ፈልግ

በፍቅር ላይ መሰረቱን ያደረገ እምነት በፍቅር ላይ መሰረቱን ያደረገ እምነት  

በፍቅር ላይ የተመሰረተ እምነት

መግቢያ

እ.አ.አ ከጥቅምት 11/2012 እስከ ሕዳር 24/2013 ዓ.ም ድረስ በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የእምነት ዓመት እንድሆን አውጀው እንደ ነበረ ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የእምነት ዓመት እንድሆን ይህን ዓመት የወሰኑበት ምክንያት ከክርስቶስ የተቀበለንውን እምነት ለማበረታታትና ከአባቶቻችን ከሐዋርያት የተላለፈልንን እምነት በተለይም በጸሎተ ሃይማኖት የሚደገመውን አንቀጸ ሃይማኖት የበለጠ በማወቅ እንድንጸልይበት ነው፡፡ የእምነት ዓመት ዋና ዓላማ ክርስቲያኖች ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታደሰ መንፈስ በየቀኑ ወደ ፍጽምና ሕይወት ለመለወጥ ሚጥሩበት ዓመት ማለት ነው (Porta Fidei. No. 6)፡፡ በየዘመኑ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ የሚመዘነው በሥሯ ታቅፎ የሚገኙ ምእመናኖች በእለታዊ ኑሮአቸው በሚያሳዩት የሕይወት ምስክርነት ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችን ትምህርተ ክርስቶስ ማእከል ደግሞ «ጸሎተ ሃይማኖት» ነው፡፡ ጸሎተ ሃይማኖት፡- የመጀመሪያው የጌታ ተከታዮች የሆኑ የሐዋርያት እምነት ጭማቂና መሠረት ሲሆን የጥንታዊ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት ምሥጢር ዋና ምልክት ነው፡፡ በጥንት ዘመን ክርስቲያኖች ጸሎተ ሃይማኖትን በቃላቸው በየዕለቱ ይደግሙ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ጸሎቱን በየዕለቱ የሚደግሙት ምክንያት በምሥጢረ ጥምቀት አማካይነት ያገኙትን የክርስትና አደራ እንዳይዘነጉ ልክ እንደ ዕለታዊ ጸሎት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ዛሬም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በተለይም «ጸሎተ ሃይማኖት» ለእምነተታችን መነቃቂያ እንደ ትልቅ መሣሪያ ሊያገለግለን ይችላል፡፡

1. መኖር የሚገባን እምነት፤

በእምነት ዓመት እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ምእመን በሀገር፣ በሀገረ ስብከት እና በቁምስና ደረጃ በሚሰጠው ትምህርት መሠረት ከክርስቶስ ያገኘውን እምነት ለመኖር ብሎም ለመንከባከብ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት አለበት፡፡ እምነት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ቁልፍ የሆነ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም (ዕብ. 11፡6) ፡፡ እምነት የእግዚአብሔር ቃል እውነት የመሆኑ የዋስትና ስሜትና በዚያ ሕያው ቃል መኖር በረከትን እንደሚያስገኝ እርግጠኛ መሆን ነው፡፡

ሰውን የሚያድነው ምን ዓይነት እምነት ነው? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ሲናገር «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም» (ማቴ.7፡21) ብሏል፡፡ የሚያድነን እምነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምያስፈጽም ነው፡፡ እውነተኛ የሚያድን እምነት ወደ ተግባር ይመራል፡፡ ኃይል ያለው እምነት በእውቀት የሚገኝ ጥልቅ ምርምር ወይም ስሜታዊ ክንዋኔ አይደለም፤ በፈቃድ ላይ ወደ ተመሠረተ መታዘዝ የሚመራ ነው፡፡ ይህ መታዘዝ ደግሞ የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመን ሁሉ የሚቀጥል ነው፤ ወደ ተግባር የሚመራ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው» ብሏል (ሮሜ. 10፡17) ፡፡ እምነት መልካም የሚሆነው ከምናምንበት ጉዳይ አንጻር ነው፡፡ ደኅንነት ያገኘነው እምነትን በማመን አይደለም፤ ነገር ግን በቃሉ በተገለጠልን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በማመን ነው፡፡ ይህንን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤን የሚታውጅልን የእርሱ ሙሽራ የሆነችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ማኅደረ ሃይማኖት ናት፡፡

