ፈልግ

መኖር የሚገባን እምነት መኖር የሚገባን እምነት 

መኖር የሚገባን እምነት

በእምነት ዓመት እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ምእመን በሀገር፣ በሀገረ ስብከት እና በቁምስና ደረጃ በሚሰጠው ትምህርት መሠረት ከክርስቶስ ያገኘውን እምነት ለመኖር ብሎም ለመንከባከብ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት አለበት፡፡ እምነት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ቁልፍ የሆነ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም (ዕብ. 11፡6) ፡፡ እምነት የእግዚአብሔር ቃል እውነት የመሆኑ የዋስትና ስሜትና በዚያ ሕያው ቃል መኖር በረከትን እንደሚያስገኝ እርግጠኛ መሆን ነው፡፡

ሰውን የሚያድነው ምን ዓይነት እምነት ነው? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ሲናገር «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም» (ማቴ.7፡21) ብሏል፡፡ የሚያድነን እምነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምያስፈጽም ነው፡፡ እውነተኛ የሚያድን እምነት ወደ ተግባር ይመራል፡፡ ኃይል ያለው እምነት በእውቀት የሚገኝ ጥልቅ ምርምር ወይም ስሜታዊ ክንዋኔ አይደለም፤ በፈቃድ ላይ ወደ ተመሠረተ መታዘዝ የሚመራ ነው፡፡ ይህ መታዘዝ ደግሞ የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመን ሁሉ የሚቀጥል ነው፤ ወደ ተግባር የሚመራ ነው፡፡ ሐዋርያው  ቅዱስ ጳውሎስ «እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው» ብሏል (ሮሜ. 10፡17) ፡፡ እምነት መልካም የሚሆነው ከምናምንበት ጉዳይ አንጻር ነው፡፡ ደኅንነት ያገኘነው እምነትን በማመን አይደለም፤ ነገር ግን በቃሉ በተገለጠልን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በማመን ነው፡፡ ይህንን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤን የሚታውጅልን የእርሱ ሙሽራ የሆነችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ማኅደረ ሃይማኖት ናት፡፡

 

2. ስለ ሥላሴ ያለን እምነት

እኛ የምናምነው አምላክ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አብ፤ የእርሱም አንድያ ልጅና መንፈስ ቅዱስ «ቅድስት ሥላሴ ነው»፡፡ የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር የክርስትና እምነትና ሕይወት ሁነኛ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ በእግዚብሔር በራሱ ውስጥ ያለ ምሥጢር ነው፡፡ የድኅነት መላው ታሪክ አንድ እውነተኛ አምላክ፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ራሱን ለሰዎች የሚገልጥበት መንገድና ብልሃት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ አንድ ነው፡፡ ሦስት አማልክት አሉ ብለን አናምንም፤ ሦስት አካላት ያሉት አንድ አምላክ፣ «የሥላሴ አንድነት» እናምናለን፡፡ ይህም መለኮታዊ አካላት አንድ መለኮት የሚጋሩ ሳይሆን እያንዳንዳቸው በምሉእነት አምላክ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ አንዱ መለኮታዊ አካል ከሌላው ይለያል፡፡ «እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ግን ብቸኛ አይደለም»፡፡ አንዱ አካል ከሌላው በግልጽ ይለያና «አብ»፣ «ወልድ»፣ «መንፈስ ቅዱስ» ለመለኮታዊው ሕላዌ የተሰጡ ስሞች ናቸው፡፡ «አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ ሲሆን፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሠራፂ ነው፡፡» (ት/ክርስቶስ፤81-82) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ «የምኖርለትንና የምሞትለትን፣ እንደ ቅርብ ወዳጄም እንዳይለየኝ የምፈልገው፣ ክፋትን ሁሉ የሚያስችለኝንና ሐሴትን ሁሉ የሚያስንቀኝን ታላቅ የእምነት ሀብት ማለቴ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚሆነውን እምነቴን ከምንም ነገር በላይ ጠብቁልኝ፡፡ ዛሬ ይህንን ለእናንተ አደራ ሰጥቼአለሁ፡፡ የምሰጣችሁም አንድ ሆኖ ሦስት አካላት ያሉት፣ ሦስቱን በግልጽ ልዩነት ያካተተ አንድ መለኮትና ኃይል ነው» (ት/ክርስቶስ፤83) ብሏል፡፡

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ «እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ ራሱን ሊገልጥና የሰው ልጅ ሥጋ በሆነው ቃል ማለትም በክርስቶስ አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ወደ አብ የምንደረስበትንና በመለኮታዊ ባኅርይ ተካፋይ የሚሆንበትን የፈቃዱን ምሥጢራዊ ዓላማ ለኛ ሊያሳውቅ ወደደ» (2ኛ ቫቲካን መሎኮታዊ መገለጥ 1፡2) ይላል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ራሱንና የራሱን ዕቅድ ለእኛ ለልጆቹ መግለጡ እውነታ ከእኛ ተግባራዊ ምላሽ ይጠይቃል፡፡ ያም ተግባራዊ ምላሽ «እምነት» ይባላል፡፡ ወደ ዕብራውያን በተላከው መልእክት ጻሐፊው ስለ እምነት ሲገልጽ « እምነት ማለት በተስፋ የሚጠበቀውን ነገር አዎን በእውነት ይሆናል ብሎ መቀበል ነው፤ በዐይን የማይታየውንም ነገር እንደሚታይ አድርጎ መቊጠር ነው» (ዕብ. 11፡1-2) ይላል፡፡ እምነት እንደራዕይ ለማየትም ሆነ ለማረጋገጥ በማንችላቸው እውነታዎች አኳያ ጽኑ እምነትን፣ ቁርጥ አሳብንና ተአማንነትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ነው፡፡ እምነት እግዚአብሔር በገለጣቸው እውነቶች መሠረት በመኖርና በማመን እርሱንና የርሱን ሕይወት መቀበል ነው (እምነታችን ፡15)፡፡ በእግዚአብሔር እውነትና ሕይወት የማመን በነርሱም መሠረት የመኖርና ብርታት የምናገኘው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው (ዮሐ. 14፡1-2) ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እምነት ሲናገር «አሁን በመስተዋት እንደምናየው ዐይነት በድንግዝግዝ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ግን በግልጽ እናያለን፤ አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያህል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል» (1ቆሮ. 13፡12) ብሏል፡፡

