ፈልግ

የሕዳር 13/2013 ዓ.ም የ32ኛው እሁድ ቃለ እግዚአብሔር እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ የሕዳር 13/2013 ዓ.ም የ32ኛው እሁድ ቃለ እግዚአብሔር እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ 

የሕዳር 13/2013 ዓ.ም የ32ኛው እሁድ ቃለ እግዚአብሔር እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     መጽሐፈ ጠበብ 6፡12-16

2.     መዝሙረ ዳዊት 62

3.     1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13- 18

4.     ማቴዎስ 25፡1-13

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ

“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን መስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ አምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።

“በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ። “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። (ማቴዎስ 25፡1-13)

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዛሬ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 25:1-13) ወደ እግዚኣብሔር መንግሥት ለመግባት ማድረግ የሚጠበቅብንን ቅደመ ሁኔታዎችን ይጠቁማል። ኢየሱስ ይህንን ሙሽራውን የመቀበል ኃላፊነት የተጣለባቸውን እና በዚያን ዘመን የሰርግ ስነ-ስረዓት ይካሄድ የነበረው በማታ በመሆኑ የተነሳ ኩራዛቸውን ይዘው በማታ የወጡትን ዐስር  ልጃገረዶች ምስሌ በመጥቀስ ያስረዳል።

የዛሬ የወንጌል ምሳሌ ከእነዚህ አዐሥሩ ሴቶች መካከል 5 አስተዋዮች አምስቱ ደግሞ ዝንጉዎች መሆናቸውን በመገልጽ፣  ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው የነበረ ሲሆን መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጭኗቸው ተኙ። እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ።

“በዚህን ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ። “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።

በዚህ ምሳሌ ኢየሱስ እኛን ምን ማስተማር አስቦ ነበር? እርሱን ለመገናኘት ሁል ጊዜ ተዘጋጅተን መኖር እንዳለብን ያስተምረናል። ብዙን ጊዜ ኢየሱስ በወንጌል ውስጥ “ነቅታችሁ ጠብቁ” ይለናል፣ እንዲሁም ዛሬ በዚህ የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ ማብቂያ ላይም “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ” በማለት ያሳስበናል። በዚህ ምሳሌ ነቅታችሁ ጠብቁ የሚለው ቃል እንቅልፍ አለመተኛት ማለት ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ተዘጋጅቶ መጠበቅ ማለት ነው እንጂ። በእርግጥ እነዚህ ዐሥር ልጃገረዶች  ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ተኝተው ነበረ፣ ነገር ግን ሙሽራው በመጣበት ወቅት ገሚሱ ነቅተው ተዘጋጅተው ይጠበቁ ነበረ፣ ገሚሱ ደግሞ ነቅተዋል ግን ዝግጁ አልነበሩም። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ አስተዋይ እና ጠንቃቃ ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ ከዚህ መረዳት እንችላለን፣ ይህም ከእግዚኣብሔር ፀጋ ጋር የምንተባበረው በመጨረሻው የሕይወታችን ሰዓት ላይ መሆን እንደማይገባው ነገር ግን ከአሁኑ መጀመር እንደ ሚገባን ያስገነዝበናል።

በምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው መብራቱ የሕይወታችንን ብርሃን የሚያበዛው የእምነት ምልክት ሲሆን ዘይት ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ የበጎ አድራጎት ምልክት ተምሳሌት ሲሆን ይህም እምነታችን ፍሬያማ እና ታዕማኒ እንዲሆን ያደርገዋል። ከጌታ ጋር ለመገናኘት የምናደርገው ቅድመ ዝግጅት በእመንት ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በርስ ፍቅር የሞላበት ክርስቲያናዊ ሕይወት በመኖርም ጭምር ሊሆን ይገባል። ለእኛ የሚስማማን እና ምቾት የሚሰጡን ነገሮች በመከተል የራሳችንን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች ብቻ በማሳደድ በምንሯሯጥበት ወቅት ሁሉ ሕይወታችን መካን ይሆናል፣ ለእምነታች ብርሃን የሚሰጠውን ዘይት የማከማቻ ሰዓት እናጣለን፣ ስለዚህ እመነታችን መብራት ጌታ ከመምጣቱ በፊት ይጠፋል ማለት ነው። ነገር ግን በተቃራኒው ነቅተን የምንጠብቅ ከሆንን እና መልካም ተግባራትን እያከናወንን የምንኖር ከሆንን፣ ይህንንም በፍቅር፣ ካለን ባማካፈል፣ በችግር ውስጥ የሚገኙትን ባልንጀሮቻችንን በማገዝ የምንኖር ከሆንን ግን ሙሽራው በሚመጣበት ሰዓት ተረጋግተን መቀበል እንችላለን፣ ጌታ እኛ ባልጠበቅንበት ሰዓት ሊመጣ ይችላል፣ ሞትም እንኳን ሊወስደን በሚመጣበት ሰዓት ምንም ነገር አያስፈራንም፣ ምክንያቱም መጠባበቂያ የሆነ ዘይት ስለያዝን ነው፣ ይህም በመልካም ተግባራችን ያጠራቀምነው በእየቀኑ ያከናወነው መልካም ሥራችን ከእኛ ጋር ስለሚኖር ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም እምነታችንን ሁል ጊዜ በመልካም ተግባራት የታጀበ እንዲሆን ትርዳን፣ ምክንያቱም የእኛ የእምነት ብራሃን እዚሁ በምድራዊ ሕይወታችን እያለን በደንብ እንዲበራ እና ከዚያም ቡኃላ ደግሞ በመግሥተ ሰማይ ሙሽራው በሚያዘጋጀው ድግስ ላይም እንዲያበራ ትርዳን። አሜን!

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እሁድ ሕዳር 13/2010 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

21 November 2020, 10:53