ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት 

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ

“የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” (ማቴ. 5 ፥9)

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ በንጹሐን ወገኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት መፈናቀል እና የንብረት ውድመት በጽኑ ታወግዛለች። በንጹሐን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የሚፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ቤተክርስቲያናችንን ጥልቅ ሃዘን ውስጥ ከትቷታል። እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ እና አፍቃሪ አባት በመሆኑ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመው እንዲህ ዓይነት በደል በእጅጉ ያሳዝነዋል። የሰው ልጅ ክቡር ነውና በክብር ልንንከባከበው እንጂ ልናሰቃየው፣ ልናሳድደው እና ልንገድለው በፍጹም አይገባም። በምንም ምክንያት እና ዓላማ ፈጽሞ የሰው ልጆች ደም መፍሰስ የለበትም። የሰውን ክብር የሚያጎድፍ እና ለስቃይ፣ ለእንግልት እንዲሁም ለሞት የሚያጋልጥ ማናቸውም ዓይነት ተግባር በማንኛውም አካል ሊፈጸም አይገባም። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕዝቦች በመከባበር፣ በመወያየት እና በመነጋገር በጋራ እንዲኖሩ እና ለጋራ ሀገራቸው ብልጽግናም ተባብረው እንዲሠሩ ትመኛለች፣ ትጸልያለች።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የዘለቀውን አለመግባባት ለማርገብ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሃይማኖት አባቶች፣ በሃገር ሽማግሌዎች እና በሚመለከተቸው ወገኖች የተደረገው ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ በመካከላቸው እየተባባሰ የመጣው አለመግባባት ዛሬ ወደ ግጭት ደረጃ ላይ መድረሱ እጅጉን አሳዝኗታል። ወደጦርነት የሚያመሩ አማራጮች በወንድማማች ሕዝቦች መካከል መተላለቅን ከመፍጠር ባሻገር ምንም ጠቀሜታ የላቸውም። ወንድማማች ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው ቢገዳደሉ ኢትዮጵያ የምታተርፈው ምንም ነገር የለም። ይልቁንም መላይቱን ሀገራችንን ወደ ውድቀት እና ኪሳራ የሚመልስ እና ማንንም ወገን ተጠቃሚ የማያደርግ ተግባር ነው። በመሆኑም ሁለቱም ወገኖች በአስቸኳይ አሁን የገቡበትን የተካረረ ሁኔታ በማቆም ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ እና በሰከነ አስተሳሰብ በመመራት በመከባበር፣ በመደማመጥ እና በመተማመን ላይ በተመሰረተ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ እንማጸናለን።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ግጭት በቀላሉ እንዲመለከተው አንሻም። ይልቁንም በአንክሮ በመመልከት እና ለመንግሥታት ብቻ የማይተው መሆኑን በመገንዘብ ዕርቅ እንዲሰፍን፣ ሕዝባዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ሰላም እና ጸጥታም እንዲረጋገጥ ሁሉም በባለቤትነት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በሀገራችን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ የማይጥሉ እና ሀገርንም ከማትወጣበት አዘቅት ውስጥ የማይከትቱ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ሆናችሁ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን የምታቀርቡ ባለሞያዎች በሙሉ የሙያ ሥነ ምግባርን የተከተሉ፣ ግጭትን የማያባብሱ እና ሕዝብን በሕዝብ ላይ የማያነሳሱ ዘገባዎችን በጥንቃቄ እንድትሠሩ ዐደራ እንላችኋለን።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ሕይወታቸው ላለፈ ዜጎች የተሰማትን ልባዊ ሃዘን እየገለጸች እግዚአብሔር ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥ ትመኛለች።

በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም የምትኖሩ ካቶሊካውያን በሙሉ ሀገራችን በዚህ ወቅት ያለችበትን ሁኔታ በአንክሮ በመገንዘብ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በልዩ ትኩረት ሰለ ሰላም እና ሰለ ዕርቅ ልዩ ጸሎት እንድታደርጉ እና ቢኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተላለፈው ጥሪ መሰረት ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ሁሉ በጸሎት እንድትተባበሩ እናሳስባችኋለን።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል

የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳሳት

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት

የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ፕሬዝደንት

04 November 2020, 23:13