ፈልግ

ያለ አጋዥ የቀሩ ብቸኛ አረጋዊያን፤ ያለ አጋዥ የቀሩ ብቸኛ አረጋዊያን፤ 

አቡነ ቦካርዶ፣ ለአረጋዊያን እና ለሕሙማን ቸርነትን በተግባር መግለጽ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

በጣሊያን ውስጥ የስፖሌቶ-ኖርቻ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሬናቶ ቦካርዶ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የብቸኝነት ስሜት ለጎዳቸው አረጋዊያን እና ሕሙማን ቸርነት የተሞላበት እንክብካቤን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳሱ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት ለሀገረ ስብከቱ በጎ ፈቃደኞች እና ለጋሽ ማኅበረሰብ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው። ብጹዕ አቡነ ቦካርዶ በማከልም ዕርዳታን ለሚፈልጉት በሙሉ፣ ትንሽም ቢሆን የተቻለን በማድረግ ቸርነትን መግለጽ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማኅበረሰብ መካከል አቅመ ደካማ ለሆኑት አረጋዊያን እና ሕሙማን በቸርነት ልብ ተነሳስተን አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሬናቶ ቦካርዶ፣ እሑድ ታኅሳስ 11/2013 ዓ. ም. በሀገረ ስብከት ለሚገኙ በጎ ፈቃደኞች እና የዕርዳታ አድራጊ ድርጅቶች ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ምክንያት በማድረግ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንብን ለማክበር ሲባል በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ጥቂት የሚባሉ የበጎ አድራጊዎች ማኅበራት ተወካዮች ብቻ መገኘታቸው ታውቋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ዕርዳታን ለሚማጸኑ አዛውንት እና ሕሙማን በቀዳሚነት መደረግ ያለበት ተግባር ቁሳዊ ዕርዳታን ከማቅረብ በተጨማሪ የመንፈስ ብርታትን እንዲያገኙ ከአጠገባቸው ሆኖ ማጽናናት እንደሚገባ ብጹዕ አቡነ ሬናቶ ባካርዶ አሳስበው፣ የኮሮና ቫይሬስ ወረርሽኝ በሰዎች መከከል ፍርሃትን በማንገሥ ግንኙነትን ሊቀንስ እንደሚችል አስረድተዋል። ምዕመናን ቸርነትን በመግለጽ በብቸኝነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት አረጋዊያን እና ሕሙማን ጥቂት ቢሆንም አቅም የሚፈቅደውን እገዛ እንዲያደርጉ አደራ ብለው፣ ይህን እና ሌሎች ዕርዳታዎችን በማድረግ አስፈሪውን ጊዜ ተደጋግፈን ለመሻገር በኅብረት መጓዝ እንችላለን ብለዋል።

ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት ዕርዳታን ማቅረብ

በጣሊያን ውስጥ የስፖሌቶ-ኖርቻ ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ኤድዋርዶ ሮሲ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር ከሁለት ወራት በፊት በሀገር ስብከታቸው የሚገኙ ዕርዳታ ፈላጊዎችን ለመደገፍ በተነደፈው መርሃ ግብር መሠረት፣ የቸርነት ተግባራትን በአዲስ ልብ እና ድፍረት ለማከናወን፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ቀድሞ በመረዳት ተግባራዊ ለማድረግ መጠራታቸውን ገልጸዋል። የቤተክርስቲያን ምልክት የሆነውን የቸርነት ሥራ በማበርከት የተቸገሩትን ለመርዳት የተጠሩ መሆናቸውን አስረድተው፣ የበጎ አድራጊ ድርጅታቸው ዋና ዓላማ የፍቅር አገልግሎትን በስውር መግለጽ ነው ካሉ በኋላ ይህም የእግዚአብሔር እርዳታ የሚገለጽበት መንገድ መሆኑን ክቡር አባ ሮሲ አስረድተዋል። ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ኤድዋርዶ ሮሲ፣ ይዚህ ተግባር ለማከናወን ቅን ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩ ወጣቶችን ማሳተፍ እንደሚገባ እና በአዲስ ወኔ፣ በድፍረት ወደ ፊት መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ተነሳሽነት ያላቸው ወገኖች ሊኖሩ ይገባል

በጣሊያን ውስጥ የስፖሌቶ-ኖርቻ ሀገረ ስብከት ከዚህ ቀደምም እርዳታን የማሰባሰብ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ በተጨማሪም አዳዲስ ተግባራትን በማከል ምዕመናን በብርሃነ ልደቱ በዓል ዕለት ለድሆች ምግብ የማዳረስ አገልግሎት የሚያቀርቡ መሆኑ ታውቋል። በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኝ፣ የዴ ካሮሊስ የአልቤርጎ መስተንግዶ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችም በግል ተነሳሽነት የተለያዩ ምግቦችን ለድሆች ሲያከፋፍሉ የቆዩ ሲሆን እንደዚሁም ሌሎች የትምህርት ተቋማት መምህራን የአረጋዊያንን የስልክ ጥሪ ተቀብለው አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሳቸው አድረገዋል። ከዚህ በተጨማሪም በስፖሌቶ የባቡር ጣቢያዎች ለሚገኙት መጠለያ አልባ ለሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሀገረ ስብከቱ በጎ ፈቃደኞች ምግብን በማከፋፈል አገልግሎታቸውን አበርክተዋል።        

23 December 2020, 13:52