የነሐሴ 17/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 8ኛ ቅዱስ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ
የዕለቱ ምንባባት
2. 1ጴጥ 4፡12-19
3. የሐዋ 9፡1-7
4. ዮሐ 15፡12-26
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም፤ የማዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ አገልጋዮች አልላችሁም፤ አገልጋይ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ። እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ እንድት ሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬያችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። ስለዚህም አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት።
ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ
“ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል። ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።
“እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ (ዮሐ 15፡12-26)።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
በቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘክረምት 8ኛ በመባል ይታወቃል። በነዚህ ጊዜያት ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ አማካኝነት የተለያዪ ትምህርቶችና መልዕክቶች አስተላልፎልናል ።
በዚህም መሠረት በዛሬው በመጀመሪያ መልዕክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዮስ (3፡1-14) በላከው መልዕክት የደስታን ዜና እያበሰረ ይጀምራል፣ ወንድሞቼ ሆይ በጌታ ደስ ይበላችሁ ይለናል ። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜም ቢሆን በሰው ልጆች ልብ እና አእምሮ ውስጥ ደስታን ለማስረጽና በደስታ እንዲኖሩ ለማድረግ የሰበከውንና ያከናወነውን ተግባር ያስታውሰናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ይህንን ደስታ ለሰው ልጆች ለማወጅ ነው፣ ይህንንም በሉቃስ ወንጌል (4፡ 19) ጀምሮ ሲገልጸው “ለታሰሩት መፈታትን ፣ ለታወሩት ማየትን እና የተጠቁትን ነፃ አወጣ ዘንድ መጥቻለሁ” ይለናል።
ታድያ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ደስታ ነው ሊያካፍለን የወደደው። (ገላ 5፡22) ላይ ደስታ ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ እንደሆነ ይናገራል፣ ታድያ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው በፊሊጲስዮስ መልእክቱ ይህንን ደስታ የሕይወታችን መሣርያ አድርገን እንድንይዝ ይመክረናል። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ ውስጥ የሚመላለስ ሰው ከክፉ ሁሉ እራሱን እንደሚጠብቅና በሐሰተኛ ግርዛት ሳይሆን በትክክለኛ በእግዚአብሔር መንፈስ እንደሚመራና እንደሚመላለስ ያስታውሰናል።
ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በራሱ አንደበቱ ገና በስምንተኛው ቀን መገረዙን የአይሁድ ሕግ መጠበቁን ስለ አይሁድ እምነቱም ብሎ ብዙ ክርስቲያኖችን አሳዷል፣ ነገር ግን ከእዚያን በኋላ የጌታ መንፈስ ወደ ልቡ ገብቶ ሲገልጽለት እስከ አሁን የተጓዘው ጉዞ የተሳሳተ መሆኑን ተረዳ፣ እንግዲህ ይህ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወቱ እንዲቀየርና ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገባ ምክንያት የሆነው። ይህንንም በማድረጉ የእውነተኛ ደስታ ተቋዳሽና መስካሪ ለመሆን በቃ።
ዛሬም የእኛ ሕይወት ይህ ነው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን ከያዝን ከእርሱ ጋር የምንጓዝ ከሆንን ደስታ የተሞላ ሕይወት ወደ ሄድንበት ሁሉ ይዘን እንሄዳለን ማለት ነው። እውነተኛ ደስታ እውነተኛ ጽድቅ ሁሌም በሥራችን ወይም በድካማችን የምናገኘው ወይም ደግሞ የምናመጣው ነገር ሳይሆን እግዚአብሔር ልባቸውን ከፍተው ከእርሱ ጋር መጓዝ ለሚፈልጉት የሚሰጠው ነጻ ስጦታ ነው። በእዚህ ሁኔታ ውስጥ ለመመላለስ ግን ሁሌም በመከራ ውስጥ ተፈትኖ ማለፍን ይጠይቃል። ለዚህ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ (1ኛ ቆሮንጦስ 15፡31) ላይ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሁሌም ለመሞት ዝግጁ እንደሆነ የሚገልጸው። ምክንያቱም ከእርሱ ጋር በመሞት ከእርሱ ጋር የመከራው ተካፋይ በመሆን፣ የትንሳኤና የደስታውም ተካፋይ መሆን እንደሚቻል ተረድቷልና ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬም ሁላችንን የእርሱን መንገድ እንድንከተል ይፈልጋል፣ ልክ እንደ እርሱ እኛም ራሳችን እውነተኛ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ወታደሮች የማንሆንበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ያስገነዝበናል። የዛሬው ሁለተኛው መልእክት( 1ኛ ጴጥሮስ 14) ላይ ይህንን ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተማረውን ትምህርት ወደ ተግባር መለወጥ ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅ ይናግራል። ምን አልባት በዚያን ጊዜ ማለትም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቱን በጻፈበት ወቅት ብዙ ክርስቲያኖች በተለያየ ቦታ የሥደት ፣ የመክራ ጽዋ እንደተጎነጩ ነበር። ነገር ግን ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በተለይም “ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው እናንተመም እምነታችሁ በመከራና ፣ በጭንቀት እና በእሳት እየተፈተነ መሆኑንና ከእዚህ እሳት ግን ተፈትነው ከወጡ በኋላ እጅግ በጣም ደስተኞችና እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን” ያሰምርበታል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን ሥቃይን ያውም እስከ መስቀል ድረስ ተቀብሉዋል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያቶች በሙሉ የዚህ መከራና ስቃይ ተካፋዮች ነበሩ። ዛሬም በተለያየ መልኩ ይህ መከራና ስቃይ አለ። ነገር ግን አሁንም ማስተዋል ያለብን ጉዳይ በመከራ ውስጥ ጽናት፣ በሐዘን ውስጥ ደስታ፣ በለቅሶ ውስጥ ሳቅ እንደሚገኝ ልንረዳ ይገባል። “በክርስቶስ መከራ በመሳተፋችን በኋላ የክብሩ ተካፋዮች ስለሚያደርገን” (ሮሜ 8፡17) በእነዚህ ቃላት ጽናት እና ድፍረት ደስታም ሊሰማን እንደሚገባን ይነግረናል። በጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እና መክራ መሳተፋችን ኋላ የደስታው እና የክብሩ ተቋዳሾች እንደሆንን ይነግረናል፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መቀበላችን የእግዚአብሔር መንፈስ በላያችን እንዲያርፍና ከእኛ ጋር እንዲኖር መንገድ እናመቻቻለን፣ ይህም ወደ ቅድስና ለምናደርገው ጉዞ በር ይከፍትልናል። ሁሌም በመከራ ውስጥ እምነታችን መፈተኑንና መጠንከሩን ልብ ብለን በመያዝ በእምነታችን ጸንተን ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል።
በዩሐንስ ወንጌል (13፡34) ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጣቸው “አዲስ ትእዛዝ” “እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት እንደገና ይደግመዋል። ከእዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው አንዱ ለወዳጁ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ቢፈልግ ፣ ለወዳጁ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ መስጠት እንዳለበት ለደቀመዛሙርቱ ነገራቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን የወደዳቸው ዛሬም እኛን የሚወደን በእንደዚህ ዓይነት ፍቅር ነው። ይህንንም ፍቅሩን የገለፀልን ሕይወቱን በመስቀል ላይ አሳልፎ በመስጠት ነው። “ወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስበርሳችን ልንዋደድ ይገባል። እግዚአብሔርን ከቶ ማንም አላየውም፣ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍፁም ሆንዋል” (1ዩሐ ም 4፡11)።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ያዘናል፣ ይህም ማለት አንዳችን ለሌላው ሕይወታችንን እስከመስጠት ድርስ የፍቅር መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁነታችንን በአኗኗራችን በማሳየት ይሆናል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን “ወዳጆቼ” በማለት ጠራቸው ዛሬ እኛንም “ወዳጆቼ” በማለት ይጠራናል፣ ነገር ግን የእርሱ ወዳጅ ለመሆን እርሱ ራሱ የሰጠውን ትእዛዝ በሕይወት መኖር ያስፈልጋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንም ዛሬ ወዳጆቼ ብሎ በመጥራት ከእርሱ ጋር በነፃነት እንድንነጋገር ወደራሱ ይጠራናል ፣ በመንፈስቅዱስ አማካኝነት ልናውቀው የሚገባንን ነገር ሁሉ ይገልጥልናል።
በመጀመሪያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል የመረጡት ሰዎች አይደሉም ፣ ይልቁንም እርሱን እንዲከተሉት ሰዎችን ሁሉ ሰፊ በሆነው ፍቅሩ አማካኝነት ሁላችንንም ያለምንም ልዩነት በእኩል ወደ ፍቅሩ ድግስ ጠርቶናል ፣ ዛሬም በቅዱሳት ምስጢራት አማካኝነት ዘወትር ጥሪውን ያቀርብልናል።
እያንዳንዳችን በእርሱ የፍቅር ጥሪ ውስጥ በመሳተፍ ከእራሳችን ጀምሮ ፣ በቤተሰቦቻችን እና በጎረቤቶቻችን እንዲሁም በምናውቃቸውም ሆነ በማናውቃቸው ሰዎች መካከል የእርሱን የፍቅር ተልዕኮ በመቀጠል ፍሬ እንድናፈራ ተጠርተናል። ፍሬ ለማፍራት ጸጋና ኃይል እንዲሰጠን ጠይቀን ጥያቄያችን ሳይመለስ የቀረው ስንት ጊዜ ነው ? ለጥያቄያችን መልስ ሳናገኝ ስንቀር መልስ ያላገኘነው ለምንድን ነው ? ብለን እንጠይቃለን ። የእነዚህን ጥያቄዎችን መልስ ለመረዳት እርሱ ራሱ የሰጠንን ትእዛዝ በሚገባ አለመረዳታችን ይሆናል። እዚህ ላይ አንድ ትልቅ እውነት እንማራለን ይህም እግዚአብሔርን የምናከብርበት እና ከታላቁ ክብር እና ጸጋ የምንካፈልበት አንድ መንገድ አለ፣ ያም መንገድ የመታዘዝ መንገድ ነው። መንፈስ ቅዱስን የምንቀበለው እና በእኛ ውስጥ ሊሠራ የሚችለው ስንታዘዝ ብቻ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የሚኖረው እኛም በእርሱ ትእዛዝ ስንኖር ነው። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር መኖር የምንችለው በመታዘዝ ነው። ይህንን ለመፈፀም እንዲያስችለን የታዛዥነት ተምሳሌት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ጸጋና በረከት ከልጇ ታማልደን።
የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !
አዘጋጅ እና አቃርቢ አባ ቢኒያም ያዕቆብ