ፈልግ

እኛ ካቶሊካዊያን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስሎች እንወዳለን እኛ ካቶሊካዊያን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስሎች እንወዳለን 

እኛ ካቶሊካዊያን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስሎች እንወዳለን

ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስንገባ ሁል ጊዜ የክርስቶስ ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳንን ምስል እናያለን፣ በቤታችንም ቢሆን የክርስቶስ መስቀልና የቅዱሳን ሰዎችን ምስል ወይም ሥዕል ማስቀመጥ የተለመደ ነው።፣በዚህም ምክንያት አንዳንድ የሚከሱን ፤ የሚወቅሱንና የሚነቅፉን ሰዎች አሉ፡ “እናንተ ካቶሊኮች የእንጨት መስቀልና የድንጋይ ሐዉልት ታመልካላችሁ” መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ታመልከዉ ዘንድ ማናቸዉንም ዓይነት ጣዖት አትሥራ፣ እንዲሁም ምስል ወይም ሐዉልት ወይም የተቀረጸ የድንጋይ ዐምድ አታቁም” ይላል (ዘሌ. 26፣1) ይሉናል፣ ለእንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች በአክብሮት እንዲህ እያልን እንመልሳለን።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እኛ ካቶሊኮች የእንጨት መስቀል ወይም የድንጋይ ሐዉልቶችን  በፍጹም አናመልክም፤ እኛ የምናመልከዉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ያለዉንና ህያዉ የሆነዉን ክርስቶስን ነዉ፣ የሆነ ሆኖ በመስቀል ስለእኛ ብሎ ተሰቅሎ የሞተዉን ጌታችንን የሚያስታዉሰንና እሱን የበለጠ እንድንወደዉ የሚረዳን ማስታወሻ እንጂ ማምለኪያ አይደለም። እስቲ በየቤታችን ስለምንሰቅለዉ የወላጆቻችን ፎቶ እናስብ፤ የነሱን ፎቶ በምንመለከትበት ጊዜ በህይወት ሳሉ ለእኛ የነበራቸዉን ፍቅርና መልካም ሥራ ሁሉ እናስታዉሳለን። በተመሳሳይ ሁኔታ በግድግዳ ላይ የምንሰቅለዉ የክርስቶስ መስቀል ወይም የሱ ምስል ለእኛ የነበረዉን ፍቅርና እሱ ለእኛ ያደረገዉን መልካም ሥራ ሁሉ ያስታዉሰናል፡፡

እኛ ካቶሊኮች በዚህ ዓይነት የቅዱሳን ምስሎችን፤ ለምሳሌ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን፤የቅዱስ ዮሴፍን፤ የቅድስት ቴሬዛና የቅዱስ ፍራንቼስኮስን ወ. ዘ. ተ. ስእሎች ወይም ምስሎች በቤታችን ማስቀመጥ እንወዳለን፣ አሁንም ታዲያ ይህን የምናደርገዉ እነዚህን ሰዎች ስለምናመልካቸዉ ሳይሆን ስለምንወዳቸዉ ነዉ፤ በእምነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለሆኑ ነዉ፣ አንዳንዴ እንዲያውም በእምነት ቅደመ አያቶቻችን ብለን እንጠራቸዋለን። እነሱ መልካም አርአያዎቻችንም ናቸዉ። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ምስል በቤታችን ብናስቀምጥ ምን ችግር አለ?

በአጭሩ፤

እኛ ካቶሊኮች ከሙታን የተነሳዉንና በመካከላችን የሚገኘዉን ክርስቶስን እንጂ ሌላ ማንንም አናመልክም፡፡

የእንጨት መስቀል ለእኛ ሲል በመስቀል ተሰቅሎ የሞተዉን ክርስቶስን የሚያስታውሰን ማስታወሻ ብቻ ነዉ፣ ክርስቶስን የበለጠ እንድንወደዉና የየዕለት መስቀሎቻችንን ከሱ ጋር ሆነን በመሸከም ክርስቲያናዊ ጉዞአችንን በጽናት እንድንጓዝ ያደርገናል፡፡

የቅዱሳን ሰዎች ምስል ልክ የቤተሰብ አልበም ወላጆቻችንን እንደሚያስታዉሰን በእምነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሆኑ ሰዎችን ከነሥራቸዉ የሚያስታዉሰን ነዉ። በተጨማሪም ክርስቶስን እነሱ በተከተሉት መንገድ እንድንከተለዉ ያበረታቱናልና እኛ ካቶሊኮች የቅዱሳን ሰዎችን ምስል በቤታችን ማስቀመጥ እንወዳለን።

