ፈልግ

መንፈሳዊ ልግስና መንፈሳዊ ልግስና 

መንፈሳዊ ልግስና

በሥጋዊ ነገር እጀ ሙሉ ሰው ይወደዳል፣ ይፈለጋልም፡፡ በሰው ሁሉ ዘንድ “ለጋስ$ እየተባለ ይጠራል፡፡ እንደ አቅሙም ያህል የልግስና ሥራውን ያሳያል፡፡ ከሰዎቻችን ማለት ከወዳጆቻችን መካከል ብዙዎቹ በጐ አድራጊዎችና ለጋሶች እንዲሆኑ እንወዳለን፡፡ በተቻለን መጠንም እነርሱን ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን፣ ለእነርሱ ስንል ከመቸገር እንደርሳለን፡፡ ስለአምላካሀችንና ስለ ነፍሳችን ብለን እንደዚህ እናደርጋለን ወይ; እግዚአብሔር አምላከችን ከእኛ አንድ ነገር ሲፈልግ እንሰጠዋለን ወይ; በአጭር አነጋገር በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲህ ያለ ልግሥና አለን ወይ; መንፈሳዊ ልግስና በጣም ስለማይሆንልን አብዛኛዎቻችን ይህ ዓይነቱ በጐ ተግባር ይጐድለናል ለማለት ያስደፍረናል፡፡

በመንፈሳዊ ሕይወታችን ብዙ ንፍገት ስላለብን ስለ ነፍሳችን ደኀንነትና ጥቅም ስለ እግዚአሔር ክብር መሥራት ይሰለቸናል፣ መታከትም ስለሚያጠቃን ወደኋላ እናፈገፍጋለን፡፡ ታዲያ ይህ ምንድን ነው; ከባድ ነው; አልችለውም ግዴታ እኮ አይደለም ጥቂት ይበቃል እያልን ቁጠባ ስናደርግና ስንቆጣጠር እንገኛለን፡፡

እግዚአብሔረን በልግስና አናገለግለውም እርሱ ከእኛ የሚፈልገውን ተደስተን መፈጸሙን ችላ ስለምንል ስለ እርሱ ትንሽ ተጋድሎ ማድረጉን እንሸሻለን፡፡ ለእግዚአብሔር ለነፍሳችንም ልግሥና ስለሌለን፡፡ የሚጠቅመንን በጐ ሥራ ለመሥራት ትጋትና ንቃት ያጥረናል፡፡ ለነፍችን ከሚያስፈልጉን ብዙ ነገሮች መካከልም ለጥቂቶቹ ብቻ እንቆማለን፣ ወይም እናተኩራለን፣ ከዚህ አልፈን ልንሞክር አንፈልግም፡፡ ጸሎት፣ በጐ ሥራ፣ ምስጢራትን መሳተፍ፣ ተጋድሎና በያይነቱ መንፈሳዊ ምግባሮችን ግብር ማብዛትን እንጠላለን፡፡ ይህ ሁሉ ምን ያደርጋል አያስፈልግም ጥቂት ነው የሚበቃው በማለት ከመንፈሳዊ ሥራ ራሳችንን እናርቃለን፡፡

ነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሎት” ይላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “እግዚአብሔር የሚወደው በደስታ የሚሰጠውን ሰው ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ለመስጠት የፈለገውን በልቡ ፈቅዶ በደስታ ይሰጥ እንጂ እየተጸጸተ ወይም በግዴታ አይሰጥ” ይላል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ከመጠን በላይ ለጋስ ነው፣ የማይሰጠን ነገር የለም፣ ሁሉን ይሰጠናል፡፡

እርሱ ለነፍስም ሆነ ለሥጋ የሚጠቅመንን ሁሉ ይህ ነው በማይባል መጠን ይሰጠናል፡፡ ይህን ሊነገር በማይቻል ልግስና የሚሰፈልገንን ሁሉ የሚያስብልንና የሚወደንን ፈጣሪያችን እኛም በልግስና ልንከሰው ባለንም ኃይል ሁሉም ልንወደውና በደስታም ልናገለግለው ይገባናል፡፡ ስናገለግለውም ስንፍናን፣ ንፍገትን፣ ሃኬትንም ትተን ትጋትንና ፍቅር እንልበስ፡፡ የነፍሳችን ደህንነት በተጋድሎና በለጋስነት የሚገኝ በመሆኑ በንፈሳዊ ሥራችንና አረማመዳችን ሁሉ ኃይላችንንና ችሎታችን መቆጠብን እናስወግድ፤ ይህስ በዛ፣ አያስፈልገኝም አንበል፡፡ ይህ ይበቃኛል የሚልና ጥቂትን የሚወድ ብዙና ብርቱ የሚጠላን ሰነፍና ንፉግ መንፈሰ ከእኛ በማራቅ መንፈሳዊ ልግስናን እንሸምት ይህንን ካደረግን ወደ ቅድስና እንደርሳለን፣ እግዜአብሔርንም በሚገባ እናስደስተዋለን፡፡

02 November 2020, 12:59