ፈልግ

የነሐሴ 10/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 7ኛ ቅ. ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 10/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 7ኛ ቅ. ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የነሐሴ 10/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 7ኛ ቅ. ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 6፡11-23

2.     ያዕ 4፡1-17

3.     የሐዋ 7፡44-50

4.     ዮሐ 7፡32-52

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጒምጒምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ ጋር የምቈየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም።” አይሁድም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ይህ ሰው፣ ልናገኘው የማንችለው ወዴት ለመሄድ ቢያስብ ነው? በግሪኮች መካከል ተበታትነው ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ግሪኮችን ሊያስተምር ፈልጎ ይሆን? ‘ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፤’ ደግሞም፣ ‘እኔ ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም’ ሲል ምን ማለቱ ይሆን?”

የበዓሉ መጨረሻ በሆነው በታላቁ ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፤ በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።” ይህን ያለው በእርሱ የሚያምኑ ስለሚቀበሉት መንፈስ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ አልተሰጠም ነበር።

ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ቃሉን ሰምተው፣ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢዩ ነው” አሉ። ሌሎችም፣ “እርሱ ክርስቶስ ነው” አሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፤ “ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ሊመጣ ይችላል? መጽሐፍ፣ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ ዳዊትም ከኖረበት ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ይናገር የለምን?” ስለዚህም በኢየሱስ ምክንያት በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ አንዳንዶቹም ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ማንም እጁን አላሳረፈበትም።

የአይሁድ መሪዎች አለማመን

በመጨረሻም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎቹ፣ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው ሄዱ፤ እነርሱም ጠባቂዎቹን፣ “ለምን አላመጣችሁትም?” አሏቸው። ጠባቂዎቹም፣ “እንደዚህ ሰው፣ ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም” ሲሉ መለሱ። ፈሪሳውያንም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተም ተታላችኋል ማለት ነው? ለመሆኑ ከባለሥልጣኖችና ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለ? ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው።”

ከዚህ ቀደም ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረውና ከእነርሱ አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፤ “ሕጋችን፣ አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን?” እነርሱም፣ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሣ መርምር፤ ትደርስበታለህ” ብለው መለሱለት። ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደ የቤታቸው ሄዱ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንቶ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ። እንደ ቤተክርስቲያናችን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር እና ደንብ መሰረት የዛሬው ሰንበት ሰንበት ዘክረም 7ኛ በመባል ይጠራል። የሰላም አምላክ የሆነው እግዚኣብሔር ጠብቆን ደግፎን ተንከባክቦን እንደ መልካም ሥራችን ሳይሆን በጸጋው እና በምሕረቱ ጠብቆን ለዛሬ እለት ያደረሰን እግዚኣብሔር አባታችን ቅዱስ ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ማርያም የጾም ወቅት ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እናወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን የምንማጸንበት ወቅት ላይ መሆናችን የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ ወቅት ለየት ባለ ሁኔታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ዘንድ ጸጋ እና በረከት ታስገኝልን ዘንድ አማልጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

