በፍትሕና በፍቅር የታረቀ ህብረተሰብ
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ተፈጥሮአዊ ባሕሪይ
ክፍል 22
የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ዓላማ በመሠረቱ ከሕልውናው ጋር ተመሳሳይ ነው። እርሱም ለደኅንነት የተጠራውን እና በክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ጥበቃና ኃላፊነት በአደራ የተሰጠው ሰው ነው (John Paul II, Encyclical Letter Centesimus Annus, 53: AAS 83 (1991), 859) ። ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ አስተምህሮዏ አማካኝነት በኅብረተሰብ ውስጥ ለሰው ልጅ ሕይወት ትሳሳለች። የማኅበራዊ ኑሮ ጥራት ማለትም ኅብረተሰብን የሚያስተሳስሩ የፍትህ እና የፍቅር ግንኙነቶች ዓይነት የሚወሰነው የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ሕልውና የቆመበትን ሰብአዊ ፍጡር በመጠበቅና ባማሳደግ ላይ ነው። በመሠረቱ በኅብረተሰብ ውስጥ ዋናዎቹ ነገሮች ሰብአዊ ክብርና ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም በሰዎች መካከልና በማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ሰላማዊ ግንኙነቶ ናቸው። በማኅበረሰብ ውስጥ ዋስትና መሰጠት ያለበት ለነዚህ ሃብቶች ነው። ከዚህ አንጻር የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የመስበክ ብቻ ሳይሆን የመተቸትም ሥራ ያጠቃልላል።
በመጀመሪያ ደረጃ ቤተክርስቲያን ስለ ሰውና ስለ ሰው ጉዳዮች በጠቅላላ የራስዋ የሆነውን ነገር መስበክ ተቀዳሚ ተግባሯ ነው (Paul VI, Encyclical Letter Populorum Progressio, 13: AAS 59 (1967), 264) ። ይህም የሚሆነው በመርህ ደርጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ነው። በመሠረቱ የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ትርጉምን እና ስሌትን ማመዛዘን ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ የሚመነጩትን መለኪያዎችና የደርጊት መርሆዎች ጭምር ይሰጣል። ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ ትምህርቷ አማካኝነት ለማድረግ የምትጥረው ህብረተስብን ለማዋቀር ወይም ለማደራጀት ሳይሆን ህብረተሰብን ለመሳብ፣ ለመምራትና ሕሊናን ለማነጽ ነው።
ይህ ማኅበራዊ አስተምህሮ በልዩ ልዩ ትምህርት በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚዘዋወረውና በእርሱም ውስጥ የሰረጸውን የበደልና የሁከት ኃጢኣት የመንቀፍ ተግባርን ያካትታል (Second Vatican Ecumenical Council, Pastoral Constitution Gaudium et Spes, 25: AAS 58 (1966), 1045-1046) ። የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሚያቀርበው ትችት ያልታወቁና የተጣሱ ሰብአዊ መብቶችን በተለይም የድሆችን፣ የአነስተኞችንና የአቅመ ደካሞችን መብቶች ይንከባከባል ይጠብቃልም። እነዚህ መብቶች ችላ በተባሉ ወይም በተረገጡ ቁጥር ሁከትና በደል እየጨመረ ይሄዳል መላው ሕዝብ እና ቀሪ የዓላም ክፍሎችን በማካተት ለማኅበራዊ ጥያቄዎች ማለትም ወደ ማኅበራዊ ብጥብጥ ያሚወስዱ ጉዳዮች በማጥናት መፍትዔ ያፈላልጋል። አብዛኛው የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን ለእነዚህም ጥያቄዎች ምላሹ ማኅበራዊ ፍትህ ነው።
የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ዋና ዓላማ ሃይማኖታዊና ግብረገባዊ ነው ( John Paul II, Encyclical Letter Centesimus Annus, 53: AAS 83 (1991), 859)። ሃይማኖታዊ የተባለበት ምክንያት የቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና የደኅነነት ተልዕኮ ሰውን ከነሙሉ እውነተኛ ሕልውናው ግላዊ ሰውነቱ ማኅበረሰባዊነቱና ማኅበራዊ ፍጡርነቱን ስለሚያጠቃልል ነው። ግብረገባዊ የተባለበት ምክንያት ቤተክርስቲያን በሙሉ ሰበዊነት ማለትም ሰው ከማንኛውም ጭቆና ነፃ ማውጥትን እና የተቀናጄ ሰብዓዊ ዕድገት ላይ ስለምታተኩር ነው። የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በታረቀና በፍቅር ስምምነት የፈረጠመ ህብረተሰብ በመመስረት በታሪክ በዝግጅትና በምሳሌ ጽድቅ የሚነግስበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር (2ኛ ጴጥ. 3፣13) የሚጠብቅ ህብረተሰብ መከተል የሚገባውን መንገድ ይመለክታል።
አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን