ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጃፓን ሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ ንግግር ሲያደርጉ፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጃፓን ሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ ንግግር ሲያደርጉ፤  

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የጸሎት ጥሪ አቀረቡ።

በሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ ዓለም አቀፍ የፍትህ እና የሰላም ኮሚቴ፣ በሁለቱ የጃፓን ከተሞች፣ በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የተፈጸሙ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች 75ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፣ ዕለቱ በጸሎት እንዲታወስ በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

የቫቲካን ዜና፤

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ለጃፓን ሰላምን በመመኘት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1945 ዓ. ም. በሁለቱ የጃፓን ከተሞች፣ በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የተፈጸሙትን የቦምብ ጥቃቶች በጸሎት ማስታወስ ያስፈልጋል በማለት የጸሎት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። መጭዎቹ ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 3/2012 ዓ. ም. በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተፈጸሙባቸው ቀናት መሆኑን አስታውሰው፣ ይህም አደጋው የደረሰበት 75ኛ ዓመት የሚታወስባቸው ቀናት መሆናቸውን ብጹዓን ጳጳሳቱ ገልጸዋል። በብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ዓለም አቀፍ የፍትህ እና የሰላም ኮሚቴ ሰኞ ሐምሌ 6/2012 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በሁለት የጃፓን ከተሞች አደጋን ያደረሱት የአቶሚክ ቦምቦች የመጀመሪያዎች እና በድጋሚ ለጦርነት መዋል የሌለባቸው ናቸው በማለት ገልጿል። የኮሚቴው መግለጫ በማከልም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዓለማችን ውስጥ የሚካሄዱ አካባቢያዊ የፖለቲካ ግጭቶች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ወገኖች የሚሳተፉበት፣ በተራቀቁ የጦር መሣሪያዎች የታገዙ፣ በዓለማችን ውስጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን የሚከልክል ሕግ የተጣሰበት መሆኑን አስታውቋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ሆነው ባወጡት መግለጫ፣ በዓለማችን ውስጥ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ግብይትም ሆነ ጥቅም ላይ ማዋል በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። 

የብጹዓን ጳጳሳቱ የጸሎት ጥሪ፤

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1981 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ወደ ጃፓን ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ በጃፓን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ አሥር ቀናትን የሚወስድ የሰላም ተማጽኖ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ስትፈጽም መቆየቷን የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት አስታውሰዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ይህን መሠረት በማድረግ፣ የጃፓን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ ከተሞች የተፈጸመውን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት 75ኛ ዓመት በምታስታውስበት ወቅት፣ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በጋራ ሆነው በመጭው ነሐሴ 3/2012 ዓ. ም. በሚካሄደው የጸሎት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም የሰሜን አሜሪካ ቤተክርስቲያን ሰላም በዓለማችን እንዲሰፍን በማለት ለምዕመናኖቿ የጸሎት ጥሪን ስታቀርብ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገኘውን የእግዚአብሔር የማዳን ሥራንም ለመመስከር መሆኑን አስታውቀዋል።  

ሰላም የነገሠበት ዓለም እንዲሆን፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር 2019 ዓ. ም. ወደ ጃፓን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስትወሱት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ የነጻ ሰላማዊ ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይመኙታል” ማለታቸውን አስታውሰዋል። ጳጳሳቱ በማከልም ቅዱስነታቸው በጃፓን ወደ ናጋሳኪ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው “ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ውግዘት፣ ዘላቂነት ያለው እና ጠንካራ የጋራ አቋም የታከለበት፣ በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ማለታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው “በዓለማችን ውስጥ ፍትህን ለማንገሥ፣ በሕዝቦች መካከል ሰብዓዊ እና ፍትሃዊ አንድነትን ለማምጣት ፍርሃትን ማስወገድ ያስፈልጋል” ማለታቸውን ብጹዓን ጳጳሳቱ አስታውሰዋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመጨረሻም ፍርሃት፣ ጥርጣሬ እና አመጽ በጋራ ጥረታችን መወገድ አለባቸው ብለው “በጠንካራ እምነት እና ጸሎት አማካይነት ሰላም እና ፍትህ በዓለማችን ውስጥ ዛሬ እና ለዘለዓለሙ ሊነግሥ ይችላል” በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል።     

15 July 2020, 18:37