ፈልግ

የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ወደ ግብጽ ያደረገው ስደት የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ወደ ግብጽ ያደረገው ስደት 

ካርዲናል ቪንሴንት፥ ቤተሰብ እና ቤተክርስቲያን ደግነት የሚገለጽባቸው ሥፍራዎች ሊሆኑ ይገባል አሉ።

የእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደትን እና የዌስት ሚኒስተር ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ የቅድስት ቤተሰብ ቀን ተከብሮ በዋለበት በታኅሳስ 18/2013 ዓ. ም. ለምዕመናን ባቀረለቡት መልዕክት፣ ቤተሰብ እና ቤተክርስቲያን ደግነት እና ደስታ የሚገኝባቸው ሥፍራዎች ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ የቅድስት ቤተሰብ ዓመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “ምዕመናን መጸለይ ያለባቸው ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ጭምር  እንደሆነ አሳስበው፣ እነዚህ ሁለት ሥፍራዎች በመከራ ጊዜያት ውስጥ ርኅራሄ፣ ምሕረት እና ፍቅር የሚገለጽባቸው ፍራዎች ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።

ኮቪድ-19 ቤቶቻችን እንዲናጉ አድርጓል

“ecology” ወይም ሥነ ምህዳር የሚለው ቃል መሠረታዊ አመጣጡ “oikos” ከሚለው የግሪክ ቃል፣ ትርጉሙም “ቤት” ማለት እንደሆነ በማስረዳት አስተንትኖአቸውን የጀመሩት ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ፣ ይህ ትርጉም የሚገልጸው የምንኖርበትን ዓለም ብቻ ሳይሆን የምንኖርበትን ቤት እና ቤተክርስቲያንን ጭምር መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ሁለቱ መኖሪያ ቤቶቻችን ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጎዳቱን አስታውሰው፣ ማኅበራዊ ሕይወት ፈተና ውስጥ በመውደቁ የተነሳ ሰዎች በገንዘብ አቅም ማነስ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አስረድተዋል። ከሚወዱት ሰው መለየት ከፍተኛ ሐዘንን እንደሚያስከትል የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽ ብዙ ሰዎች ለሚወዷቸው እንኳን ሐዘናቸውን በሚገባ እንዳይገልጹ እድል ሳይሰጥ እንዲለዩ አድርጓቸዋል ብለዋል። “በቅድስት ቤተሰብ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ መኖሪያ ቤቶቻችን የደግነት እና የደስታ ሥፍራ እንዲሆኑ በማለት ዘንድሮ የእግዚአብሔርን ቡራኬ የጠየቅንበት ነው” ብለዋል። ሐዋ. ጳውሎስ ወደ ቆላስያስ ሰዎች የጻፈውን መልዕክት በማስታወስ፣ ሐዋርያው በመልዕክቱ “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” ማለቱን እና ሐዋርያው ከሁሉ በላይ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት አስታውሰው፣ ቤተክርስቲያን ማለት ፍቅርን እና ርኅራሄን ለዓለም እንድንመሰክር በእግዚአብሔር የተመረጥን እኛ ሰዎች መሆናችንን አስረድተዋል።

ለቤተሰቦቻችን እና ለቤተክርስቲያን መጸለይ ይገባል

በእንግሊዝ፣ የዌስት ሚኒስተር ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት ባሰሙት ስብከት ምዕመናን ለቤተሰቦቻቸው እና ለቤተክርስቲያን መጸለይ እንደሚገባ አሳስበው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት ወራት ቤተክርስቲያንም በጭንቅ ውስጥ መቆየቷን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት አክለውም ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ያህል በእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሕጻናት እና በአቅመ ደካሞች ላይ ጥቃት ሲደርስባቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዓይንን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ ይገባል

ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ ለአገራቸው ካቶሊካዊ ምዕመናን ባቀረቡት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ምዕመናን ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለከቱ አደራ ብለው “እግዚአብሔር ዘወትር ከእኛ ጋር በመሆን የራሱ አካል የሆነችውን ቤተክርስቲያን ፈጽሞ አይተዋትም” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ “አባታዊ ልብ” በማለት ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ መልዕክት በማስታወስ “ቅዱስ ዮሴፍ የቤተክርስቲያን ጠባቂ እና የችግር ጊዜ አጽናኝ በመሆኑ የመማጸኛ ጸሎታቸውንን ወደ እርሱ ማቅረብ ይገባል” በማለት ብርታትን ሰጥተዋል። “ሕመም እና ችግር የበዛበትን የዘንድሮ ዓመት ለማገባደድ በተቃረብንበት ጊዜ ሕይወታችን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ መቆየቷን፣ መንፈስ ቅዱስም ቤተክርስቲያናችንን ዘወትር እንደሚጠብቃት እና ዓለምም የእግዚአብሔር እጅ ድንቅ ሥራ ውጤት መሆኑን መመልከት ያስፈልጋል” በማለት የእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደት እና የዌስት ሚኒስተር ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮላስ ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።              

29 December 2020, 15:30