እግዚአብሔር በመሠረቱ ምሥጢር ነው፡፡ ምሥጢራዊ የሆነውን ስሙን ያሕዌን «እኔ ያለሁ እሱ ነኝ»፣ «እኔ የሆንሁ ነኝ» ወይም «ያለና የሚኖር ነኝ» (ዘጸአት 3፡14) ብሎ ለሙሴ ሲናገር እግዚአብሔር ማንነቱንም ምን ተብሎም እንደሚጠራ ተናግሯል፡፡ ይህ መለኮታዊ ስሙም ምሥጢራዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስውር አምላክ ነው፤ ስሙም በቃላት የማይገለጽ ነው፤ የእግዚአብሔር ማንነት በሰው አንደበት ሊገለጽ አይችልም፡፡ እርሱ ራሱን የሚገልጽ ከሁሉም የላቀ ማለትም ከፍጥረቱ ሁሉ ፍጹም ልዩና ሊደረስበት የማይቻል ሆኖ ነው፡፡ ከዚህም በቀር፣ እግዚአብሔር ዓለምን የሞላ፣ ማለትም፣ በፍጥረቱ ዘንድ የሚገኝና ከርሱም ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ አንዳንድ መለያ ጠባያት የርሱን ግርማ ሞገስና የበላይነትነት አጉልተው ሲያሳዩ፣ ሌሎቹ ባህርያት ስለ እኛ ያለውን ቅርበትና አሳቢነት በአጽንኦት ያወሳሉ (እምነታችን፤ገጽ. 22) ፡፡    

3. በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለን እምነት፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል መሆኑን ሐዋርያት ይመሰክራሉ፡- «ቃል በመጀመሪያ ነበር፤ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበር» (ዮሐ.1፡1) በማለት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እርሱ «ለማይታየው እግዚአብሔ ምሳሌ፤ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ የባሕሪውም ማኅተም ነው» (ቈላ.1፡15፣ ዕብ.1፡3) ብሏል፡፡

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡» (ዮሐ.3፡16) ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ከሁሉም የበለጠ ነገር፣ ይኸውም፣ ዘላለማዊ ደኅንነትን አስገኝቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና «እምነት ጉዞ» እምብርት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ከፍተኛው መግለጫ ነው፡፡ ራሱ ሲናገር «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፣ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡ እኔን አውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፡፡» (ዮሐ.14፡6-7) ብሏል፡፡ እርሱን ማውቅ የምንችለው በእምነት ነው፡፡  

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለሰው ልጆች «አዳኝ» (ማቴ.1፡21) ነው፡፡ ደኅንነት እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ለእኛ ያሰበልን በጎ ነገርና ደስታ ነው፡፡ በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ያገኘነው ደኅንነት የኃጢአት ቁስላችን ፈውስ፣ የእግዚአብሔር ሰላም ነው፡፡ ደኅንነት ከእግዚአብሔርና ከሰው ሁሉ ጋር አንድ አካል እንዳንሆን ያደረገን የተቋረጠ ግንኙነት መጠገኛ ነው፡፡ በክርስቶስ ያገኘነው ደኅንነት በእኛ ላይ የሚፈስ የእግዚአብሔር ቡራኬና ጸጋ ከመሎኮታዊ ቤተሰቡ (ቅድስት ሥላሴ) ጋር የመቀላቀያ፣ ሕይወቱን ከእኛ ጋር መጋሪያ ነው፡፡ የጌታችን አዳኝነት የእርሱ ፍቅር፣ የእርሱ አገልግሎት፣ የእርሱ መሥዋዕትነት፣ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አማካይነት ሞት ራሱ አብሮ ሞተ፡፡ የትንሣኤ ሕይወት ተጀመረ፡፡ ጌታችን በአዳኝነቱ ያደረገውን ማለትም የኃጢአት ስርየትንና የዘላለማዊ ሕይወት ስጦታን ሌላ ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም (እምነታችን፤55)፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናምን በዚህ ደኅንነት ምሥጢር እናምናለን፡፡

4. በመንፈስ ቅዱስ ያለን እምነት፤

የእምነት ቀዳሚ ምሥጢር በሆነው ጥምቀታችን ኃይል መሠረትነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ከአብ መንጭቶ በወልድ አማካይነት ስለተሰጠን ሕይወት በጥልቀትና በግል ይገልጽልናል፡፡ በጸጋው አማካይነት እምነትን በውስጣችን በማስጀመር አዲሱን ሕይወት ለእኛ በማስተላለፍ ረገድ መንፈስ ቅዱስ ግምባር ቀደም ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ማመን፣ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ሥላሴ አካላት አንዱ መሆኑን ከአብና ከወልድም ጋር አንድ ህልውና ያለው መሆኑን ማመን ነው፡፡ እርሱ «አብና ከወልድ ጋር አብሮ ይሰገድለታል፤ ይከብራልም፡፡» የደኅንነታችን እቅድ ተጀምሮ ፍጻሜ እስከሚያገኝ ድረስ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ አብ ወደ ልባችን የላከው፣ መንፈስ፣ በእውነት አምላክ ነው (ገላ.4፡6)፡፡ ከአብና ከወልድ ጋር ህልውናው አንድ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ በሥላሴ ውስጣዊ ሕይወትና ለዓለም ባበረከተው ፍቅር ጭምር ከእነርሱ ፈጽሞ አይለይም፡፡ አብ ቃሉን በሚልክበት ጊዜ እስትንፋሱንም ሁልጊዜ ይልካል፡፡ በጋራ ተልእኮአቸው ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለዩ ቢሆኑም አይነጣጠሉም፤ እርግጠኛ ለመሆን የማይታየው እግዚአብሔር ገሀድ ተምሳሌት ክርስቶስ ቢሆንም፣ የሚገልጠው ግን መንፈስ ቅዱስ ነው (ት/ክርስቶስ፤ 208-209) ፡፡ ይህ የጌታ መንፈስ በእያንዳንዳችን ላይ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት በምንቀበልበት ጊዜ ያርፋል፡፡ ይህ አንዱ መንፈስ እንደየ ስጦታችን እግዚአብሔርን እንድናገለግል ያነሣሣናል፤ ያው አንዱ የጌታ መንፈስ እንደምመራን እስከ ዕለተ ሞታችን በእግዚአብሔር ፊት እንመላለሳለን፡፡ እግዚአብሔር ዛሬ በውስጣችን አድሮ የሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይልና ሙላት እንደሆነ እናምለን፡፡

