ፈልግ

በቅርቡ በአሜሪካ በተቃጠለው የቅዱስ ገብርኤል ታሪካዊ ቤተክርስቲያን አጠገብ ምዕመናን ጸሎት ሲያደርሱ በቅርቡ በአሜሪካ በተቃጠለው የቅዱስ ገብርኤል ታሪካዊ ቤተክርስቲያን አጠገብ ምዕመናን ጸሎት ሲያደርሱ  

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ላይ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች በፍቅር ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ተባለ!

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ላይ በአንዳንድ ቤተክርስቲያኗን በሚጠሉ ሰዎች አማካይነት እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት እንዳሳሰባቸው የገለጹ ሲሆን በዚህ ጥቃት የቤተክርስቲያኗን ተቋማት ማፈራረስ፣ በእሳት ማቃጠል፣ ቅዱሳን ምስሎችን መሰባበር የመሳሰሉ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ቢሆንም ቅሉ ለዚህ ዓይነቱ በጥላቻ እና በግራ መጋባት መንፈስ ለሚከናወኑ ጥቃቶች የሚሰጠው ምላሽ በፍቅር እና በመግባባት መንፈስ ላይ የተመረኮዘ መሆን እንደ ሚገባው የአገሪቷ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመልእክታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዜና እቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 15/2012 ዓ.ም ከቅርብ ጊዜያት ጀመሮ በቤተክርስቲያኗ ተቋማት ላይ እየተከሰቱ እና በመጠን እያደጉ የመጡትን ጥቃቶችን ተከትሎ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት በቤተክርስቲያን፣ በቅዱሳን ምስሎች እና ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም በሌሎች የሃይማኖት ምልክቶች ላይ የሚሰነዘሩ በርካታ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን በመልእክታቸው አብክረው ገልጸዋል።

“አገራችን በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈሪ በሆነ የባሕል ግጭት ውስጥ ትገኛለች” በማለት ጉዳዩን አስመልክተው በጹሑፍ መልእክት ያስተላለፉት የማያሚ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ እና የኦክላሆማ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ፖል ኮክሌይ እንደ ነበሩ ተገልጿል።

የጭካኔ ድርጊቶች እና ጥፋት

በሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሃይማኖት ነፃነት እና የአገር ውስጥ ፍትህ እና የሰብአዊ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ እንደ ገለጹት ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በፍሎሪዳ ውስጥ አንድ ሰው መኪናውን ተጠቅሞ በቤተክርስቲያን ላይ አዳጋ ለማድረስ እና ቤተክርስቲያን ለማቃጠል የሞከረውን ሰው ጨምሮ በርካታ የአመጽ ድርጊቶችን በአሜሪካ በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ እንደ ሆነ ገልጸዋል።  ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በርካታ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅድስት ድንግል ማርያም ምስሎች “እንዲሰባበሩ ወይም ገጽታቸው እንዲጠፋ፣ ሐውልቶችም አንገታቸው መቀንጠሳቸውን” ሊቀ ጳጳሱ በመልእክታቸው አስታውሰዋል።

በሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ታሪካዊ ቤተክርስቲያን በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በእሳት እንዲወድም እንደ ተደረገ የተገለጸ ሲሆን የአደጋው ምክንያት እስካሁን እንዳልታወቀ ጨምረው ገለጸዋል።

ምክንያቶች ግልጽ አይደሉም

ሊቀ ጳጳሱ እንደተናገሩት “እነዚህን ድርጊቶች የፈጸሙት ሰዎች ችግር ላይ የወደቁ ግለሰቦች ወይም የጥላቻ ወኪል በሆኑ ሰዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሊሆኑ የሚችል ቢሆንም ጥቃቶቹ መፈወሻ የሚያስፈልጋቸው በህብረተሰብ ውስጥ የሚንጸባረቁ ምልክቶች ናቸው” ብለዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ በበኩላቸው እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙበትን ምክንያት ግልፅ አለመሆኑን በመገንዘባቸው ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሰዎች እየፀለዩ መሆናቸውን በመግለጽ “በበኩላችን ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል የበለጠ መጠንቀቅ ይኖርብናል” ብለዋል።

ለጥላቻ በፍቅር ምላሽ መስጠት

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ በሰጡት መግለጫ “ወደፊት የምንሄድበት መንገድ ኢየሱስ እና ቅድስት እናቱ የተለማመዱት እና ያስተማሩት የርህራሄ እና የመግባባት መንገድ መሆን አለበት” ብለዋል። ቅዱሳን ስፍራዎችን ከማውደም ይልቅ “የእነዚህን የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸባቸውን ምሳሌዎች” ማሰላሰል እንደ ሚገባም አክለው ገልጸዋል።

ሁለቱ ሊቀ ጳጳሳት “የጌታችንን አርአያ በመከተል፣ ግራ ለተጋቡት በማስተዋል፣ በጥላቻ መንፈስ ለታወሩት ደግሞ በፍቅር ምላሽ እንሰጣለን” ካሉ በኃላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

24 July 2020, 11:22