ፈልግ

በፖርቱጋል አገር የሚገኘው የፋጢማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ በፖርቱጋል አገር የሚገኘው የፋጢማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ  

ብፅዕት ድንግል ማርያም እና ቤተ ክርስቲያን

“አንድ እግዚአብሔር አለና፤ ደግሞም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አንድ አስታራቂ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሰዎች ሁሉ ቤዛ አድርጎ ሰጠ” (1ኛ ጢሞቴ 2፡5-6) ከሚሉ የሐዋርያው ቃላት ውስጥ በመአከሉ የሚገኝ አንድ ነገር እንዳለ እንገነዘባለን። ማርያም በሰው ላይ ያላት እናታዊ ተግባር ተወዳዳሪ የሌለው የክርስቶስ መካከለኛነት እንዲበረታ ያደርጋል እንጂ በምንም ዓይነት አይጋርደውም፤ ወይም አይቀንሰውም ምክንያቱም ብፅዕት ድንግል ስለሰው የምታደርጋቸው የማዳን አማላጅነቶች የሚመጡት ከእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ነው እንጂ ከውሥጣዊ አስፈላጊነት አይደለም፡፡ እነዚህ አማላጅነቶች ከክርስቶስ ተግባር ይወጣሉ፤ ከእርሱም አስታራቂነት ይመነጫሉ፤ ፈጽሞም በእርሱ ሥር ናቸው ኃይላቸውንም የሚያገኙት ከሱ ብቻ ነው፡፡ ከክርስቶስ ጋር ያለ ቅርብ የሆነ የእምነት ሱታፌ በእነዚሁ አማላጅነቶች አማካይነት አይታገድም ይልቁኑ በእነሱ ይዳብራሉ፡፡

ብፅዕት ድንግል የአምላክ እናት ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተወሰነው መለኮታዊ ቃል ሥጋ ለመሆን ከአቀደበት ከዘለዓለም ጀምሮ ነው፡፡ ማርያም “በእግዚአብሔር ታላቅ ጥበብ” በዚሁ ምድር የመለኮታዊው መድኀን እናት የእርሱም ተባባሪና የጌታ ትሁት አገልጋይ ሆና እንድታገለግል ተደረገች፤ እርስዋ ክርስቶስን ፀነሰች፤ ወለደች፤ መገበች በቤተ መቅደስም ለአባቱ አቀረበችው፤ በመስቀል ላይ ሲሞት የስቃዩም ተካፋይ ሆነች፡፡ መልዓተ-ባሕርያዊ ሕይወት ተመልሶ ለነፍሳት ይሰጥ ዘንድ በመታዘዝዋ በእምነቷ በተስፋዋና በጋለ ፍቅርዋ ልዩ በሆነ ሁኔታ በመከራ ውስጥ ተካፋይ ሆነች፡፡ እንግዲህ እርስዋ በጸጋ እናታችን ናት፡፡

ይህ የማርያም እናትነት በጸጋ የተጀመረው መልአኩ የምሥራቹን ቃል በነገራት እርስዋም እምነት በመላበት መንፈስ እሺታዋን  በሰጠችበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን እናትነት ሳታመነታ ተቀብላ እስከ  መስቀል ሥር ድረስ ጸንታ ኖረች፡፡ ይህ የእርስዋ እናትነት እስኪያገኙ የተመረጡት ሁሉ ዘለዓለማዊ ፍጻሜን እስኪያገኙ ድረስ ያለአንዳች   መቋረጥ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም እርስዋ ወደ ሰማይ ስለተወሰደች ይህን የማዳን ተግባር አልተወችም፤ ይልቁንም  እኛ የዘለዓለም ደኀንነት ጸጋ እናገኝ ዘንድ ልዩ ልዩ የሆኑ የምልጃ  ስራዎችን ትቀጥላለች፡፡ ማርያም በፀጋ በመከራ ተከበው ገና በምድር ላይ የሚኖሩትን  የልጅዋን  ወንድሞች  ወደ ቅድሰት አገራቸው እስኪመጡ ድረስ በእናታዊ ፍቅርዋ ታስባቸዋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ቅድስት ድንግል በቤተክርስቲያን ዘንድ “ጠበቃ ረዳት፡ ደጋፊ፡ አስታራቂ” በተሰኙ የማዕረግ ስሞች ተጠራለች፣ ዳሩ ግን እነዚህ ስሞች ተወዳዳሪ የሌለው አስታራቂ ከሆነው ክርስቶስ አንዳችን ክብር እንደማይቀንሱ ወይም ክብርንም ኃይልን እንደማይጨምሩለት መገነዝብ ያስፈልጋል። አዳኙ ሥጋ ከለበሰው ቃል ጋር ሊወዳደር ሊመዛዘን የሚችል አንድ ፍጡር የለም፡፡ ዳሩ ግን ካህናትና ምእመናን ልዩ በሆነ መንገዶች በክርስቶስ ክህነተ ተካፋዮች ስለሆኑ፤ የእግዚአብሔር ደግነትም ልዩ በሆኑ ሁኔታዎች በፍጥረቶች ውስጥ ተሰራጭቶ ስለሚገኝ የመድኀን አስታራቂነት ደግሞ በፍጥረቶች መካከል ከአንድያ ምንጭ ብቻ የሚከፋፈል ብዙ ዘርፍ ያለውን ትብብር ከማስነሣት አይከለከልም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በረዳትነት ረገድ ሁለተኛ ማዕረግን ይዞ የሚገኘው የማርያምን ስራ በይፋ ለመግለጽ አትጠራጠርም፡፡ ያለ ማቋረጥም በተግባር ታስመሰክራለች ምእመናን በዚሁ እናታዊ ፍቅር ጠንክረው ወደ አስታራቂነትና መድኀኑ በይበልጥ ይቀርቡ ዘንድ ይህን የማርያምን ረዳትነት እንዲያፈቅሩ አደራ ትላለች፡፡