5. እመቤታችን ድንግል ማርያም መድኃኔ ዓለም እናት መሆኗን ማመን፤

«እግዚአብሔር ልጁን ላከልን» በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንድፀነስም ፈቃዱ ሆነ፤ ነገር ግን ሥጋን ሊያዘጋጅለት የአንድ ፍጡር ነጻ ትብብር ፈለገ፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ከሁሉ አስበልጦ የእስራኤል ልጅ የሆነች፣ በናዝሬት በገሊላ የምትኖር፤ አንዲ አይሁዳዊት ወጣት ሴት፣ «ለዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለተባለ ሰው የታጨች ድንግል መረጠ፤ የድንግላዊቷም ስም ማርያም ነበር» (ሉቃስ 1፡26-27) ፡፡ መልአኩ ገብርኤል የምሥራቹን ሲያበሥራት «አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን» (ሉቃስ 1፡28) አላት፡፡ በእርግጥም፣ ማርያም ለጥሪዋ በእመነቷ ነጻ እሽታዋን መስጠት ትችል ዘንድ በእግዚአብሔር ጸጋ መሞላት ነበረባት፡፡ ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ማርያም በእግዚአብሔር «በጸጋ የተሞላች፤» ያለ አዳም ኃጢአት ከተጸነሰችበት ጊዜ ጀምሮም የተቀደሰች  መሆኗን በሚገባ ተገንዝባለች፡፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ IX በ1854 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ «እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከተፀነሰችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሁሉን በሚችል አምላክ ልዩ ጸጋና ክብር፣ እንዲሁም የሰው ዘር አዳኝ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ትሩፋት፣ ከአዳም ኃጢአት ሙሉ በሙሉ የተጠበቀች ናት» (Pius IX, Infabillis Deus, 1854:Ds 2803, 1:28) ብሏል፡፡ የካቶሊክ እምነት ስለ ማርያም ያለው እምነት መሠረት በክርስቶስ ላይ ያለው እምነት ነው፡፡ ማርያም «ከተፀነሰችበት ከመጀመሪያይቱ ሰዓት አንስቶ» የተጎናፀፈችውን ፍጹም ልዩ የሆነ የቅድስና ድምቀት ሙሉ በሙሉ ያገኘችው ከክርስቶስ ነው፡፡ እርሷ «በልጇ ትሩፋት እጅግ በላቀ ሁኔታ የተቀደሰች» (2ኛ ቫቲካን ቤ/ክ ቀኖናዊ አቋም 53፡56) ናት፡፡ እግዚአብሔር አብ ማርያምን ከሌላው ሁሉ ሰብአዊ ፍጡር አስበልጦ «በሰማይ ሁሉንም በረከት በክርስቶስ በመስጠት» (ኤፌ.1፡3-4) ቅድስትና ነውር የሌለባት ሆና በፊቱ እንድትገኝ ዓለም ሳይፈጠር በክርስቶስ ቀድሷታል፤ መርጧታልም (ት/ክርስቶስ፤144)፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን ያላት ሚና ከክርስቶስ ጋር ካላት አንድነት የማይነጠልና ከእርሱም በቀጥታ የሚመነጭ ነው፡፡ «በማዳን ሥራ ረገድ የእናትና የልጅ አንድነት ከክርስቶስ በድንግልና መጸነስ ጀምሮ እስከ ሞቱ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይገለጻል» (2ኛ ቫቲካን ቤ/ ክ ቀኖናዊ አቋም 57)፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ማንኛውም ሰው ከአንድ አባትና ከአንዲት እናት የተወለደች አይሁዳዊት ነች፡፡ ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋት ግን የእግዚአብሔር ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ እውነት ራስዋ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ስትናገር «ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሰም በመድኃኔ ትደሰታለች፤ እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና፤ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይለኛል ምክንያቱም ኃያሉ እግዚአብሔር ትልቅ ነገር ስላደረገልኝ ነው፤ ስሙም ቅዱስ ነው» (ሉቃስ 1፡46-49) ብላለች፡፡ ማርያም ከእግዚአብሔር ነጻ ምርጫ የተነሣ በጸጋ የተሞላች ነች፡፡ በእግዚአብሔር ጸጋ የተሞላ ሰው በሚገኝበት ሥፍራ ሁሉ እግዚአብሔር ሕያውና የሚሠራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ለሌሎች መስጠት የሚችለው ትልቁ ነገር እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ ይህንን እውነት ማርያም ዘመድዋን ኤልሳቤጥን በጎበኘችበት ጊዜ ከተፈጸመው ድንቅ ሥራ መርዳት ይቻላል፡፡ ማርያም ስትጎብኛት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላች፤ በማህጸንዋም የነበረው ሕፃን በደስታ እንደ ዘለለ ቅዱስ ሉቃሰ ይናገራል (ሉቃስ 1፡43-45) ፡፡ ከዚህ የተነሣ ነው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ማርያም ባለችበት እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አለ የሚሉት፡፡ እርስዋ የቅድስት ሥላሴ ቤተመቅደስና የአዲስቷ ሄዋን የክርስቶስ ምድራዊ ገነት ነችና፡፡ ስለዚህም ከሌሎች ተለይታ የአምላክ እናት ሆናለች፡፡ የክብርዋና የልዕልናዋ መሠረት ይኸውም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደኅንነት ሥራ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን ያህል የላቀ ሙያ ለማከናወን የተጠራችው የእመቤታችን ድንግል ማርያም ስም ልዩ አድናቆት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ከዘለዓለም ጀምሮ ማኅደሪያ እንድትሆነው ከፍጡራን ሁሉ  በላይ ልዑል አሸብርቆ የፈጠራት ሴት ናትና ልዩ ናት፡፡ ልዩ የሚያደርጋትም ያለ አዳም ኃጢአት ተፀንሳ መወለድዋ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ «ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ» (መዝ. 45፡5) ይላል፡፡ ጥንትም ይሁን ዛሬ ልዑል እግዚአብሔር የሚያርፍበት ቦታ የተቀደሰ፣የተባረከ ነው፡፡ እመቤታችን ልዑል አምላክ በመሎኮቱ ያረፈበት ቦታ ብቻ ሳትሆን የልዑል አምላክ ማደርያም ነበረች፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ድንግል ማርያም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናትና የእኛም እናት መሆኗን እናምናለን፡፡

6. በአማላጅነት ያለን እምነታችን፤

የእምነት ዐምድ የሆነችሁ ቅድስት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያናችን በማርያምና በቅዱሳን አማላጅነት እንድናምን ታስተምረናለች፡፡  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድን ቅዱስ ወደ መንበረ ታቦት ከፍ የምታደርገው እግዚአብሔር ያን ቅዱስ ተጠቅሞ ለሰው ልጆች ያደረገውን ድንቅ ሥራውንና መለኮታዊ ቸርነቱን ለማወጅ ነው፡፡ የቅድስና ሕይወቱን ከእኛ ከፍጥረታቱ ጋር የሚካፈለውን እግዚአብሔርን ሊትወድስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር «እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» (ዘሌ.19፡2) ይለናል፡፡ ቅድስና ባሕርይ የእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ፣ ቅድስናውን ከማንም ያልተዋሰው ወይንም ያልተቀበለው፣ ማንም ሊወስድበት የማይችል የራሱ ሀብት የሆነ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ቅድስና ከእርሱ እርሱም ከቅድስና ተለይተው የማይታሰቡ ናቸው፡፡ በእርሱ ዘንድ ከቅድስና በስተቀር ሌላ ነገር የማይታሰብበት፤ በቅድስናው እንከን፣ ከሁሉ ልዩ በመሆኑ ሐሰት የሌለበት አምላክ ነው፡፡ ስለሆነም #ቅዱስ እግዚአብሔር$ ይባላል፡፡

ሰዎች ቅዱሳን የሚባሉት በፊታቸው ከተዘረጉላቸው ሁለት አቅጣጫዎች እውነተኛውንና ቀጥተኛውን የመረጡ፤ ከተከፈቱላቸው ሁለት በሮች በጠባቧ ለመግባት የወደዱ፣ የተጣራ የሕይወት አቋም የነበራቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ብዙ ጊዜ ሳይታዩና ዓለም ሳይቀበላቸው፣ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ሳያውቀአቸው፣ ነገር ግን በአብ ዘንድ ተወዳጅ ሆነው በጌታችን እርሻ ሳይደክሙና ሳይታክቱ የሠሩ ናቸው፡፡ ለራሳችን ብቻ ስንሠራ በመንፈስ ከመሻገት ይልቅ ለክርስቶስ እየሠራን በሥጋ ብንደክምና ብንሞት ይሻላል ብሎ የክርስቶስን የመረጡ የእምነት አርበኞች ናቸው፡፡ ቅድስና ለክርስቶስ ተከታዮች የተሰጠ «የክብር ማስረጃ» ነው፡፡ እነዚህን ታላቁን መከራ ያለፉትን እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው የሆነ አብነታቸውን እንድንከተል፤ እነርሱ የደረሱበትን ለመድረስና አማላጅነታቸውን እንድንጠይቅ ለእኛ ታቀርብልናለች፡፡ አብነታቸውም እኛ ራሳችን ወደ ቅድስና በሚናደርገው ጉዞአችን ጀግንነትን፣ ትዕግሥትን፣ ቆራጥነትን ወዘተ የሚጠይቁ የአገልግሎት ተግባራትን እንድከናውን ይቀሰቀቅሱናል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን እምነት ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ሆነው ያማልዱልናል፡፡ በዛሬው ዓለማችን ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም እና ስለ ቅዱሳን አማላጅነት ስንናገር ደስ የማይላቸው ልኖሩ ይችላሉ፡፡

በእርግጥ አመላጅ ማለት ምን ማለት ነው? ምልጃ ማለት፤ አንዱ ስለሌላው የሚያደርገው ልመናና ጸሎት ነው፡፡ የሚለመነው እግዚአብሔር ሲሆን የሚያማልዱት ደግሞ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ምልጃ የታዘዘውና ያስፈለገው እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች ይልቅ የጻድቃንን ጸሎት የበለጠ ስለሚሰማ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ዳዊት #የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸው$ (መዝ.34፡15) ይላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም #የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች$ (ያዕ.5፡16) ÃLM፡፡ በመጻሐፈ ምሳሌም #እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል$ (መ.ምሳሌ 15፡29) ይላል፡፡

አመላጅነት የሚንጠይቃቸው ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር የበለጠ ለሰዎች ርኅሩሆችና ደጎች ስለሆኑ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር የበለጠ ለሰው ልጆች አዛኝና መሐሪ የለም፡፡ ምልጃ በእግዚአብሔር ሥልጣን ጣልቃ መግባትም አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እንደ አምባገነን መሪዎችም አይደለም፡፡ ራሱ አንዱ ስለሌላው እንዲጸልይና እንዲለምን ያሳሰበ፤ ሳይለምኑት ሲቀሩ ሳይሆን ሲለምኑት ደስ የሚለው ቸር አምላክ ነው፡፡ ሲለምኑት ደስ የሚለው ብቻ ሳይሆን እኛ ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች ወገኖቻችን ስንለምነው ለእኛው ለራሳችን ዋጋ የሚሰጥም ፍጹም ደግ አባት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ #በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሀ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል$ (ዮሐ.7፡38) ብሏል ፡፡ እንዲሁም #እኔ የምሰጠው ውሀ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል$ በማለት እርሱን ያመኑና በጸጋ ላይ ጸጋ እስኪሰጣቸው ደረሰው የከበሩ ወዳጆቹ እግዚአብሔር የሚሰጠው ጸጋና በረከት እንዲሁም ሕይወት በእነርሱ አማካይነት ሲሰጥ የሚኖር መሆኑን ይገልጻል (ዮሐ.4፡14)፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን የሕይወት ውሀ ወንዝ መፍለቂያዎች ናቸው፡፡

በሌላው አንድም ፍጡር መቼም ቢሆን ሥጋን ከለበሰው ከእግዚአብሔር ቃልና መድኃኒት፤ ቤዛ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ ማወዳደር ራሱ የተሳሳተ አሳብ ነው፡፡

የአዳኙ ልዩ አስታራቂነት ከዚህ ከአንድ ምንጭ የመጋራትን ዘርፈ ብዙ ትብብር ይፈጥራል እንጂ አያግድም:: እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፡፡ እኛ እርስ በርስ ከተፈቀርን የእግዚአብሔር ፍቅር አንቀንስም፡፡ ይልቁንም በሥራችን ጎልቶ እንዲታይ እናደርጋለን፡፡ አማላጅነትም እንደዚያው ነው፡፡ ከሰው ልጅ ከጥልቅ ማንነቱ ለሚነሡት መሠረታዊ ለሆኑት ለሕይወት ጥያቄዎች ከእግዚአብሔር የተሰጠው ብቸኛ መልስ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑንም የሌሎች የአማላጅነት ሚና በምንም መልኩ በጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ አይችልም፡፡ ኢየሱስ አስራቂያችን ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ እርቅ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በሰው፣ በሰውና በፍጥረታት መካከል ከኃጢአት የተነሣ የተፈጠረውን የጠላትነትን ግድግዳ በማፍረስ ሰላምን የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ ሰላማችን ነው፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ለሰዎች ምሕረቱን፣ ፍቅሩን፣ ይቅርታውን፣ ቸርነቱን የሚገልጸው በሰዎችና በሰዎች አማካይነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር የተመረጡ ጻድቃን ሰዎች ሊያማልዱልን እንደሚችሉ እናምናለን፤ ይሁንና እግዚአብሔር አማላጅነትን በሙላት የገለጸው አንድ ልጁ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው፡፡ እርሱ የአማላጆች ሁሉ አማላጅ ነው፡፡ የሌሎች የአማላጅነት ሚና ትክክለኛ ትርጉምንና ዋጋን የሚያገኘው ከእርሱ ነው፡፡

