ፈልግ

ማርያም በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ወጣች ማርያም በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ወጣች 

ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ የወጣች

በአገራችን በኢትዮጲያ በሚገኙ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ ዛሬ ነሐሴ 16/2012 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ያረገችበት ዓመታዊ በዓል በታላቅ መንፈሳዊነት በመከበር ላይ ይገኛል። እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣቱዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስለ ድንግል ማርያም ከደነገገቻቸው የእምነት እውነቶች አራተኛው ነው፡፡ ይህንንም የእምነት እውነት እ.አ.አ. በኅዳር 1 ቀን 1950 ዓ.ም. “Munificentissimus Deus” እግዚአብሔር እጅግ ለጋሽ በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው አማካይነት በይፋ የደነገጉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) ነበሩ፡፡ ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሰጠችው እሽታ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ማኅፀንዋ እንዲወርድ ያደረገችው በከበረው ሰውነት የሰማይና የምድር ንግሥት መሆን ምንኛ የተገባ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገትና በፍልሰታ ማርያም መካከል መሠረታዊ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅና ከሙታን የተነሣ ጌታ በመሆኑ ወደ ሰማይ ያረገው በአምላካዊ ኃይሉ ነው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከሙታን የተነሣችውና በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ የተወሰደችው በአምላክ ኃይልና ጸጋ ነው፡፡ ፍልሰታ ማርያም የእምነት እውነት እንዲሆን በደነገጉበት እግዚአብሔር እጅግ ለጋሽ በተባለው ሐዋርያዊ መልእክታቸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው እንዲህ ይላሉ፣ “እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች የአምላክ እናት፣ ዘለዓለማዊ ድንግል፣ የምድራዊ ሕይወትዋን ጉዞ ከጨረሰች በኋላ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማያዊ ክብር ተወስዳለች፡፡” ይህ ድንጋጌና እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አዳም ኃጢአት የተፀነሰች ስለ መሆንዋ የተደረገው ድንጋጌ የሚያመለክቱት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ አስተዳደር ስላለው ዓለም አቀፋዊ እውነተኛና ጠንካራ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከቶሊካውያን ምእመናንም በየዘመኑ ስለ ጉዳዩ የነበራቸውን ጠንካራ እምነት ጭምር ነው፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት ለብዙ ዘመናት በቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ከእምነት ጋር በተያያዘ ትምህርት ሲጠቀስ መቆየቱም የሚታወስ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በነገረ-መለኮት ትምህርት መግለጫ፣ በሥርዓተ-አምልኮ ሥነ ሥርዓትና በካቶሊካውያን ምእመናን አንደበትም ጉዳዩ ሲጠቀስ እንደ ቆየ ይታወሳል፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የእምነት እውነት ስለ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የተገለጸ ስለሆነ ጥያቄ በማያስከትል ሁኔታ በመለኮታዊ መገለጽ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ማለት የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ዋና ዓላማ ከእግዚአብሔር ጋር በፍጹም አንድነት በመኖር መንፈሳዊ ተልእኮዋን መፈጸም እንደ ነበረም የሚያመለክት ነው፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የአምላክ እናት የመሆንዋ ውጤት እንደ ሆነም ማሰብ ይቻላል፡፡ በምድር ላይ ከልጅዋ ጋር በፍጹም አንድነት ስለ ኖረች፣ ለእርሱም ብቻ ስለ ነበረችና እውነተኛ ተከታዩም ስለ ነበረች፣ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይም ከልጁዋ ጋር መሆን፣ ለእርሱም ብቻ መሆንና የእርሱም እውነተኛ ተከታይ መሆን ይገባታል፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ የልጁዋ እጅግ ለጋስ ተባባሪ እንደ ነበረችም የሚታወስ ነው፡፡ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣቱዋ በምድር ላይ ከልጁዋ ጋር የነበራት እጅግ ለጋስ ትብብር በሰማይም እየቀጠለ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ በዚህ ዐይነት እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጁዋ ጋር በምድርም ሆነ በሰማይ የማይፈርስ አንድነት አንዳላት ግልጽ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይም በሰው ደኅንነት ታሪክ ያላትን ሚና በትጋት በመፈጸም ላይ እንደምትገኝ በማስመልከት የአሕዛብ ብርሃን የተባለው የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሰነድ እንደሚከተለው ያትታል፣ “ወደ ሰማይ ከወጣች በኋላ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በሰው ደኅንነት ታሪክ ያላትን ተልእኮ አላቋረጠችም፡፡ በእናትነት ፍቅርም የልጁዋን ወንድሞችና አህቶች ትንከባከባለች፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በአደጋዎችና በሕይወት ችግሮች ውስጥ በማለፍ ወደ ዘለዓለማዊ ቤታቸው እስኪደርሱ ድረስ የዓለም ላይ ኑሮአቸውን እየቀጠሉ ናቸውና” (የአሕዛብ ብርሃን ምዕራፍ 8 ቁ. 62 ተመልከት)፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ፣ “እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርቲያን ከሞት በኋላ ለምትኖረው ሕይወት ልዩ ምልክት ናት” ይላል (አዲሱን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትምህርተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቁ. 972 ተመልከት)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ መውጣት የእምነት እውነት መሆኑን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው የደነገጉበት ሰነድ ሁኔታው እንዴት እንደ ተከሠተ በግልጽ አይዘረዝርም፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ ነበር? ወደ ሰማይ የተወሰደችው በቅድሚያ ነፍሱዋና ሥጋዋ ሳይለያዩ ነበር? እነዚህ ጥያቄዎች ለውይይት ክፍት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በአምላክ ኃይል ወደ ሰማይ የተወሰደችው ልክ እንደ ልጁዋ ከሞተች በኋላ ነበር የሚል ሐሳብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በነፍስና በሥጋ ተከብራ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም አሁን ያለችው በክርስቶስ የምናምነው ሁላችንም ከሙታን ትንሣኤ በኋላ ለመሆን ተስፋ በምናደርገው ዐይነት ነው፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

18 August 2020, 08:32