ማርያም በመለኮታዊው የእናትነት ስጦታና ስራ አማካይነት ከአዳኙ ልጅዋና ተቀናቃኝ ከሌለው ከጸጋ ስራዎቹ ጋር ታስተሳስራላች። ቅድስት ድንግል በነዚህ ነገሮች ከቤተ ክርስቲያንም ጥልቅ በሆነ ሁኔታ ታስተሳስራለች፤ ቅዱስ አምብሮዚዮስ እንዳስተማረን “የአምላክ እናት” ለእምነት ለፍቀርና ከክርስቶስ ጋር ለሚደረግ ፍጹም አንድነትን ስለሚመለከት ጉዳይ የቤተ ክርስቲያን አርአያ ናት ይለናል። በእውነቱ በቤተ ክርስቲያን ምሥጢር በይፋ እናትና ድንግል ተብላ የምትጠራ ብፅዕት ድንግል ማርያም በድንግልናና በእናትነት ከፍ ያለ እና እንግዳ የሆነ መልክ ያለው አርአያ ሆኖ ትታያለች። ምክንያቱም ማርያም  ስለአመነችና ስለታዘዘች የአብን ልጅ በምድር ላይ ወለደች። ለመውለድም የበቃችው ከወንድ ሳትገናኝ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። እርስዋ በእግዚአብሔር መልእክተኛ እንጂ በጥንታዊው እባብ የማታምን አዲስ ሔዋን ናት፡፡ እርስዋ የወለደችው ልጅ እግዚአብሔር በብዙዎች ወንድሞች “ማለት በምእምናን መካከል በኩር ይሆን ዘንድ” (ሮሜ 8፡29 ተመልከት) ያኖረው ነው። እርስዋ በእርሱ ዳግም ልደትና እድገት በእናታዊ ፍቅር ትተባበራለች።

እንደዚሁም ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መሥጢራዊ የሆነው የማርያምን ቅድስና በጥሞና በማሰብ፤ የእርስዋን በጎ አድራጊነት በመከተል፤ የአብን ፈቃድ በታላቅ ታማኝነት በመፈጸም፤ የእግዚአብሔርን ቃል በመቀበል እናት ሆነች። እርስዋ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተፀንሰው ከእግዚአብሔር የተወለዱ ልጆችን በስብከቷና በጥምቀት አማካይነት ለአዲስና ለማይሞት ሕይወት ስለምትወልዳቸው እናት ሆነች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሙሽራዋ (ለጌታ) ቃል የገባችለትን ታማኝነት በሙሉ ንጽሕና ስለምትጠብቀው ራስዋ ድንግል ናት፡፡ የጌታዋን እናት አርአያ ስለምትከተልና በመንፈስ ቅዱስ ኃይልም ስለምትረዳ ድንግላዊ ንሕጽናን፤ የሃይማኖት ምላትን ጽኑ ተስፋንና እውነተኛ ፍቅርን ጠብቃ ትኖራለች ፡፡

በቤተ ክርስቲያን እጅግ በጣም ብፅዕት በሆነችው ድንግል በኩል ያለ “ጒድፍ ወይም የፊት መጨማደድ” (ኤፌ 5፡27)  ወደ ፈጽምና የደረሰች ብትሆንም እንኳን፤ ምእመናን ኃጢአትን አሸንፈው ቅድስናን ለማብዛት ትልቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ምእመናን የመንፈሳውያን ኃይላት አርአያ ሆና ለምርጦች ሁሉ በማብራት ላይ ወዳለችው ማርያም ዓይኖቻቸውን ያነሣሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ማርያምን በልጅነት ስሜት እያሰበች እርስዋን የሚመለከት ጉዳይ ሥጋ ከሆነው ቃል ብርሃን ፊት አድርጋ እየመረመረች  አክብሮት በመላበት መንፈስ እጅግ ከፍ ወዳለው ወደ ምሥጢር ትገባለች፤ እዚያም በበለጠ አኳኋን ሙሽራዋን ትመስላለች።

        

ማርያም በደኀንነት ታሪክ ውስጥ ጠለቅ ባለ ሁኔታ ተቀርፃ ስላለች አንዳንድ ጊዜ ታላላቅ ዘለዓለማዊ እውነቶችን በልብዋ ውስጥ ሰብስባ ታስገባለች ለማለት ይቻላል። ማርያም እንደዚህ ባለሁኔታ ስትሰብክና ስትከብር ምእምናን ወደ ልጅዋ፤ ወደ መሥዋዕቱና ወደ አብ ፍቅር ይመጡ ዘንድ ትጋብዛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በበኩሏ የክርስቶስን ክብር ለመከተል በሁሉ ነገር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ ማድረግ ፈልጋ ያለማቋረጥ በእምነት፤ በተስፋ፤ በበጎ አድራጎት ወደ ፍቅር በመራመድ ላይ ስላለች የላቀ አርአያዋ የሆነችውን ማርያምን ትመስላለች። ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ስራዋን በምታከናውንበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ስራ ተፀንሶ ከድንግል የተወለደ ክርስቶስ በእርስዋ አማካይነት ከምእምናን ልብ ውስጥ ይወለድ ዘንድና ያድግ ዘንድ እርሱን ወደ ወለደችው ወደ ማርያም ትመለከታለች። ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ “ስለ ሰዎች ዳግም ልደት” የሚተባበሩ ሁሉ ሊነቃቁበት የሚገባ አብነታዊ የሆነ እናታዊ ፍቅር የመላበት ሕይወት ነበራት።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

12 August 2020, 09:36