7. ስለ ሞትና ስለ ወዲያኛ ዓለም ያለን እምነት፤

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ፤እኛንም ከሞት በኋላ በመጨረሻዋ ቀን ከሞት አስነሥቶ ከእርሱ ጋር ለዘላለም ያኖረናል ብለን እናምናለን፤ ተስፋም እናደርጋለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እስካደረ ድረስ ያው መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለና ኢየሱሰን እነዳስነሣው ሁሉ በሚሞተው ሰውነታችን ውስጥ ሕይወትን ይዘራልናል (ሮሜ.8፡11)፡፡

ሞት የሥጋዊ ሕልውናችን ማክተሚያ በመሆኑ ምንጊዜም አስፈሪ ነው፡፡ ከሞት በኋላ የሚሆነውን ስለማናውቅ እንፈራዋለን፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ህልውና ከፍ ያለ እንቆቅልሽ ሆኖ የሚገኘው ሞት በሚገጥመው ጊዜ ነው፡፡ ሰው የሚጨነቀው በሕመምና በሥጋው እርጅና ብቻ ሳይሆን፤ በይበልጥ የሚጨነቀው ደግሞ በዘላለማዊ ሞት ስጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰው ሞትን የሚቃወምበት ምክንያት ወደ ሌላ ነገር ዝቅ የማይል መለኮታዊ ዘር በአካሉ ስላለ ነው፡፡ ሰው በሞት ፊት በማንኛውም ረገድ ተሸናፊ ሆኖ ቢታይም እንኳን ቤተ ክርስቲያን ከመለኮታዊ ግልጸት ባገኘችው ትምህርት ሰው ምድራዊ መከራ በማይደርስበት ለታላቅ ደስታ በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ ታረጋግጣለች፡፡ በተጨማሪም ክርስቲያናዊ እምነት እንደሚያስተምረው በሞት ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለው ኃያሉ ቸር የሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክፉ ሥራ ጠፍቶ የነበረውን ሰው ወደ ድሮው ሁኔታ በሚመልስበት ጊዜ፤ ሰው ኃጢአት በማድረጉ የመጣበትን ሥጋዊ ሞት፤ ድል ይመታል (2ኛ ቫቲካን በዚህ ዘመን ስለምትገኘው ቤ/ክ 18)፡፡ ሰው በተፈጥሮ ሟች ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ከመጀመሪያው እንዲሞት አልወሰነበትም ስለዚህም ሞት ከፈጣሪ እግዚአብሔር እቅድ ጋር የሚቃረንና በምድር ላይ በኃጢአት ምክንያት የመጣ ነው፤ ሰው ኃጢአተኛ ባይሆን ኖሮ ከሞት ነፃ በሆነ ነበር (ት/ክርስቶስ፤299)፡፡

የእግዚአብሔር ቃል  እግዚአብሔር የሕይወት ምንጭ መሆኑን ይናገራል፡፡ ሕይወት የሚገኘው ከእርሱ ነው፡፡ ለሚፈልገው ሕይወትን ይሰጠዋል (መዝ.104፡27-30)፡፡ ሞት በኢየሱስ ክርስቶስ ተለውጧል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ» ብሏል (ዮሐ.11፡25)፡፡ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መስዋዕት ሆኖ መሞት የሞትን ርግማን ወደ ጽድቅ ለውጦታል (ሮሜ. 5፡19-21)፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምክንያት የክርስቲያን ሞት አዎንታዊ ትርጉም አለው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ጥቅም ነውና» (ፊልጵ.1፡21) ብሏል፡፡ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምኑ በመንፈስ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት እንደመሆኑ መጠን በእርሱ ለሚያምኑት ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ቢሞቱም እንኳ ሕያዋን ናቸው፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ «ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም» (1ዮሐ.5፡12)  ብሏል  ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለተነሣ በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ ደግሞ እንደሚነሡ ታውቆአል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ አማኞች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በሞት፣ በትንሣኤና በዕርገት ከክርስቶስ ጋር ተባብረናል፡፡ ይህ በክርስቶስ ያገኘነው ከፍ ያለ ሥፍራ መላምት ወይም ገና ልንደርስበት የሚገባን ግብ ሳይሆን የተፈጸመ እውነት ነው፡፡ ክርስቶስ ዘላለማዊ ሕይወታችን ነው፡፡ የዘላለማዊ ሕይወት ማለት እኛ ኃጢአተኞች በአዳኛችን ስንታመን እግዚአብሔር የሚሰጠን ሰማያዊ ስጦታ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለማዊ ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድራችን የመጣው ለእኛ ነው፤ የሞተውም ለእኛ ነው፤ የተነሣውም ለእኛ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው በእኛ ስም ነው፡፡ ስለዚህ በስሙ ያመንን ሁሉ የክርስቶስ አካል ሆነናል፤ እንዲሁም ለእርሱ የሆነውም ሁሉ ለእኛ ሆኖአል ወይም ተደርጎአል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣው እኛን አብሮ አስነሣን አብሮም በሰማያዊ ሥፍራ አስቀመጠን፡፡ ይህ ነው ካቶሊካዊ እምነታችን!

8. ምሥጢራት ላይ ያለን እምነት፤

ምሥጢር የሚለው ቃል መሠረቱ «ሰጠረ» ከሚለው የግእዝ ግሥ የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም በቁሙ መመስጠር፣ መሰወር፣ መደበቅ፣ ማልበስ፣ መሸሸግ፣ እንዳይታይ ማድረግ ሲሆን፣ ምሥጢረ ሲል ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ አምላካዊ ተግባርን፣ መንፈሳዊ ረቂቅ በሰው ልጆች የማይታይ፣ የማይታወቅ፣ ነገር ግን የሚታመንና የመደነቅ ተግባርን ወይም ሁናቴን ያመለክታል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ደግሞ ምሥጢር ሲባል ለብዙ ዘመናት ተሰውሮ የኖረ አሁን ግን በወንጌል የተገለጠ ከእግዚአብሔር የወጣ የእውነት ቃል ትምህርት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በዐይን የማይታይ ረቂቅ በመሆኑ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የዓለም ሕዝቦች የተለያዩ ቁሳቁሶችና የተለያዩ ምልክቶን ይጠቀማሉ፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማምለክና እምነታቸውን ለመግለጽ በተለያዩ መልክ ለእግዚአብሔር ልመናቸውን፣ ምሥጋናቸውንና ውዳሴያቸውን በሚታዩ ምልክቶች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ምሥጢራት ብለን የምንጠራቸው ናቸው፡፡

ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ ሊዮ እንዳሉት «በቅዱሳት መጽሐፍት ትምህርት፣ በሐዋርያዊ ትውፊቶችና በአበው ስምምነት ጸንተን የአዲስ ኪዳን ምሥጢራት ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተሠሩ ናቸው ብለን እናምናለን» ብሏል (st.Leo the Great, Sermo.74,2:PL.54.398)፡፡

በቤተ ክርስቲያን አጠቃቀም ምሥጢር ማለት ዐይን በሚያያቸውና እጆች በሚዳስሳቸው ቁሳቁሶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት እንቅስቃሴዎች በመጠቀም ረቂቅና መልዕተ ባሕርይ የሆኑ ነገሮች መወከልና መድረስ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር መሎኮታዊነት የማይታይ እንደሚታይ፣ የማይጨበጥ እንዲጨበጥ የሚደረግበት እምነት መንገድ ነው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን በምሥጢራት የምንጠቀምባቸው ምልክቶች ከጥንት ቤተ ክርስቲያን የወረስናቸው ሲሆን ምንጫቸው ከመጽሐፍ ቅዱስና በተለይም ከወንጌል ነው፡፡ እነዚህ ምልክቶች ዘወትር ለተለመዱ ሥራዎች በምንጠቀምባቸው ጊዜ የሚያስከትሉት ውጤት የመልዕተ ባሕርይ ፀጋዎች ምንጭ ነው፡፡

ምሥጢራት ምን ጊዜም ሕያውና ሕይወት ሰጪ ከሆነው ከክርስቶስ አካል የሚወጡ ኃይላት ናቸው (ሉቃ.5፡17፤5፡19፣8፡46)፡፡ አካሉ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የሚገለጥባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ በአዲሱና በዘላለማዊው ኪዳን ውስጥ «የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራዎች» ናቸው (ት/ክርስቶስ፤ ገጽ. 333)፡፡

         ምሥጢራት በግል ደረጃም ሆነ በአንድነት ስናያቸው የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት ምልክቶች ናቸው፡፡ ምሥጢራትን በምንቀበልበት ጊዜ ገደብ የሌለው የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ውስጥ ይሞላል (ዮሐ.3፡5)፡፡ ስለዚህ ስለ ምሥጢራት በምናስብበት ጊዜ የመጀመሪያው ግንዛቤ የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክቶች መሆናቸው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ሙሉ በሙሉ የተገለጠልን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለአይሁዳውያን ምሥጢር ነበር (ኢሳ.7፡14)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቃይቶ በመሞቱ፣ ከሞት በመነሣቱ ለእኛ እርቅንና ሰላምን አመጣልን፡፡ ስለዚህም ምሥጢራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመጣልን ፀጋዎች በምልክቶች እንዲፈፀሙና ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡

         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕርገት ወደ አባቱ ክብር ስለተመለሰ በሰው ዘንድ የማይታይ ሆነ (ኤፌ.1፡2)፡፡ በዚህ ጊዜ በጥበቡና በፍቅሩ ተመርቶ ከእኛ ጋር እንዲኖር ሌላ የሚታይ አካል መረጠ፤ ይህም ምሥጢራዊ አካል ቤተ ክርስቲያን ነው (ማቴ.16፡18) በእርሷ አማካይነት ከሞት የተነሣ ክርስቶስ በእኛ መካከል ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ክርስቶሰ በቤተ ክርስቲያን በኩል የመንፈሱን ኃይል ሰጥቶ ከእኛ ጋር ይወያያል፣ ፀጋውን ይሰጠናል፡፡ ከሞት የተነሣ ክርስቶስ የእርሱ ውጫዊውን ምልክት የሆነችውን ቤተክርስቲያን ይጠብቃታል(ኤፌ.5፡22-29)፤ በእርሷ አማካይነት ክርስቶስ አማኑኤል ሆኖ ይኖራል (ማቴ.1፡23)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ድኅንታችንን እንጅ ጥፋታችንን ስለማይፈልግ ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ከእኛ አይለይም፡፡ ስለሆነም በቤተክርስቲያን አማካይነት እግዚአብሔር በሕይወታችን ዘመን ስሜትን የሚነኩ የፍቅር ምልክቶች ይሰጠናል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ሰባት ቅዱሳት ምሥጢራት መኖራቸውን ተገነዘባለች፡፡ ሰባት ቁጥር የፍጹምነት ወይም የምሉእነት ምልክት ነው፡፡ በሕይወታችን ቁልፍ ወቅቶች የሚነኩንን እነዚህን ሰባት የፍቅር ምልክቶች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለክርስቲያን ማኅበረሰብ እንደሰጠ እናምናለን፡፡

የክርስትና ሕይወት ስንጀምር #ጥምቀት$ ከሞት ከተነሣው ክርስቶስና (ዮሐ.3፡3-7) ከመላው ክርስቲያን ወገኖቻችን ጋር አንድ ያደርገናል ፡፡ በአካል እየጎለበትንና ይበልጥ የተሟላ የክርስትና ሕይወት መቀበልና መኖር ስንጀምር በታማኝነት ለጌታ እንኖር ዘንድ #በምሥጢረ ሜሮን$ የመንፈስ ቅዱስ ብርታት ያስፈልገናል (የሐዋ.19፡6፣1ጢሞ.5፡22)፡፡ ስለደኅንነታችን ጌታችን በመስቀል ላይ ያቀረበውን መሥዋዕት እንደገና የሚያስታውሰውን የሚፈጽመው ቅዱስ ማዕድ የሆነው #ቅዱስ ቊርባን$ ከእግዚአብሔር ያለንን አንድነት ያመለክታል ያስገኛልም (ሉቃ.22፡17-20፣1ቆሮ.11፡23-26)፡፡ ኃጢአት ስንሠራና ይቅርታ ሲያስፈልገን የጌታ የምሕረት ፍቅር የምንለማመደው #በንስሐ ምሥጢር$ ነው (ማቴ.4፡17)፡፡ እንዲሁም በከባድ ሕመም ወቅት #የቅብዐ ቅዱስ ምሥጢር$ የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ይቅርታ፣ ብርታትና ተስፋ ይሰጠናል (ያዕ.5፡14-15)፡፡

