ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም. የፍልሰታ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም. የፍልሰታ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም. የፍልሰታ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2012 ዓ.ም. የፍልሰታ ጾም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን እና የቅድስት ድንግል ማርያምን በነፍስ እና በስጋ በክብር ወደሰማይ መውጣት በማሰብ የሚቀጥሉትን ሁለት ሳምንታት በጾም እና በምህለላ ለሚያሳልፉ ወገኖቻችን በሙሉ  እንኳን ለ2012 ዓ.ም. ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ የፍልሰታ ጾም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር የተገለጠ መለኮታዊ የሃይማኖት አንቀጽ እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ በቅድስት መንበር ከተደነገጉ ቀኖናዊ እምነቶች ሁሉ ከፍ ብለው ከሚቆጠሩት አንዱ እና ዋነኛው ነው።

የፍልሰታ ምስጢር ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋን የተሞላች፣ ያለአዳም ኃጢአት የተፈጠረች፣ ምድራዊ ሕይወቷንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እና ህማማት ጋር እጅጉን በተቆራኘ መልኩ ያሳለፈች በመሆኗ እና እግዚአብሔር በሁሉ ቻይነቱ ስጋዋ ምድራዊ መበስበስን እንዳያይ በመፍቀዱ ያገኘችው ልዩ ጸጋ ነው። በመሆኑም በተለይ በኢትዮጵያ የመትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጾመ ፍልሰታን በየዓመቱ በፍጹም ትህትና፣ ንስሃ፣ ጸሎት እና ምህለላ ታሳልፋለች።

ኢትዮጵያውያን ዘንድሮ በተደራራቢ ችግር እና አስጨናቂ ሁኔታዎች ውስጥ እንገኛለን። ቅድስት ድንግል ማርያምም ምድራዊ ሕይወቷን በስደት፣ በመከራ፣ በድህነት እና እንግልት አሳልፋለች። ልጇን የምትወልድበት ቦታ ይሞቀውም ዘንድም የምትጠቀልልበት እራፊ እንኳን አላገኘችም ነበር። ከኢየሱስ ጋር ተሰድዳለች፣ በቀራንዮም የህማማቱ ሁሉ ምስክር በመሆን ቅዱስ ስምዖን አንደተነበየው ልቧን ሰይፍ ሰንጥቆ እስከሚያልፍ ድረስ በሃዘን ሰይፍ ተወጋች። እኛ አሁን ያለንበትን የጭንቀት እና ስጋት ሁኔታ ቅድስት ድንግል ማርያም በምድራዊ ሕይወቷ ያለፈችበት፣ የኖረችበትም ነውና ትገነዘበዋች፣ አስከፊነቱንም ትረዳዋለች፣ ታዝንልንማለች።

በመሆኑም መላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ በሙሉ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት ከነሐሴ 1 እስከ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመከላከል በመንግስት እና በቤተክርስቲያን የተላለፉላችሁን የጥንቃቄ መመሪያዎች እያከበራችሁ በያላችሁበት ሰለ ሀገር ሰላም፣ ሰለሕዝቦች አንድነት እና ሰለ ኮቪድ ወረርሺኝ መወገድ ልዩ ጸሎት በማድረግ፣ በጾም እና በምህልላ የቅድስት ንጽህት ማርያምን አማላጅነት እንድትለምኑ ዐደራ ጭምር አሳስባችኋለሁ።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታዛዥነት እና የትህትና አስተማሪያችን ናት፡፡ በእርሷ የፍቅር ሥራና የትሕትና ሕይወት ልንማረክ ይገባናል፡፡ "ኃይለኞችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰድዷቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል" (ሉቃ.1፡12) በማለት ለእግዚአብሔር ምሥጋና ማቅረቧ ዛሬ በሀገራችን ብሎም በዓለማችን ለሚታዩ ችግሮች እግዚአብሔር ድሆችን የወገነ መልስ እንደሚሰጥ በደለኞችንም ሳይቀጣ እንደማይተው ያሰተማረችበት ነው።

