ፈልግ

የምግብ እርዳታ አቅርቦትን የሚጠባበቁ ተረጂዎ፤ የምግብ እርዳታ አቅርቦትን የሚጠባበቁ ተረጂዎ፤ 

የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር አባላት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁትን በጸሎታቸው አስታወሱ።

የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ቫሌሪዮ ዲ ትራፓኒ ማኅበራቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተይዘው በስቃይ ውስጥ የሚገኙ የዓለማችን ሕዝቦች በጸሎት በማስታወስ ከጎናቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል። እሑድ ሐምሌ 5/2012 ዓ. ም.  በፌስቡክ ማኅበራዊ መገናኛ በኩል በተዘጋጀው የኅብረት ጸሎት የተሳተፉት የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበራት ከ200 መሆናቸው ታውቋል። የኅብረት ጸሎት ሌሎችንም ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም የምዕመናን ማኅበራትን የሚጋብዝ እንደ ነበር ክቡር አባ ቫሌሪዮ አስታውቀው፣ ዋና ዓላማውም የቅዱስ ቪንሴንትን ፈለግ በመከተል “በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በራስ ወዳድነት እና በዘረኝነት የተጎዳ ምድራችንን የሚፈውስ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከእግዚአብሔር ለመለመን ነው ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ በመልካም ሁኔታ መከናወኑን በሮም የሌዮኒያን ኮሌጅ በጎ ፈቃደኞች ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ቫሌሪዮ ዲ ትራፓኒ በቫቲካን ሬዲዮ ለጣሊያንኛ አገልግሎት ገልጸዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ከአስራ ስምንት ሺህ በላይ አባላት መሳተፋቸውን ገልጸው፣ ይህም በርካታ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር አባላት፣ ወንድሞች እና እህቶች መሳተፋቸውን ያረጋግጣል ብለዋል። በዚህ ጸሎት አማካይነት በኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ ክፉኛ በተጠቁ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ፣ በተለይም ድሃ ማኅበረሰብ እግዚአብሔር ፈውሱን እንዲያመጣላቸው መጸለያቸውን ክቡር አባ ቫሌሪዮ አስታውቀዋል።

እርሳቸው በአባልነት የሚገኙበት የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር በዓለማችን በበርካታ አገሮች እንደሚገኝ የገለጹት ክቡር አባ ቫሌሪዮ፣ የጸሎት እገዛቸው ማኅበራቸው ባልደረሱባቸው እና በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቁት አካባቢዎች ለሚገኙ ድሃ ማኅበረሰብ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። የወረርሽኙን መዛመት ለመቀነስ ተብሎ የወጡ ደንቦች፣ የልዩ ልዩ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት የበላይ አለቆች እና የአገራት መሪዎች ወረርሽኙ ባጠቃቸው አካባቢዎች ተገኝተው ሕዝቡን እንዳጠይቁ ማገዱን ገልጸው በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦችን በጸሎት ማገዝ አለኝታነታቸውን ይገልጻል ብለዋል። ድሆችን መጠየቅ፣ ከጎናቸው በመሆን መርዳትን ቅዱስ ቪንሴንት አስተምሮናል ያሉት ክቡር አባ ቫሌሪዮ፣ ወረርሽኙ ባስከተለው አደጋ ውስጥ ለሚገኙት ይህን በተግባር በሚገባ ማከናወን ባይቻልም በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የእግዚአብሔርን እርዳታ በጸሎት በመጠየቅ እና ምስክርነትንም መስጠት አስፈልጓል ብለዋል። ማኅበራዊ ሚዲያዎች በጎ ፈቃድ ያላቸውን ወንድሞች እና እህቶች በማስተባበር፣ በአካል ተገኝተን ማድረግ ያልተቻለውን በጸሎት ለማበርከት አስችሎናል ብለዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በተካሄደው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበው ርዕሥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጠቁትን በጸሎት ከማስታወስ በተጨማሪ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ፣ ሚኒያፖሊስ ግዛት ውስጥ የተፈጸመውን የአፍሮ-አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ግድያን በማስታወስ፣ በሕዝቦች መካከል እየተስፋፋ የመጣው የዘረኝነት መንፈስ ተወግዶ ፣ ሕዝቦች በእኩልነት፣ እርስ በእርስ በመዋደድ እንዲኖሩ በጸሎት ማገዝን የሚያስታውስ መሆኑን አባ ቫሌሪዮ አስታውሰዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሕዝቦች በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸው፣ እርሳቸው በሚኖሩበት ሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙ መጠለያ የሌላቸውን ጨምሮ በድህነት ሕይወት የሚኖሩትን ሰዎች ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን አስታውሰዋል። በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ለሚገኙ ድሆች ከማኅበራቸው በጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር የምግብ ማቅረብ አገልግሎት ማድረጋቸውን አስታውሰው ምግብ እና መጠለያን አጥተው የሚሰቃዩ ወንድሞችን እና እህቶችን መጎብኘት እና የሚቻለውን እርዳታ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

14 July 2020, 18:25