በመንፈሳዊ የሕይወት ጥሪያችን መሠረት ስንኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ ዲያቆናት፣ ካህናት ወይም አቡናት ሆነው ለማገልገል የተጠሩት ድጋፍ የሚያገኙት #በክህነት ምሥጢር$ ነው፡፡ እንዲሁም #ምሥጢረ ተክሊል$ እስከ ሞት ድረስ እርስ በርሳቸው በመዋደድ ቃል በገቡ ባልና ሚስት አንድነት እንደሚታየው፤ በመካሄድ ላይ ያለ የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት ነው፡፡ የእነርሱ አንድነትና ታማኝነት የጌታና የክርስቲያኖች እንዲሁም ለቤተክርስቲያኑ ያለው ታማኝነት ምልክቶች ናቸው (እምነታችን፤ገጽ.168)፡፡

እነዚህ ሰባቱ ምሥጢራት ረቂቅና የማይታይ የእግዚአብሔር ፍቅር ተንከባክበው ሕያውና ተጨባጭ ያደርጋሉ፡፡ በምሥጢራት አማካይነት ሰው የእግዚአብሔርን አባታዊ ፍቅር በሱ ላይ እንዳለ ጉልህ በማድረግ እምነቱን ያጠናክራል፡፡

ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥጢራትን በሚቀበልበት ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞትና ሞትን በማሸነፍ ያመጣልንን ፀጋዎች ይቀበላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመጣልን የድኅነት ፀጋዎች ማለት እርቅ፣ ሰላምና ፍቅር ምሥጠራትን በተቀበልን ቊጥር በእኛ ላይ ይፈሳሉ፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                 

9. ምሥጢረ ንስሐ እና እምነታችን፤

ንስሐ፡ ዋና የቃሉ ትርጉም በሙሉ ልብ የሐሳብ መለወጥና መመለስ ማለት ነው፡፡ ሐሳብ ከተለወጠ ድርግት ሁሉ ይለወጣል (ኢሳ.46፡9፣ኤር.8፡4፣ሕዝ.18፡30-31)፡፡

የመጀመሪያ ሰው አዳም በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት የሰው ልጅ ሁሉ ኃጢአተኛ እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይገልጻል (ሮሜ.3፡23)፡፡ እንዲሁም የኃጢአት ዋጋ ሞት እንደሆነ ይነግረናል (ሮሜ.6፡23)፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር የኃጢአተኛ ሞት እንደማይፈልግም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ሕዝ.18፡32a)፡፡ የእግዚአብሔር ፍላጎት ኃጢአተኛ ሰው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር ይፍልጋል (ሕዝ.18፡32b):: የእግዚአብሔር አምላክ ፍላጎትና እቅድ የሰው ልጅ ሁሉ በንስሐ ወደ እርሱ ተመልሶ የኃጢአቱን ይቅርታ አግኝቶ እንዲድን ነው፡፡ በእርግጥ ከአንድ ነገር ለመዳን አዳኝ ያስፈልጋል፤ ስለዚህ ከኃጢአት የሰውን ልጅ የሚያድነውን አዳኝ እግዚአብሔር አምላክ ወደ ምድራችን ልኮአል፡፡ «መንጋውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የእግዚአብሔርም የክብር ብርሃን በላያቸው ላይ አበራ ስለዚህም በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው «አይዞአችሁ አትፍሩ ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው»»(ሉቃ.2፡9-11) ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህ ቃል መሠረት ልዑል እግዚአብሔር ጥንት ለሰው ዘር በሙሉ የሰጠውን ተስፋ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመላክ አከበረ (ዘፍ.3፡15)፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ይህንን በጎ ነገር ሁሉ ያደረገው ዓለም በኃጢአቷ እንዳትጠፋ መሎኮታዊ ፍቅሩን ለመግለጽ ነው (ዮሐ.16፡17)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ነው፤ ሆኖም ሥጋ ለብሶ ሰው በሆነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ማንነት አሳየን፡፡ «መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም» ብሏል (ዮሐ›14፡6)፡፡ በእውነት በእርሱ በኩል ካልሆነ ባስተቀር የነፍስ ድኅነት አይገኝም፡፡ ሐዋርያው «ስለዚህ ደኅንነት ከእርሱ በቀር በሌላ በማንም የለም፤ ምክንያቱም እኛ ልንድንበት የሚገባን እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ስም ከእርሱ በቀር በመላው ዓለም ማንም የለም» ብሏል (የሐዋ.4፡12)፡፡

እንግዲህ ጌታችን መድኃኒታችን ወደ ምድራችን የመጣው እንደ እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እቅድ የሰው ልጆች እንደ እግዚአብሔር ልጆች የመጀመሪያው ሰው አዳም ከመውደቁ በፊት የነበረውን ክብርና ሙሉ ስብእና ተቀዳጅተው እንዲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ጌታችን ሲያረጋግጥልን «ሌባው የሚመጣው ለመስረቅና ለማረድ ለማጥፋትም ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው» ብሏል (ዮሐ›10፡10)፡፡

         የሰው ልጅ የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖረው ብሎም መሎኮታዊ ሕይወት ተካፋይ ይሆን ዘንድ ኃጢአቱን አምኖ በንስሐ ሕይወት መመላለስ ይኖርበታል፡፡ ንስሐ የሚያስፈልገው ለኃጢአተኛ ነው፡፡

ኃጢአት ምድር ነው?

ኃጢአት የሚለው ቃል አመጣጡ ከግእዝ ነው፡፡ መሠረታዊ ቃሉ «ኃጢእ» ይባላል፡፡ ትርጉሙም ያጣ፣ የተገፈፈ፣ የተነጠቀ ማለት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር በጥምቀት አማካይነት የተሰጠውን የልጅነት ጸጋ ያጣ፣ የተገፈፈ፣ የተነጠቀ ማለት ነው፡፡

ኃጢአት የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ አውቆ፣ ፈቅዶ በቀጥታ መቃወም ወይም ማፍረስ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተከለከለውን ፍሬ አውቆ በመብላቱ የእግዚአብሔርን ሥልጣን በቀጥታ ተቃወመ፣ ቸርነቱንም ረሳ፣ ጸጋውን ናቀ፣ ጥበቡን ነቀፈ፣ ጽድቁንም ካደ፣ የትእዛዝ ቃሉንም አቃለለ (ዘፍ.3፡1-6)፡፡ ኃጢአት ማለት በልዑል እግዚአብሔር ላይ ማመጽ፣ በቅዱስ አመራሩ ሥር አለመሆን፣ መሎኮታዊ ጥሪውንም አለማዳመጥ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የመጀመሪያውን ሰው ሲፈጥር ግብ ነበረው፣ ዓላማም ነበረው፡፡ ሆኖም ያ ዓላማ በኃጢአት ምክንያት ተበላሸ፤ ከዚህም የተነሣ ሰው ወደ አስቸጋሪና አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ገባ፡፡ ለክርስቶስ ምስጋና ይግባውና የሰው ልጅ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር አብ ቀርቦ የኃጢአቱን ይቅርታ እንዲያገኝ ተጋብዞአል፤ «ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር ብንናዘዝ እርሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ይላል» (1ዮሐ.1፡9)፡፡ እንዲሁም «ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል» ተብሏል (ምሳሌ.28፡13)፡፡