ስለዚህ ሥዕሎችና ምስሎች በቤታችን ለቤተሰብ አባላት ሁሉ ምቹ የሆኑና የካቶሊካዊ ቤታችን ማስጌጫ ናቸዉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስና ምስሎች

መጽሐፍ ቅዱስ በእየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዉስጥ ስለነበረዉ ከእንጨት ስለተሠራ ምስልና ሙሴ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሠርቶ በበረሃ ስለሰቀለዉ የነሐስ እባብ ይነግረናል፣ በአንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 6፡23-28 እንዲህ የሚል ነገር እናነባለን።“የእያንዳንዳቸዉ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ምስሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ዉስጥ ሠራ።”

ንጉሥ ሰለሞንና ሕዝቡ እነዚህን ምስሎች አላመለኳቸዉም፣ ነገር ግን እነዚህ ምስሎች በጊዜዉ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ በመላዕክት ተከበዉ በእግዚአብሔር ጥበቃ ሥር እንዳሉ፤ እግዚአብሔር ከነሱ ጋር እንዳለ እንዲረዱ፤ ያ ስሜት በዉስጣቸዉ እንዲፈጠር ረድቷቸዋል፣ በተመሳሳይ ምክንያት ነዉ እኛ ካቶሊኮች የእንጨት ምስሎችንና ሥዕሎችን የምንሠራዉ፤ መስቀልን ስናይ ከሙታን የተነሳዉ ክርስቶስ ስለእኛ የተሰቀለዉና የሞተዉ ክርስቶስ አሁን በመካከላችን እንዳለ ይሰማናል፣ የቅዱሳን ሰዎች ምስልም ክርስቶስን እነሱ በተከተሉት የቅድስና መንገድ እንድንከተለዉ ያነሳሳናል።

በኦሪት ዘኁልቁ 21፡8-9 እንዲህ የሚል እናነባለን «እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ ሙሴን “አንድ የነሐስ እባብ ሠርተህ በረዥም ትክል እንጨት ላይ ስቀለዉ፤ በእባቡ የተነከሰ ሁሉ እርሱን በሚያይበት ጊዜ ይድናል” አለዉ።’’

የእስራኤል ሕዝብ ግን የነሐስ እባቡን አላመለከዉም፤ የነሐሱ እባብ እግዚአብሔር ቃል በገባላቸዉ መሠረት እንደሚያድናቸዉ፤ እንደሚፈዉሳቸዉ የሚያሳስብ ምልክት ነበር፣በተመሳሳይ ሁኔታ እኛ ካቶሊኮች የእንጨት መስቀል ከተሰቀለበት የክርስቶስ አካል ጋር ስናይ ይህንን የእንጨት መስቀል እያመለክን ሳይሆን ይህ የተሰቀለዉ ክርስቶስ አዳኛችንና ፈዋሻችን እንደሆነ እናስባለን፡፡

በተለያዩ ባህሎች የሚገኙ አርቲስቶች እምነታቸዉን በሥነ-ጥበብ ሥራቸዉ ይገልጻሉ። አንዳንድ የአፍሪካ አርቲስቶች ክርስቶስን አፍሪካዊ አድርገዉ መሥራትን ይወዳሉ፤ የእስያ አርቲስቶችም እስያዊ ያደርጉታል፤ አዉሮጳዊያንም አዉሮጳዊ ያስመስሉታል። ለምንድነዉ እንደዚህ የሚያደርጉት?

ይህን በማድረጋቸዉ ሁሉንም ሕዝብና የሰዉን ዘር ሁሉ እኩል በሚወደዉ ክርስቶስ ላይ ያላቸዉን እምነት ይገልጻሉ፣ እሱ በአፍሪካ፤በእስያ፤ በአዉሮጳ … ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል ይላሉ፣ እሱ እያንዳንዳችንን ያዉቃል፤ እያንዳንዳችንን ይመስላል፤ ሕይወታችንን ሕይወቱ አድርጓል፣እነዚህ አርቲስቶች ማርያምን አፍሪካዊት፤ እስያዊትና፤ አዉሮጳዊት ሲያደርጓት በጥበብ ሥራቸዉ አማካይነት ማርያም የሰዉ ዘር ሁሉ እናት መሆኗን ያበስራሉ፣ እሷ እንደ እኛዉ ናት እኛን ትወደናለች  ለእኛ ቅርባችን ናት ብለው ያስባሉ፡፡

ምንጭ፡ የካቶሊካዊ እምነታችን ማንነትና ምንነት በምል አርእስት የካፑቺን ማሕበር አባል በሆኑት በክቡር አባ አበራ ማኬቦ የተዘጋጀ።

26 November 2020, 12:57