ፈልግ

 ብፅዕ  ካርዲንል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብፅዕ ካርዲንል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን 

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም የፍልሰታ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

የተከበራችሁ ምእመናን

እንኳን ለ2012 ዓ/ም ለፍልሰታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ዛሬ የትንሣኤን ፍሬ የምናከብርበት የተለየ ዕለት ነው። የትንሣኤ ፍሬ በሰው አንደበት ተገልጾ የማያልቅ ምሥጢር ነው። ሞት በሕይወት፣ ጨለማ በብርሃን፣ ክፋት በፍቅር የተወገደበት ምሥጢር ነው። የትንሣኤ ፍሬ የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋና የምሥራች ነው። የእመቤታችን ማርያም ፍልሰትም የዚሁ ፍሬ ክፍል ነው። እግዚአብሔር ቅድስት ድንግል ማርያምን ስላከበራትና ስላነገሣት ከወዲሁ በዚህ ድንቅ ሥራ የምንደነቅበትና የምንደሰትበት ወቅት ነው። የጽድቅ ፀሐይ በሆነው ክርስቶስ የምታበራውን የሰማይ ንግሥት እየተመለከትና ከመላእክት፣ ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጋር ሐሤትን የምናደርግበት ጊዜ ነው።  

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በምዕራፍ ስምንት ላይ ልብ ልነለው የሚገባ ቁም ነገር ይነግረናል፣

“ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።”

እነኚህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት እነሆ ተፈጸሙ። እግዚአብሔር ማርያምን ለልዮ ጸጋ እንደጠራት እናውቃለን። እንዳጸደቃትም እናስተውላለን፤ እንዳከበራትም እናምናለን።

ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ብቻ አይቆምም። እንዲህም ይላል፣

“ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? … ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኀይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ. 8፡29-39)                                                                                                                                           

የክርስቶስን ያህል ማርያምን የወደደ ማን ሊኖር ይችላል? ማንም አይኖርም። እንግዲያውስ በዚህ በዓላችን በክርስቶስ አማካይነት የሰማይዋን ንግሥት ቅድስት ድንግል ማርያምን እናፈቅራለን። ከፍጥረታት መሃልስ እንደማርያም ክርስቶስን ያፈቀረ ማን ሊኖር ይችላል? ማንም ሊኖር አይችልም። ታድያ ማን ወይንም ምን ጉዳይ ክርስቶስን ከማርያም፣ ማርያምን ከክርስቶስ ሊለይ ይችላል? ሞትም ቢሆን ስለማይለያቸው ነው የፍልሰታን በዓል የምናከብረው!

ገና ድሮ፣ ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ ዓመት በፊት ነቢዩ ዳዊት ስለ መሢሕ እና ስለ እመቤታችን ተንብዮ ነበር። በመዝሙር አርባ አራት ወይም አርባ አምስት ላይ ነቢዩ “ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፣ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብዕር ነው” እያለ ለጸሎትና ለውዳሴ ያዘጋጀናል። “ኃያል ሆይ፥ በቍንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ” እያለ ስለ ክርስቶስ ድል አድራጊነት ያበሥረናል። ከዚያም “ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፣” በማለት ክርስቶስ የጽድቅ ንጉሥ መሆኑን ያስተምረናል። የክርስቶስ ዙፋን ዘላለማዊ መሆኑንም ያውጃል። ምክንያቱም ዳግመኛ ላይሞት ሞትን ድል አድርጓልና። በሲኦል የታሠሩትን ነጻ ጻድቃን ነጻ አውጥቶአልና። የሲኦልን መክፈቻ ይዞ ከወረደ በኋላ ምርኮን ይዞ ወደ ሰማይ አርጓልና። ውርደትን በክብርና በውበት ተክቷልና።

“እነኚህ ከክርስቶስ ጋር ወደ ተከፈተው ሰማይ የገቡትና እዚያም ያሉት እልፍ አእላፋት መላእክት አምልኮን፣ ስግደትን ለታረደው በግ፣ ለይሁዳ አንበሳ ያቀርባሉ። የኃይል ሁሉ ሙላትን ተጎናጽፎ ለተቀመጠው ውዳሴን እና ዜማን ያቀርባሉ። ታዲያ በዚሁ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት ሌላ የሚያበሥረን ነገር አለ፤ “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤” የሚል ትንቢት ይነግረናል።” (ዮሐ.5፡5-6)

የፍቅር ምድጃ ወደሆነው ክርስቶስ እየቀረብን፣ ምድጃውን በማሕፀኗ የተሸከመችውን እናት መራቅ እንዴት ይቻላል? ወደ ክርስቶስ ስንቀርብ ወደ ማርያምም እንቀርባለን። አንድ ላይ ናቸውና። እንዲሁም “ይችውልህ እናትህ፣ ይችውልሽ የአንቺ እናት” (ዮሐ.19፡27) ብሎ እናት ይሰጠናልና። በታላቅ ትሕትና እንድንቀበላት ይጋብዘናልና። ያኔ የክርስቶስ የሕይወት ቃል ወደ ልባችን ይሰርጻል። ያኔ ቃሉ በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር ይሞላናል። የማይታየውን ያሳየናል። አርቀን እንድናይ ያደርገናል። ከሰው ልጅ ሁሉ ጋር ያለንን ዝምድና ያስታውሰናል። ከፍጥረታት ጋር ያለንን ትስስር ይገልጽልናል።

በፍልሰታ በዓል፣ በሙታን ትንሣኤ እንደምናምን እናረጋግጣለን። እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያርፉት ሁሉ የሚሰጠውን በረከት አስቀድሞ ለቅድስት ድንግል ማርያም ማበርከቱን እናበሥራለን። በዓሉ የሚደምቀው የሰማይዋ ንግሥት ፈቃድ ሲፈጸም ነው። ፈቃዷንም በማያዳግም ሁኔታ ለሰው ልጆች ሰጥታለች። ፈቃዷ በሦስት ቃላት ይጠቃለላል፤ እነኚህም ቃላት፣ “እሱ የሚላችሁን ስሙት” (ዮሐ.2፡5) የሚሉት ናቸው። የሰማይዋ ንግሥት ፍላጎትና ደስታ ክርስቶስ የሚለንን እንድንፈጽም ነው። በመንፈስ ድሆች እንድንሆን ነው። የሰላም መሳርያዎች እንድንሆን ነው። በኛ ላይ እንዲደረግልን የምንፈልግውን ለሌሎች እንድናደርግ ነው።

አፍቃሪና አዛኝ እመቤታችን የመጣብንን የቫይረስ ወረርሽኝ እንዲያስወግድልንና የታመሙትን እንዲፈውስልን ልጇን ትለምንልን! እንዲሁም ከትዕቢት፣ ከምቀኝነት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከመከፋፈልና ከጥላቻ ወረርሽኝ ልጇ ያድነን ዘንድ ታማልደን !

መልካም የፍልሰታ በዓል

+   ካርዲንል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

16 ነሐሴ 2012 ዓ/ም

አዲስ አበባ

22 August 2020, 16:16