         ንስሐ መግባት ማለት የልብና የአእምሮ መለወጥ፣ አኗኗርንና አካሄድን ከእግዚአብሔር ፈቃድና ከወንጌል እውነቶች ጋር ማስማማት፣ አሮጌ ማንነትን በመቀየር አዲስና የተሻለ ሕይወት ለመጀመር ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ ነው፡፡ ያኔ በተጠመቅንበት ጊዜ በእያንዳንዳችን ልብ ወስጥ የተዘራውን መልካም ዘር እንዳያድግ ፍሬ እንዳይሰጥ አንቆ የያዘውን እሾህና አረም ነገሮችን ነቅሎ መጣል ነው፡፡ ንስሐ መግባት ማለት በጌታ ፊት እምነታችንን፣ ደካማነታችንን፣ ተሰባሪዎች መሆኖችንን አምነን ከልዑል እግዚአብሔር ብርቱ እጅ ሥር ራሳችንን ዝቅ ማድረግ፣ ማዋረድና ጸጋንና ኃይልን ወደ ሚያስታጥቀን ቸር አባት ልባችንን ከፍ ማድረግና ምህረቱንም መለመን ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲጀምር «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» (ማር.1፤15) በማለት የሰበከው የክርስትና ሕይወት ብርሃን በሰው ልጆች ውስጥ የሚጀምረው በንስሐ መሆኑን ለማስተማር ነው፡፡ ንስሐ በመግባት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ስለሚቻል ጌታችን ንስሐ ግቡ አለ፡፡ በንስሐ የሕይወት ምርጫችንና ዋስትናችን ወደ ሆነው አምላክ መመለስ ያስፈልገናል፡፡ ከራስ ወዳድነት፣ ከክፉ መሻቶችና በውስጣችን ጠንካራ ሥር ከሰደደው ከኃጢአት ሥራዎች ጋር በርትተን መታገል፣ ጠንካራ ጦርነትን ማካሄድ ይኖርብናል፡፡ ኃጢአትን ብንሸፍንና ብናባብል፤ መልካም እንደሆነ አድርገን ለሕሊናችን ብናቀርብ በእግዚአብሔር ዘንድ የኃጢአትነትን ይዘት በፍጹም አይለቅም፡፡ የሸራሪት ትልቅ ትንሽ የለም ሁሉም ድር መሥራት ይችላል፡፡ እባብም ቢሆን እንደዚው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል «ኃጢአት አልሠራንም ብንል እግዚአብሔርን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም» ይላል (1ዮሐ.1፡8-10)፡፡ እንዲሁም «ኃጢአትህን ለመደበቅ ብትሞክር በኑሮህ ሁሉ ነገር አይቃናልህም፤ ኃጢአትህን ተናዝዘህ ዳግመኛ ኃጢአት ከመሥራት ብትቆጠብ ግን የእግዚአብሔር ምህረት ታገኛለህ» ብሏል (ምሳሌ.28፡13)፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ኃጢአትን ይቅር ለማለትና ከኃጢአት የተነሣ በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ የሻከሩ ግንኙነቶችን ለመጠገን ነው፡፡ እርሱም ደቀመዛሙርቱን በስሙ ኃጢአትን ይቅር እንዲሉ ባዘዛቸው ጊዜ የማዳንና የማስታረቅ አገልግሎቱን እንድትቀጥል ለቤተክርስቲያኑ ሥልጣን ሰጣት፡፡ «መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፣ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል» (ዮሐ›20፡23)፡፡ ዛሬ ምሥጢረ ንስሐን ለመቀበል ከሁሉ የተሻለው ዝግጅት በኢየሱስ ክርስቶስና በቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር በጸሎት መንፈስ ህሊናን መመርመር ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ረድኤት እየታገዙ በታማኝነት ህሊናን መመርመር በሕይወታችን ውስጥ የኃጢአታችንን ምክንያት ያደረግነውን ማናቸውንም ጉዳት እንድንክስ ይቀሰቅሰናል፡፡

ቤተክርስቲያናችን እምነት ጉዞ ንስሐ ጥልቅ ታሪክ አለው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት ምሥጢረ ንስሐ ይሰጥ የነበረው በዕድሜ ውስጥ በጣም ውስን ጊዜ ብቻ ነበር፤ ይኸውም በጣም ከባድ ኃጢአቶች ብቻ ነበር፡፡ ኃጢአተኛውን ከእግዚአብሔርና ከክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ የመገለሉ ከባድነት እንዲሰማው ለማድረግ የረዥም ጊዜ ንስሐ መግባትን ያካትት ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ፣ ይህን ምሥጢር የመቀበል ሌላኛ መንገድ ማለትም በካህን ፊት የተደጋገመ፣ ግላዊና ታማኝ ኑዛዜ የማድረግ ሁኔታ ስለታመነበት ተወሰነ፡፡ ይህም የንስሐ ዘዴ ካህኑ ኃጢአተኛውን ሁነኛ የንስሐና የፍቅር ምልክት የሆነውን የንስሐ ቅጣት እንዲመርጥ ይረዳዋል፡፡ ካህኑ እንደ ጌታ ወኪል ሆኖ ያገለግላል፣ በቤተክርስቲያን ስም ቃለ ፊታት ይሰጣል፡፡ ካህኑ እጆቹን በኃጢአተኛው ራስ ላይ አድርጎ «በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ከኃጢአትዎ እፈታዎታለሁ» የሚሉ ቃላት ሲደግም፣ ሰው እንደመሆናችን ኃጢአታችን እንደቀረልን የምናውቅበትን ምልክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ይሰጠናል፤ (እምነታችን፤ገጽ.213-215) ራሱም ለደቀ መዛሙርቱ «በእውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም በሰማይ የተፈታ ይሆናል» (ማቴ.18፡18) ብሎ ሥልጣን የሰጠቸው ስለሆነ ዛሬም የእርሱ አገልግሎት ቃል ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ አገልግሎት በለየቻቸው ካህናት ዘንድ ይፈጸማል፡፡

 

30 October 2020, 14:40