ፈልግ

IRAQ CHRISTMAS IRAQ CHRISTMAS 

ኢራቅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ወሰነች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከማድረጋቸው ከሁለት ወራት በፊት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ብሔራዊ በዓል እንዲሆን የአገሪቱ ፓርላማ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መላው የኢራቅ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በናፍቆት የሚጠብቀው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚያች አገር የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ብቻ ሳይሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ ፓርላማ ጸድቆ በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር የተወሰነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በታላቅ ደስታ ለማክበር መሆኑ ታውቋል።

በኢራቅ የገና በዓል ታሪክ

የኢራቅ መንግሥት ከዚህ ቀደም፣ በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2008 ዓ. ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በብሔራዊ ደረጃ ተከብሮ እንዲውል ቢወስንም፣ ውሳኔው በቀጣይ ዓመታት ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በኪርኩክ ክፍለ ሃገር ብቻ ተግባራዊ ሲከበር መቆየቱ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2018 ዓ. ም. የኢራቅ መንግሥት በአገሪቱ በሚከበሩት ብሔራዊ በዓላት ላይ ባደረገው ማሻሻያ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በሁለቱም የእምነት ተከታዮች ማለትም በክርስቲያን እና በሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ በብሔራዊ ደረጃ ተከብሮ እንዲውል መወሰኑ ይታወሳል። ወሳኔው ከተደረገ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከያዝነው 2020 ዓ. ም. ጀምሮ ሕዝባዊ በዓል ሆኖ በአገሪቱ በይፋ እንዲከበር መወሰኑ ታውቋል።

የብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ አስተዋጽዖ

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 17/2020 ዓ. ም.  ምስራቃዊ ስርዓት በምትከተል የባቢሎን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በኢራቅ ውስጥ ሕዝባዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ለአገሪቱ ፓርላማ ሃሳብ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ብጹዕ ፓትሪያርክ ሳኮን በቤተመንግሥታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ክቡር ባራም ሳሊ፣ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የያዙትን የሞሱል ክፍለ ሃገርን እና ሰሜናዊውን የኢራቅ ክፍለ ሃገራትን መልሶ በመገንባት ሥራ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ያበረከተው አስተዋስጽዖ ከፍተኛ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በማለት የኢራቅ ፓርላማ መወሰኑን የሰሙት፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ በመልዕታቸው፣ ለአገሪቱ ፕሬዚደንት ክቡር ባራም ሳሊ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ክርስቲያን ማኅበረሰብን በማስታወስ መልካም ስላደረጉላቸው የፓርላማው አፈ ጉባኤ ለሆኑት ለክቡር ሙሐመድ ሐልቡስን እና ለመላው የፓርላማ አባላት የእግዚአብሔርን ቡራኬ ተመኝተውላቸዋል። ክቡር ፕሬዚደንት ባራም ሳሊ በበኩላቸው፣ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች አስገዳጅነት ከሞሱል እና ከነነዌ ክፍላተ ሃገራት የተፈናቀሉ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የሚመለሱበትን መንገድ የሚያመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለአሥራ አምስት ወራት አቋርጠው የቆዩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊ አቶ ማቴዎ ብሩኒ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

19 December 2020, 20:33