፣ የምድራዊ ሕይወትዋን ጉዞ ከጨረሰች በኋላ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማያዊ ክብር ተወስዳለች፡፡” ይህ ድንጋጌና እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች ስለ መሆንዋ የተደረገው ድንጋጌ የሚያመለክቱት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ አስተዳደር ስላለው ዓለም አቀፋዊ እውነተኛና ጠንካራ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከቶሊካውያን ምእመናንም በየዘመኑ ስለ ጉዳዩ የነበራቸውን ጠንካራ እምነት ጭምር ነው፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት ለብዙ ዘመናት በቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ከእምነት ጋር በተያያዘ ትምህርት ሲጠቀስ መቆየቱም የሚታወስ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በነገረ-መለኮት ትምህርት መግለጫ፣ በሥርዓተ-አምልኮ ሥነ ሥርዓትና በካቶሊካውያን ምእመናን አንደበትም ጉዳዩ ሲጠቀስ እንደ ቆየ ይታወሳል፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የእምነት እውነት ስለ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የተገለጸ ስለሆነ ጥያቄ በማያስከትል ሁኔታ በመለኮታዊ መገለጽ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ማለት የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ዋና ዓላማ ከእግዚአብሔር ጋር በፍጹም አንድነት በመኖር መንፈሳዊ ተልእኮዋን መፈጸም እንደ ነበረም የሚያመለክት ነው፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የአምላክ እናት የመሆንዋ ውጤት እንደ ሆነም ማሰብ ይቻላል፡፡ በምድር ላይ ከልጅዋ ጋር በፍጹም አንድነት ስለ ኖረች፣ ለእርሱም ብቻ ስለ ነበረችና እውነተኛ ተከታዩም ስለ ነበረች፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይም ከልጁዋ ጋር መሆን፣ ለእርሱም ብቻ መሆንና የእርሱም እውነተኛ ተከታይ መሆን ይገባታል፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ የልጁዋ እጅግ ለጋስ ተባባሪ እንደ ነበረችም የሚታወስ ነው፡፡ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣቱዋ በምድር ላይ ከልጁዋ ጋር የነበራት እጅግ ለጋስ ትብብር በሰማይም እየቀጠለ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ በዚህ ዐይነት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጁዋ ጋር በምድርም ሆነ በሰማይ የማይፈርስ አንድነት አንዳላት ግልጽ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይም በሰው ደኅንነት ታሪክ ያላትን ሚና በትጋት በመፈጸም ላይ እንደምትገኝ በማስመልከት የአሕዛብ ብርሃን የተባለው የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ እንደሚከተለው ያትታል፣ “ወደ ሰማይ ከወጣች በኋላ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰው ደኅንነት ታሪክ ያላትን ተልእኮ አላቋረጠችም፡፡ በእናትነት ፍቅርም የልጁዋን ወንድሞችና አህቶች ትንከባከባለች፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በአደጋዎችና በሕይወት ችግሮች ውስጥ በማለፍ ወደ ዘለዓለማዊ ቤታቸው እስኪደርሱ ድረስ የዓለም ላይ ኑሮአቸውን እየቀጠሉ ናቸውና” (የአሕዛብ ብርሃን ምዕራፍ 8 ቁ. 62 ተመልከት)፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ፣ “እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርቲያን ከሞት በኋላ ለምትኖረው ሕይወት ልዩ ምልክት ናት” ይላል (አዲሱን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቁ. 972 ተመልከት)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የእምነት እውነት መሆኑን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው የደነገጉበት ሰነድ ሁኔታው እንዴት እንደ ተከሠተ በግልጽ አይዘረዝርም፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ ነበር? ወደ ሰማይ የተወሰደችው በቅድሚያ ነፍሱዋና ሥጋዋ ሳይለያዩ ነበር? እነዚህ ጥያቄዎች ለውይይት ክፍት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ኃይል ወደ ሰማይ የተወሰደችው ልክ እንደ ልጁዋ ከሞተች በኋላ ነበር የሚል ሐሳብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በነፍስና በሥጋ ተከብራ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም አሁን ያለችው በክርስቶስ የምናምነው ሁላችንም ከሙታን ትንሣኤ በኋላ ለመሆን ተስፋ በምናደርገው ዐይነት ነው፡፡