ፈልግ

የታኅሳስ 04/2013 ዓ.ም የ1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት እሁድ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የታኅሳስ 04/2013 ዓ.ም የ1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት እሁድ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የታኅሳስ 04/2013 ዓ.ም የ1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት እሁድ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“እግዚአብሔር በጭራሽ አያሳፍረንም፣ ልባችንን ሲያንኳኳ እንክፈትለት"

የእለቱ ምንባባት

1.      ኢሳያስ 63፡16-17፣ 19፡64 1-7

2.    መዝሙር 79

3.    1 ቆሮንጦስ 1፡3-9

4.    ማርቆስ 13፡33-37

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል 

ቀኑና ሰዓቱ አይታወቅም

ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም። ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤ ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ!”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የመጀመርያ የስብከተ ገና ሳምንት እሁድ እና አዲሱ የዓመቱ የሥረዓተ አምልኮ አመት የመጀመርያ ሳምንት ይጀምራል። ቤተክርስቲያን በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ዋና ዋና ክስተቶችን እና የመዳንን ታሪክ በማክበር በእዚህ የስብከተ ገና ውቅት ውስጥ ትጓዛለች። ይህን በማድረጓ ቤተክርስቲያን እናት እንደመሆኗ መጠን የህልውናችንን መንገድ ታበራለች ፣ በዕለት ተዕለት ሥራችን ትደግፈናለች እና ከክርስቶስ ጋር ወደ ሚደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ትመራናለች። የዛሬው ስርዓተ አምልኮ የመጀመርያውን “አስፈላጊ ወቅት” እንድንኖር ይጋብዘናል ፣ ይኸውም የስብከተ ገና ወቅት እና አሁን የተጀመረው አዲስ የሥረዓተ አምልኮ አመት የመጀመሪያ ሳምንት በተለይም ደግሞ ይህ የስብከተ ገና ወቅት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓለ የሚያዘጋጀን ወቅት ስለሆነ የእርሱን መወለድ በተስፋ የምንጠባበቅበት ወቅት ነው። በጉጉት መጠባበቅ እና ተስፋ ማደረግ።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ (1 ቆሮ 1፡3-9 ይመልከቱ) የምንጠብቅበትን ዓላማ ያመለክታል። የምንጠብቀው ምንድን ነው? “የጌታን መገለጥ በጉጉት መጠባበቅ” (1ቆሮ. 1፡7)። ሐዋርያው ​​የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እና እንዲሁም እኛም ትኩረታችንን ከኢየሱስ ጋር በመገናኘታችን ላይ እንድናተኩር ይጋብዘናል። ለክርስቲያን በጣም አስፈላጊው ነገር ከጌታ ጋር በመሆን ከጌታ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት መፍጠር ነው። እናም በዚህ መንገድ ሕይወት ሰጪ ከሆነው ጌታ ጋር አብሮ የመቆየት ልምድ በማዳበር ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ለመኖር ከጌታ ጋር ለምናደርገው ግንኙነት ራሳችንን እናዘጋጃለን። እናም ይህ ወሳኝ ግንኙነት የሚፈጠረው የዓለም መጨረሻ ሲመጣ ነው። ነገር ግን ጌታ በየቀኑ ይመጣል ፣ ስለዚህ በእሱ ፀጋ በራሳችን ሕይወት እና በሌሎችም ሕይወት መልካም ነገሮችን እናከናውን ዘንድ ይጋብዘናል። አምላካችን የሚመጣ አምላክ ነው ፣ ይህንን መዘንጋት የለብንም፣ እግዚአብሔር የሚመጣ ፣ ያለማቋረጥ የሚመጣ አምላክ ነው። በጉጉት መጠባበቃችን ደግሞ አያሳፍረንም! ጌታ በጭራሽ አያሳፍረንም። እሱ እንድንጠብቅ ያደርገናል ፣ ተስፋችን እንዲበስል ለመፍቀድ በጨለማ ውስጥ ጥቂት ጊዜያትን እንድንጠብቅ ያደርገናል ፣ ነገር ግን በጭራሽ አያሳፍረንም። ጌታ ሁል ጊዜ ይመጣል ፣ እርሱ ሁል ጊዜ ከጎናችን ነው። አንዳንድ ጊዜ እሱ እራሱን እንዲታይ አያደርግም ፣ ነገር ግን እሱ ሁል ጊዜ ይመጣል።  እርሱ በታሪክ ውስጥ በትክክለኛው ጊዜ መጥቶ ኃጢአታችንን ሊሸከም የእኛን ስጋ ለብሶ ሰው ሆነ - የልደት በዓል በታሪክ ውስጥ የኢየሱስን የመጀመሪያ መምጣት ያስታውሳል፣ እርሱ በዓለም ላይ ለመፍረድ በመጨረሻው ቀን ይመጣል፣ እርሱ የሚመጣው የእርሱን የራሱ የሆኑ ሰዎችን ለመጎብኘት ፣ በቃሉ ፣ በቅዱስ ቁርባን ፣ በወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ውስጥ እርሱን የሚቀበሉትን እያንዳንዱን ወንድና ሴት ለመጎብኘት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ኢየሱስ በራችን ላይ ሆኖ ያንኳኳል። በየቀኑ ያንኳኳል። እርሱ በልባችን በር ላይ ነው። እሱ ያንኳኳል። ዛሬ ሊጎበኝዎት የመጣው ፣ ያለ እረፍት ፣ ልብዎን በሀሳብ ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የሚያንኳኳውን ጌታ እንዴት ማዳመጥ እንደሚችሉ ያውቃሉ? ወደ ቤተልሔም መጣ ፣ በዓለም መጨረሻ ይመጣል ፣ ነገር ግን በየቀኑ ወደ እኛ ይመጣል። እንጠንቀቅ፣ ጌታ ሲያንኳኳ በልብዎ ውስጥ የሚሰማዎትን ስሜት ይመልከቱ።