2. ስለ ሥላሴ ያለን እምነት

እኛ የምናምነው አምላክ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አብ፤ የእርሱም አንድያ ልጅና መንፈስ ቅዱስ «ቅድስት ሥላሴ ነው»፡፡ የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር የክርስትና እምነትና ሕይወት ሁነኛ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ በእግዚብሔር በራሱ ውስጥ ያለ ምሥጢር ነው፡፡ የድኅነት መላው ታሪክ አንድ እውነተኛ አምላክ፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ራሱን ለሰዎች የሚገልጥበት መንገድና ብልሃት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ አንድ ነው፡፡ ሦስት አማልክት አሉ ብለን አናምንም፤ ሦስት አካላት ያሉት አንድ አምላክ፣ «የሥላሴ አንድነት» እናምናለን፡፡ ይህም መለኮታዊ አካላት አንድ መለኮት የሚጋሩ ሳይሆን እያንዳንዳቸው በምሉእነት አምላክ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ አንዱ መለኮታዊ አካል ከሌላው ይለያል፡፡ «እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ግን ብቸኛ አይደለም»፡፡ አንዱ አካል ከሌላው በግልጽ ይለያና «አብ»፣ «ወልድ»፣ «መንፈስ ቅዱስ» ለመለኮታዊው ሕላዌ የተሰጡ ስሞች ናቸው፡፡ «አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ ሲሆን፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሠራፂ ነው፡፡» (ት/ክርስቶስ፤81-82) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ «የምኖርለትንና የምሞትለትን፣ እንደ ቅርብ ወዳጄም እንዳይለየኝ የምፈልገው፣ ክፋትን ሁሉ የሚያስችለኝንና ሐሴትን ሁሉ የሚያስንቀኝን ታላቅ የእምነት ሀብት ማለቴ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚሆነውን እምነቴን ከምንም ነገር በላይ ጠብቁልኝ፡፡ ዛሬ ይህንን ለእናንተ አደራ ሰጥቼአለሁ፡፡ የምሰጣችሁም አንድ ሆኖ ሦስት አካላት ያሉት፣ ሦስቱን በግልጽ ልዩነት ያካተተ አንድ መለኮትና ኃይል ነው» (ት/ክርስቶስ፤83) ብሏል፡፡

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ «እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ ራሱን ሊገልጥና የሰው ልጅ ሥጋ በሆነው ቃል ማለትም በክርስቶስ አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ወደ አብ የምንደረስበትንና በመለኮታዊ ባኅርይ ተካፋይ የሚሆንበትን የፈቃዱን ምሥጢራዊ ዓላማ ለኛ ሊያሳውቅ ወደደ» (2ኛ ቫቲካን መሎኮታዊ መገለጥ 1፡2) ይላል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ራሱንና የራሱን ዕቅድ ለእኛ ለልጆቹ መግለጡ እውነታ ከእኛ ተግባራዊ ምላሽ ይጠይቃል፡፡ ያም ተግባራዊ ምላሽ «እምነት» ይባላል፡፡ ወደ ዕብራውያን በተላከው መልእክት ጻሐፊው ስለ እምነት ሲገልጽ « እምነት ማለት በተስፋ የሚጠበቀውን ነገር አዎን በእውነት ይሆናል ብሎ መቀበል ነው፤ በዐይን የማይታየውንም ነገር እንደሚታይ አድርጎ መቊጠር ነው» (ዕብ. 11፡1-2) ይላል፡፡ እምነት እንደራዕይ ለማየትም ሆነ ለማረጋገጥ በማንችላቸው እውነታዎች አኳያ ጽኑ እምነትን፣ ቁርጥ አሳብንና ተአማንነትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ ነው፡፡ እምነት እግዚአብሔር በገለጣቸው እውነቶች መሠረት በመኖርና በማመን እርሱንና የርሱን ሕይወት መቀበል ነው (እምነታችን ፡15)፡፡ በእግዚአብሔር እውነትና ሕይወት የማመን በነርሱም መሠረት የመኖርና ብርታት የምናገኘው ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው (ዮሐ. 14፡1-2) ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እምነት ሲናገር «አሁን በመስተዋት እንደምናየው ዐይነት በድንግዝግዝ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ግን በግልጽ እናያለን፤ አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያህል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል» (1ቆሮ. 13፡12) ብሏል፡፡

