ፈልግ

የፋጢማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፖርቱጋል የፋጢማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፖርቱጋል  

እመቤታችን ድንግል ማርያም የኃጢአተኞች ተገን ናት

የቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ስንደግም እምቤታችን ድንግል ማርያምን “ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን ልጅሽን ለምኚልን…..» እያልን እንማጠናታለን፣የልባችንን ምኞት እንገልጥላታለን፡፡በሊጣንያ ደግሞ “የኃጢአተኞች አጽናኝ ሆይ ለምኚልን» እንላታለን፡፡

በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ ዘወትር ኃጢአት ከእኛ ጋር ነው፡፡ ምከንያቱም ሰይጣን እኛን ከመፈተን አያርፍም&ጥረቱንም አያቋርጥም፡፡ የሰው ልጅ በሞላው በመንፈስ ባለመጠንከሩ ትንሽ ወይም ትልቅ ኃጢአት ይፈጽማል፡፡ በምስጢር ንሰሐ ቢሰረይለትም ጥቂት ቆይታ ተመልሶ ወደ ኃጢያት ይወድቃል፡፡ እነደገና ተጸጽተን ንሰሐ እንገባለን፣ ተመልሰን ወደ ኃጢአት እንወድቃለን፡፡ እንደዚህ እያደረግነ ከኃጢአት ወደ ኃጢያት እየወደቅንና ከፈተና ጋር እየታገልን እንኖራለን የኃጢያት ባርነት አድካሚና ኃይለኛ ግዞት በመሆኑ ብዙ ሊያስጨንቀን ይችላል&አንዳንዴ ቢያሸንፈንም፣ ቆርጠን ከተነሳን ግን ድል እናደርጋለን፡፡ ከኃጢያት ጋር በምናደርገው ጦርነት ድል እንድንቀዳጅና እንድናሸንፍ እግዚአብሔርን ስለሚፈልግ ይህችን የተመረጠችና በጸጋ የተሞላች እናት ሰጠን፡፡ የኃጢያት ማዕበል ሊውጠን ሲቃረብ ተገንና መጠጊያ ስለምትሆነን አንዳንዴ በኃጢአት ተሸንፈን ብንወድቅ ተስፋ ቆርጠን የኃጢአት ቁራኛ እንዳንሆን በቅድስት ድንግል ማሪያም ዕርዳታና እርሷን ተደግፈን ከኃጢአት እንነሳለን፡፡ እኛን ደካሞችና ምስኪኖች ወደ እግዚአብሔር እንድታቀርበንና ምሕረቱን እንድታማልድልን በጥበቃዋ ሥርም እንድንሆነ ስለፈለገ መረጣት፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም ከደኀንነታችን በስተቀር ሌላ ምኞትም የላትም፡፡ ለእኛ ለኃጢአተኞች ተስፋና መድኃኒት የደኀንነታችን ዋስትና በመሆኗ ደስተኛ ናት፡፡ ከኃጢአት ጋር በምደርገው ውጊያ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ናት፡፡ የንጹሐን ንጽሕት የቅዱሳን ሁሉ ቅድስት ስለሆነች የሰይጣን ተቋዋሚና የኃጢያት ቀንደኛ ጠላት በመሆኖ እኛን ልጆቿን ከሰይጣን እጅና ቀንበር ከአስፈሪ ጥፋትም እንዲያድን ትፈልጋለች፡፡ በዚህ ሕይወት እያለን እርሷን መስለንና የእርሷን ንጽሕና ተከትለን እንድንኖርና ከሞትንም በኋላ በሰማይ ከእርሷ ጋር እንድንደሰትና እንድንነግስ ምኞትዋ ነው፡፡በመሆኑም በመንግስት ሰማያት ሆና እኛን ኃጢአተኞችን ለማዳን ታማልዳለች፡፡

            በእመቤታችን አማላጅነት፣ዕርዳታና አጋዥነት ብዙዎች የታወቁ ኃጢአተኞች ተብትቦ አስሯቸው የነበረውን የኃጢያት ሰንሰለት በጣጥሳው ከአምላካቸው ጋር ታርቀው ደኀንነታቸውን አግኝተዋል፡፡ ከኃጢያት ከአጸያፊና አስነዋሪ ሕይወት ወደ ጽድቅ የተሻገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ኃጢአተኞች ወደ ጽድቅ መንገድ ለመመለስ ያደረገችው ተአምራት ብዙ በመሆኑ ለመቁጠርም ያዳግታል፡፡

አባታችን ቅዱስ በርናርዶስ (1090-1153 ዓ.ም) “ፈተና ቢመጣብህ ማርያምን ጥራ በመጥፎ ነገር ብትታወክ በተስፋ መቁረጥም በሐዘን ልትወድቅ ብትጀምር ማርያምን አስብ» እያለ ይመክረናል፡፡ ደካማና ያልጠነከረ ባሕሪያችን ወደ ኃጢአት ሲጐትተንና ሲፈትነን ይህችን የኃጢአተኞች መጠጊያ እንመልከት፡፡ “የኃጢአተኞች መጠጊያ ሆይ ለምኚለኝ»እያልን እንለምናት& ወደ እርሷ እንቅረብ፡፡ እርሷ በርኀራኄና በደግነት እንደምትቀበለን እንመን በምንም ምክንያት አንጠራጠር፡፡

25 November 2020, 12:52