ሕይወት በከፍታዎች እና በዝቅታዎች ፣ በብርሃን እና በጨለማ የተዋቀረ መሆኑን በሚገባ እናውቃለን። እያንዳንዳችን የተስፋ መቁረጥ ፣ የውድቀት እና የጠፋን መስሎን በሚሰማን ስሜቶች ልምድ ሊኖረን ይችላል። በተጨማሪም ፣ በወረርሽኙ የታየው የምንኖርበት ሁኔታ በብዙ ሰዎች ላይ ጭንቀት ፣ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ይፈጥራል። መጽዕይ ጊዜ ጨለማ እንደ ሚሆን በማሰብ ወደ ተስፋቢስነት እና ወደ  ግዴለሽነት የመውደቅ አደጋ እንጋለጣለን። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ፊት ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለብን? ዛሬ የተነበበው የመዝሙረ ዳዊት ተመጽሐፍ እንደሚጠቁመው “ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና መጠጊያችን ነው። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና” (መዝ 33፡20-21) ይለናል። ይህ ማለት ደግሞ የምትጠብቀው ነፍስ ጌታን በልበ ሙሉነት በመጠባበቅ በሕይወታችን ጨለማ ጊዜያት ውስጥ መፅናናትን እና ድፍረትን እንድናገኝ ያስችለናል። እናም ይህ ድፍረት እና ይህ የታመነ ቃል ምን ያስከትላል? ከየት ነው የመጡት? በተስፋ የተወለዱ ናቸው። እናም ተስፋ አያሳፍረንም፣ ከጌታ ጋር የሚገጥመንን በመመልከት ወደ ፊት የሚወስደን ያ በጎነት እና የተስፋ መንፈስ ነው።

ስብከተ ገና ቀጣይነት ያለው የተስፋ ጥሪ ነው - ወደ መጨረሻው ግቡ እንዲወስደው እና ወደ ሙላቱ እንዲመራን እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እንዳለ ያስታውሰናል፣ እርሱም ጌታ ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ይገኛል፣ እሱ “ከእኛ ጋር የሚኖር እግዚአብሔር” ነው ፣ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የልባችንን በር እያንኳኳ ይጠባበቀናል፣ እሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። እግዚአብሔር እኛን ለመደገፍ ከጎናችን ይራመዳል። ጌታ አይተወንም፣ የጉዞውን ትርጉም የዕለት ተዕለት ሕይወት ትርጉም እንድናገኝ ይረዳናል ፣ በሕይወታችን ውስጥ በጭንቀት ውስጥ ሆነን ወይም ስንሰቃይ ድፍረትን ይሰጠናል። በህይወት ማእበል መካከል ፣ እግዚአብሔር ዘወትር እጁን ወደ እኛ ይዘረጋል እና ከስጋቶች ነፃ እንድንሆን ያደርገናል። ይህ ደግሞ መልካም ነው! በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ነቢዩ ለሕዝቡ “በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?” (ዘዳግም 4፡7) የሚል እጅግ ውብ የሆነ ምንባብ እናገኛለን። ማንም የለም ፣ እኛ ብቻ የምንቀርበው እግዚአብሔር ወደ እኛ የሚቀርብበት ጸጋ ነው። እግዚአብሔርን እንጠባበቃለን፣ እሱ እራሱን እንደሚገልጥ ተስፋ እናደርጋለን ፣ ነገር ግን እሱ ራሱ እኛ ራሳችንን ለእርሱ እንደምንገለፅ ተስፋ ያደርጋል!

በጉጉት የመጠባበቅ መንፈስ የነበራት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ የጀመርነው አዲሱ የስርዓተ አምልኮ አመት የመጀመሪያ ሳምንት ላይ እርምጃችንን አጅባ በሐዋርያው ​​ጴጥሮስ የተመለከተውንና በውስጣችን ያለውን ተስፋ በማለምለም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ተግባር ለመወጣት ትረዳን ዘንድ አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

ምንጭ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ፡ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

12 December 2020, 12:54