እግዚአብሔር በመሠረቱ ምሥጢር ነው፡፡ ምሥጢራዊ የሆነውን ስሙን ያሕዌን «እኔ ያለሁ እሱ ነኝ»፣ «እኔ የሆንሁ ነኝ» ወይም «ያለና የሚኖር ነኝ» (ዘጸአት 3፡14) ብሎ ለሙሴ ሲናገር እግዚአብሔር ማንነቱንም ምን ተብሎም እንደሚጠራ ተናግሯል፡፡ ይህ መለኮታዊ ስሙም ምሥጢራዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስውር አምላክ ነው፤ ስሙም በቃላት የማይገለጽ ነው፤ የእግዚአብሔር ማንነት በሰው አንደበት ሊገለጽ አይችልም፡፡ እርሱ ራሱን የሚገልጽ ከሁሉም የላቀ ማለትም ከፍጥረቱ ሁሉ ፍጹም ልዩና ሊደረስበት የማይቻል ሆኖ ነው፡፡ ከዚህም በቀር፣ እግዚአብሔር ዓለምን የሞላ፣ ማለትም፣ በፍጥረቱ ዘንድ የሚገኝና ከርሱም ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ አንዳንድ መለያ ጠባያት የርሱን ግርማ ሞገስና የበላይነትነት አጉልተው ሲያሳዩ፣ ሌሎቹ ባህርያት ስለ እኛ ያለውን ቅርበትና አሳቢነት በአጽንኦት ያወሳሉ (እምነታችን፤ገጽ. 22) ፡፡    

3. በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለን እምነት፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል መሆኑን ሐዋርያት ይመሰክራሉ፡- «ቃል በመጀመሪያ ነበር፤ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበር» (ዮሐ.1፡1) በማለት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እርሱ «ለማይታየው እግዚአብሔ ምሳሌ፤ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ የባሕሪውም ማኅተም ነው» (ቈላ.1፡15፣ ዕብ.1፡3) ብሏል፡፡

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡» (ዮሐ.3፡16) ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ከሁሉም የበለጠ ነገር፣ ይኸውም፣ ዘላለማዊ ደኅንነትን አስገኝቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና «እምነት ጉዞ» እምብርት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ከፍተኛው መግለጫ ነው፡፡ ራሱ ሲናገር «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፣ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ማንም ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡ እኔን አውቃችሁኝ ቢሆን ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፡፡» (ዮሐ.14፡6-7) ብሏል፡፡ እርሱን ማውቅ የምንችለው በእምነት ነው፡፡  

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለሰው ልጆች «አዳኝ» (ማቴ.1፡21) ነው፡፡ ደኅንነት እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ለእኛ ያሰበልን በጎ ነገርና ደስታ ነው፡፡ በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ያገኘነው ደኅንነት የኃጢአት ቁስላችን ፈውስ፣ የእግዚአብሔር ሰላም ነው፡፡ ደኅንነት ከእግዚአብሔርና ከሰው ሁሉ ጋር አንድ አካል እንዳንሆን ያደረገን የተቋረጠ ግንኙነት መጠገኛ ነው፡፡ በክርስቶስ ያገኘነው ደኅንነት በእኛ ላይ የሚፈስ የእግዚአብሔር ቡራኬና ጸጋ ከመሎኮታዊ ቤተሰቡ (ቅድስት ሥላሴ) ጋር የመቀላቀያ፣ ሕይወቱን ከእኛ ጋር መጋሪያ ነው፡፡ የጌታችን አዳኝነት የእርሱ ፍቅር፣ የእርሱ አገልግሎት፣ የእርሱ መሥዋዕትነት፣ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አማካይነት ሞት ራሱ አብሮ ሞተ፡፡ የትንሣኤ ሕይወት ተጀመረ፡፡ ጌታችን በአዳኝነቱ ያደረገውን ማለትም የኃጢአት ስርየትንና የዘላለማዊ ሕይወት ስጦታን ሌላ ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም (እምነታችን፤55)፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናምን በዚህ ደኅንነት ምሥጢር እናምናለን፡፡

03 August 2020, 10:17