ፈልግ

ዘርና ምድር ፤ የእግዚአብሔር ቃልና የሰው ልብ ዘርና ምድር ፤ የእግዚአብሔር ቃልና የሰው ልብ 

ዘርና ምድር ፤ የእግዚአብሔር ቃልና የሰው ልብ

እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ እርሱም ሲዘራ እንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ወፎችም መጥተው በሉት፣ ሌላውም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ ጥልቅም መሬት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀለ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ፡፡ ሌላውም በእሾክ መካከል ወደቀ እሾክም ወጣና አነቀው ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ አንዱ መቶ አንዱም ስልሳ አንዱም ሰላሳ ፍሬ ሰጠ፡፡ ሐዋርያት የዚህን ምስጢር ትርጉም መረዳት ስላልቻሉ እንዲተረጉምላቸው ለመኑት፡፡ ኢየሱስም “አልሰማችሁንም; ዘር የእግዚአብርሔር ቃል ነው ፤ መሬት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ልዩ ልዩ የሰው ልብ ነው”(.ማቴ. 13፣3-23፤ ማር 4፣3-20፤ ሉቃ 8፣4-15) አላቸው፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የእግዚአብሔር ቃል መልካም ዘር ነው፡፡ ይህ መለኰታዊ ቃል መጀመሪያ ዓለምን ሰማይንና ምድርን ከኢምንት ፈጠረ ፤ ለዕውሮትች ብርሃን አሳየ ፣ በሽተኞችን ፈወሰ ፣ሙታንን አስነሣ፣ ያጠፉትን ሕይወት መልሶ ሰጥቷቸዋል፡፡ ኃጢአተኞችን ለንስሐ ጠርቷል፣ የተጨነቁትንና ያዘኑትን አጽናንቷል፣ በአጋንንት የታሰሩትን ነፃ አውጥቷል፡፡ አሁንም ለዘላለም የሚሆን ፍሬ እንዲያፈራ በሰው ልብ ይህንን መልካም ዘር ለመዝራት በገበሬ ምሳሌ የራሱ ወደ ሆነው ዓለም መጥቷል፡፡ ይህ አይነት ዘር ዘወትር ጥሩ ነው፡፡ አመቺ ሁኔታ ካገኘ ምን ጊዜም ቢሆን ያለ እንዳች ጥርጥር የተጠበቀው ፍሬ ይሰጣል፡፡ ድንገት ለፍሬ ያልደረስ እንደሆነ ከራሱ አይደለም ከመጥፎ መሬት ከዝናም እጥረት ወይም ደግሞ ከፀሐይ እና ከሌላ ከመሳሰለ ምክንያት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ፍሬ ካላፈራ ከራሱ አይደለም ከሚሰማው ሰው ስንፍና ነው፡፡

ሀ/ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ቃሉን ሰምተው የማያስተውሉትን ሰዎች ይመስላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ ባሉ ሰዎች ልብ ሊገባ አይችልም ወይም ቢገባም እንደገባ በፍጥነት ይወጣል፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን መጥቶ እንዳይድኑ መሰናክል ለመፍጠርና ለማጥመድ ይህን በልባቸው የተዘራውን መንፈሳዊ መልካም ዘር በፍጥነት አንስቶ ወስዶ ያጠፋባቸዋል፡፡ እንዲሁ ያሉት ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል በአንድ ጆሮአቸው አስገብተው በሌላ ጆሮአቸውን የማያስወጡትና የሚጥሉት ናቸው፡፡ ልባቸው ደንዳና እና በዚህ ዓለም ሐሳብ የተሞላ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል በውስጣቸው ለረጅም ጊዜ ሊኖር አይችልም፡፡ በዳንኤል መጽሐፍ የሚከተለውን እናነባለን “ንጉስ ናቡከደነፆር አንድ ሌሉት እጅግ የሚያስፈራውና የሚረብሸው አስደንጋጭ ህልም አለመ፡፡ ይህም ሕልም በመንግስቱ ላይ ከጥቂት ጊዜ በኃላ ምን ዕድል እንደሚገጥመው የሚያመለከት ነበር፡፡ ከዚህ አስፈሪ ሕልም ከነቃ በኋላ ምን እንዳለመና ምን እንደሚያደርግ ፈጽሞ ጠፋበት” (ዳን. 2፣1-3)፡፡ ብዙ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰሙ ሰዎች ደግሞ በዚህ ንጉስ ይመሰላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ ቃል ጠንቅቀው ይሰማሉ የዘለዓለም ሐሳብ በአእምሮአቸው ይቀረፃል፡፡ ትዝ ይላቸዋል፣ ብርቱ ኃይል ይቀሰቅሳቸዋል ግን ለጥቂት ጊዜ ነው በልባቸው የሚንቀሳቀሰውን ጊዜያዊ መንፈሳዊ ከቤተክርስቲያን እንደወጡ ሁሉን ይረሳሉ ፣ ወደ ቀድሞ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡

ለ/ በቋጥኝ እና በጭንጫማ መሬት የወደቀው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብለው እንዲያፈሩት ተስፋ የተጣለባቸውን ሰዎች ያመለክታል፡፡ ዘሩ መብቀል ጀምሮ ነበር ነገር ግን በቂ አፈር የሌለው ጭንጫማ መሬት ስለሆነና የፀሐይ ሙቀት የበረታበት በመሆኑ ለአበባና ለፍሬ ሳይደርስ ይጠወልጋል ይደርቃልም፡፡ ብዙዎች ተገንዝበው በጣም አስፈለጊ መሆኑን አውቀው ቆርጠውና ታጥቀው በተግባር ሊፈጽሙት ይወስናሉ፡፡ ችግር እስኪገጥማቸው በጅምሩ  ተግባር ላይ ያውሉታል ጥቂት ቆየት ብለው በተቸገሩ ጊዜ በአንድ አፍታ ቁጥር ፈቃዳቸውን አፍርሰው ይተውታል፡፡ በፈተናና በተጋድሎ ጊዜ ራሳቸውን ተሸንፈው ወደ ኃላ በማለት የተጋድሎና መንፈሳዊውን የጦር ሜዳ ለቀው ያፈገፍጋሉ ይሸሻሉ፡፡ እነዚህ ባላቸው የፈቃድ ስንፍና “መንግስተ ሰማያት የሚወርሷት ኃይለኞች ናቸው” የሚለውን የኢየሱስ ቃል ሊሰሙ አይፈልጉም ማለት ስለ ሰማይ ብርቱ ተጋድሎ ሊያደርጉና ራሳቸውን ሊንቁ አይወዱም፡፡ ይህንንም የማይወዱ በመሆናቸው መንፈሳዊነታቸው ስንፍናና ድካም የተሞላበት በአሸዋ ላይም የተመሠረተ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ቀን ጐርፍ ሲመጣ ሥር መሠረቱ ነቃቅሎ ያፈራርሰዋል ይዞትም ይሄዳል፡፡

ሐ/ በእሾክማ ቦታ የወደቀ ዘር እነዚያ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ንሰሐ ለመግባት የሚፈልጉ ግን በሥጋ ምኞት ስለተጎተቱ በኃጢአት ጫና ስለ ተረገጡ ምስጢረ ንሰሐ ማድረግ የሚያስቸግራቸው ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሰማያዊ ቃል ደስ ብሏቸው ይቀበሉታል ለጊዜው ይቀሰቅሳቸዋል፡፡ ነገር ግን በሰይጣን በዓለምና በሥጋ ሰንሰለት ከባድ ወጥመድ ውስጥ ስለገቡ ለዚህ ኃይለኛ ባርነት ቀንበር በማምለጥ ወደ መልካም መንገድ መመለስና በምስጢረ ንሰሐ ከአምላካቸው ጋር መታረቅ ያቅታቸዋል፡፡ በዚህ መጥፎ ሁኔታ  የንሰሐን ተግባር መወጣት የማይቻል አቀበት እና ትልቅ ተራራ ይሆንባቸዋል፡፡

መ/ በመልካም መሬት  የወደቀ ዘር ብዙ ፍሬ ያፈራና አንዱ ሰላሳ አንድ ስልሳ አንዱ መቶ ፍሬ የሰጠው እነዚያ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በደስታና በጥንቃቄ በልባቸው ውስጥ የሚያሳድሩት እንዲሁም በተግባር የሚያውሉት ሰዎች ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ “እነዚያ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በልባቸው የሚጠብቁትን የታደሉ ብፁአን ናቸው” ይለናል፡፡

እነዚህ የቅዱሳን ወገኖች ናቸው፡፡ እኛስ የትኞቹ ነን? ከእነዚያ የሚያፈሩት ወይስ ከፍሬ አልባዎቹ? ብዙ ጊዜ የእግዚአበሔርን ቃል እንሰማለን ታዲያ ምን እናደረግበታለን? ምንስ እንጠቀምበታለን? በተግባርስ እናውለዋለንን ልባችንስ የትኛውን መሬት ይመስላል መልካም ለም መሬት ወይስ ቋጥኝ የተጫነው ጭንጫና አሽዋማ ነው ወይስ ሁሉ የሚተላለፍበትና የሚረግጠው መንገድ መሬትን ይመስላል; ሕሊናችንን አስተውለን እንመርምረውና መልስ እንሰጠው፡፡

09 July 2020, 15:37