ቤተክርስቲያናችን  በእየእለቱ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ድጋፍ ይሆን ዘንድ በማሰብ ከወቅቱ ጋር ተስማሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትን ለምዕመናኖቿ በማቅረብ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በእግዚባሔር ቃል ላይ መሰረቱን ባደረገ መልኩ ይኖሩ ዘንድ ታስተምራለች። በእዚህም መሰረት ለዛሬው ሰንበት ለአስተንትኖ እንዲሆነን በቀዳሚነት የተመረጠው የእግዚኣብሔር ቃል የተወሰደው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሲሆን “እንደዚሁም ለኀጢአት እንደ ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁን ቊጠሩ። ስለዚህ ክፉ መሻቱን ትፈጽሙ ዘንድ በሟች ሥጋችሁ ላይ ኀጢአት እንዲነግሥበት አታድርጉ። ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ፣ ኀጢአት አይገዛችሁምና” (ሮሜ 6፡11-23) በማለት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለምዕመናኑ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል። በእዚህ መልእክቱ ቅዱስ ሐውርያው ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን አሁን ያለበት ደረጃ እና ሁኔታ ይኸውም ለኅጢአት ሲል መሞቱ በክርስቶስ ሕያው እንዲሆን እንደ ሚያደርገው እና ለእግዚኣብሔር መኖር እንደ ሚገባው በተግባር እንዲገለጥ ጥሪ የሚያደርግ ክፍል ነው። ኅጢአትን ድል ለማደረግ ክርስቲያን መውሰድ ያለበት ሁለተኛው እርምጃ ኅጢያት በሕይወቱ እንዳይነግስ መከላከል እንደ ሆነ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ሁሉ ያሳስባል። ኅጢአትን ከሕይወታችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማስወገ እና በእግዚኣብሔር ጸጋ ተሞልተን ለመኖር የሚያስችለን ሦስተኛው እርምጃ ደግሞ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ እንደ ሚመክረን ኅጢአት በሕይወታችን ውስጥ እንዳይንግሥ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእግዚኣብሔር አሳልፎ መስጠት እንደ ሆነ ሐዋርያው ያሳስበነናል።

ራሳችሁን ለእግዚኣብሔር መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ በማለት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሁሉም ክርስቲያኖች ዛሬ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ማነኛውም ተግባራችን እና ሐሳባችን ሳይቀር እግዚኣብሔርን እና ባልንጀሮቻችንን ለማገልግል ይውል ዘንድ ይመክረናል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ” ማለቱ ደግሚ ሁሉም የአካል ክፍሎቻችን የሚያመልክት ሲሆን በተቻለን መጠን መላውን የአካል ክፍሎቻችንን ሰውን ለመበደል እና ለመጨቆን ሳይሆን በተገቢው ሁኔታ በመኖር ለእግዚኣብሔር እና ለባልንጀሮቻችን መልካም የሚባሉ ተግባራትን በማከናውን መኖር እንደ ሚገባን ያሳስበናል። “ኅጢአት አይገዛችሁ” በማለት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ኃጢአትን ልክ እንደ አንድ ሰው አድርጎ በመቁጠር ኃጢአት ባሪያ አድርጎ እንዳይገዛን መጠንቀቅ እንደ ሚገባን ያሳሰበን ሲሆን ኃጢአት የሰውን ልጅ እንደ ባሪያ አድርጎ የመግዛት ኃይል እንዳለው በመጠቆም ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ተጠብቀን ራሳችንን ለእግዚኣብሔር በማስገዛት መኖር እንደ ሚገባን ያሳስበናል። በአጠቃላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ የሚያስተላልፍን መልእክት በስነ-ምግባር የተሞላ ሕይወት መኖር እንደ ሚገባን፣ ሕግ በኅጢአተኛው ላይ ለመፍረድ የሚያስችል መሳሪያ እንጂ በራሱ የኅጢያትን ኃይል ለመቋቋም የማያስችል በመሆኑ የተነሳ ይልቁኑ የኃጢአትን ኃይል መቋቋም የሚችለው የእግዚኣብሔር ጸጋ ብቻ በመሆኑ ይህንን በኃጢአት ላይ ድል መጎናጸፍ የሚያስችለንን የእግዚኣብሔርን ጸጋ አጥብቀን መፈለግ እንደ ሚገባን ያስተምረናል። ክርስቲያኖች በሙሉ ልባቸው ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ ሚኖርባቸው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ የገለጸ ሲሆን አንድ ክርስቲያን ለእግዚኣብሔር መታዘዝ የሚገባው በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ እንጂ በግዳጅ መሆን እንደ ሌለበት ያሳስበናል።

ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ወንጌሉ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደኔ ይመጣና ይጠጣ ይለናል” በእርግጥ ጌታችን መድኃኒታችን ይህንን የሚለን በአይሁዳውያን እጅ ከመግባቱ በፊትና መንፈስም ወደሱ ሳይወርድ መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ጌታችን ይህንን የሚጋብዘን ከአነጋገሩም የምንረዳው “ማንም የተጠማ” ብሎ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አማኝ የሆነ ወይም ያልሆነ፤ ፈርሳዊያን ወይም ሳምራዊያን ወየም ሰዶቃውያን እንዲሁም ሌሎቹን ለይቶ አልተጣራም ሁሉንም በተለይ የተሙትን ይጋብዛል፡፡ ታዲያ ሰዎች ብዙ ጊዜ ውሃ ጥም ግዜ አይሰጥምና የተጠማነውን ለመርካት እንሞክራለን፡፡ ጌታችን ግን ይህንን የሚምን ከዚህም በላይ የሕይወት ውሃ ወንዝ ከሆዱ እንደሚፈልቅ ይነግረናል፡፡

ዛሬ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ አካል የሆነችውን ሐዋርያዊ የሆነችው ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ልዑክ በመሆን በዚህ ምድር ላይ የሰራውን ሙሉ ስራውን ተረክባ ምዕመናኖችዋን የክርስቶስ አካል ለማድረግ አላፊነቱን ተቀብላ እየሰራች ትገኛለች ምክንያቱም ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሚስጥራዊ አካል ነች፡፡  ወደ ምስጢራት እየመራች ምስጢራትን እያካፈለች በሚስጥራቷ እየፈወሰችና እየባረከች ክርስቲያኖችዋን ወደ መንግስተ ሰማይ ትመራለች፡፡ ቤተክርስቲያን ቅድስት ስትሆን በውስጧ ኃጢያንም ቅዱሳንም ይገኛሉ፡፡ ኃጢያንንም ወደ ቅዱሳን እየመራች ለመንግስተ ሰማይ ታበቃለች፡፡

ታዲያ ዛሬም ቤተክርስቲያን ያኔ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደጋበዘን የተጠማ ቢኖር ወደኔ ይምጣ እያለች ጥሪዋን ታሰማለች ጥሪዋን ስታሰማ ግን እሷን እንደ ክርስቶስ የዚህ ወገን የዛ ወገን ሳትለይ የዚህ ዘር፣ የዛ ዘር ሳትል የተጠማውን ሁሉ ትጣራለች።

ዛሬ የምንኖርባት ዓለማችን እጅግ በጣም ብዙ የሚባሉ ነገሮችን የተጠማች ዓለም ናት። ሰዎች እርካታ አጥተው በመባዘን ላይ ይገኛሉ፣ ሕይወታችን ረፍት አጥታ በመቃተት ላይ ትገኛለች። ዛሬ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም ረሃባችንን እና ጥማታችንን ማስታገስ እንችል ዘንድ ወደ እርሱ ይጋብዘናል። ለነፍሳችን ጥም እርካታ የሚሰጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፣ ብዙን ጊዜ ጥማችንን ያረኩልናል ብለን ያሰብናቸውን ዓለማዊ የሆኑ ነገሮችን በማከናውን እርካታን ለማግኘት እንሞክራለን፣ ነገር ግን የእርካታችን መንጭ አንድ እና አንድ ነው፣ ጌያ ኢየሱስ ብቻ ነው። እርሱም ወደ እርሱ መጥተትን በነጻ ይህንን የሕይወት ውሃ እንድንጠጣ ይጋብዘናል፣ እኛም ይህንን የእርሱን ጥሪ ተከትለን የሕይወት ጣማችንን ማርካት እንችል ዘንድ ወደ እርሱ መቅረብ ይኖርብናል። ወደ እርሱ መቅረብ እንችል ዘንድ እና ለሕይወታችን እርካት ማግኘት እንችል ዘንድ እንድትረዳን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት መማጸን ይገባል። የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን።

ምንጭ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

13 August 2020, 09:30