እናስተውል ያለአግባብ ሀብት ሰብስበን ብንበለጽግ፣ በኃይል በዙፋን ለመቀመጥ ስንል ብጥብጥ እና ቀውስን ብናነግስ ከዙፋን የሚያዋርድ፣ ሀብትንም አምክኖ ባዶ የሚያድርግ እግዚአብሔር ለድሆች ይደርሳል። ትሁታንንም ከፍ  ከፍ ያደርጋል። ሕዝብን፣ ድሆችን ማስቀደም አስፈላጊ እና ሰብዓዊም ጭምር ነው፡፡ በሀገራችን ፖለቲካ ተሳትፎ ለማደረግ የምትፈልጉ ተፎካካሪዎችም የበለጸገች እና የተረጋጋች ሀገርን መምራት እንድትችሉ  መጀመሪያ የድሆችን ልብ አሸንፉ፣ አስቀድማችሁ በሕዝብ ልብ ለመንገስ ጥረት አድርጉ እንጂ ኃይልን፣ ሁከትን፣ በደልን መሳሪያ አታድርጉ። ሁከት የሕዝብን በተለይ የድሆችን እና ዐቅመ ደካሞችን ሕይወት የሚያቃውስ ተግባር በመሆኑ እግዚአብሔርን እጅግ ያሳዝነዋል። የሕዝብንም ይሁንታ አያስገኝም። በሁከት የሚያብሩ ሁሉ በሁከት ያነገሱትን በሌላ ሁከት ያዋርዱታል አንጂ  ለማንም አይበጁም።

በዚህ አጋጣሚ ካቶሊካውያን በሙሉ በያላችሁበት ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም፣ በመከባበር እና ብሎም እርስ በእርስ ከልብ በመዋደድ የጾምና የጸሎትን መንፈስ ተላብሳችሁ የሃይማኖት፣ የዘር፣ ወይም የጾታ ልዩነቶችን ሳታደርጉ በፍጹም ትህትና ድሆችን በማገልገል እንድትኖሩ አሳስባለሁ፡፡

እግዚአብሔር ክረምቱን ባርኮ ዝናቡን በሚያስፈልግበት ቦታ እና መጠን እንዲሰጠን አንጸልይ። የገጠመንን የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በመከላከል እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የጀመርነውን ተሳትፎ በማጠናከር ለመጪው ትውልድ ስነምህዳሯ የዳበረ፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ተግባራችንን አንድንቀጥል ዐደራ አላለሁ።

ባለፈው ሰኔ መጨረሻ በተከሰተው አሰቃቂ ደም መፋሰስ የሞቱትን የወገኖቻችንን ነፍሳት በመንግስቱ ያሳርፍልን፤ ያዘኑትን ያጽናናልን፣ የወደመውም ንብረት በሁላችን ድጋፍ ተመልሶ ይቋቋም፣ ዘረኛነትንና ጥላቻን በኢትዮጵያዊ ወንድማማችንትና አህትማማችነት ወደ ይቅርታና ወደ ኖርንበት ፍቅርና አብሮነት እንመልሰው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን በአንድነት፣ በመከባበርና በመረዳዳት ጸንተን ሰንኖር ነው፡፡

ቸሩ እግዚአብሔር የዘንድሮውን የፍልሰታ ጾም ወራት በልዩ ጸሎት፣ በጾምና በተጋድሎ በማሳለፍ ለበዓለ ፍልሰታዋ በሰላም እንድንደርስ ያብቃን፡፡ ለመላው ካቶሊካውያን ምእምናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ አምላክ የተቀደስ የተባረከ ጾመ ፍልሰታ  ያድርግልን።

ቸሩ አምላካችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ኢትዮጵያን ይባርካት፡፡

 

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

  ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

  የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

 

 ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም.

 አዲስ አበባ

06 August 2020, 10:57