ፈልግ

በከፍተኛ ችግር ውስጥ ከሚገኝ የሶርያ ሕዝብ መካከል፤ T በከፍተኛ ችግር ውስጥ ከሚገኝ የሶርያ ሕዝብ መካከል፤ T 

ክቡር አባ ባጃት፣ የሶርያ ሕዝብ ስቃይ መዘንጋት እንደ ሌለበት አሳሰቡ።

በሶርያ፣ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ የባብ ቱማ ፍራንችስካዊያን ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ባጃት ካራካች፣ በአካባቢያቸው በችግር ውስጥ ለሚገኝ ሕዝብ እርዳታን ተማጽነዋል።

የቫቲካን ዜና፤

አባ ባጃት ካራካች በገዳማቸው ማኅበራዊ መገናኛ ድረ ገጽ በኩል ባቀረቡት የዕርዳታ ጥሪ አካባቢያቸው በጦርነት ሙሉ ለሙሉ የወደመ በመሆኑ ባሁኑ ሰዓት ሕዝቡ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከመጋቢት ወር 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በሶርያ ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የእርስ በእርስ ጦርነት በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ እንደዚሁም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ቤተሰቦች መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሶርያን ሕዝብ ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ ማድረጉ ታውቋል።

በደማስቆ ከተማ አቅራቢያ የባብ ቱማ ፍራንችስካዊያን ገዳም አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ባጃት ካራካች፣ በዚህ አስጨናቂ ወቅት የዕርዳታ ጥያቄያችንን ከማቅረብ ሌላ አማራጭ የለንም ብለዋል። ገዳማቸው የሚገኝበት የቅዱስ ጳውሎስ ቁምስና በጥንታዊው የደማስቆስ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ እና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት ሥፍራ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ቤተክርስቲያን አባል፣ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ያስረዱት አባ ባጃት፣ ማንም ያለ ዕለት እንጀራ እንዳይውል፣ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ ሐዋርያዊ ተልዕኳቸው ያለ በጎ አድራጊዎች እርዳታ ፍሬያማ እንደማይሆን ገልጸዋል። ባለፉት አሥር ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የሶርያ ሕዝብ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት አባ ባጃት፣ በሶርያ ውስጥ ጦርነቱ ካስከተለው ውድመት በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉን አስረድተዋል። የአገራቸው የገንዘብ ምንዛሪም ማሽቆልቆሉን የገለጹት አባ ባጃት፣ በዚሁ መጠን የፍጃታ ዕቃዎች ዋጋም ሦስት እጥፍ መናሩን አስረድተዋል። በመሆኑም የሕዝቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃን፣ ምግብን እና የመሳስሰሉ ቁሳ ቁሶችን የመግዛት አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ባሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።

አንድ የቤተሰብ አባት አንድ ኪሎ ስጋን ለመግዛት አንድ ወር ሙሉ መሥራት ይጠበቅበታል ያሉት አባ ባጃት፣ እንደዚሁም የአንድ ሕጻን የትምህርት ቤት ወጭን ለመሸፈን አንድ ዓመት ሙሉ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል። በአካባቢው የሚገኙት ካህናት እና ገዳማዊያን የቻሉትን የእርዳታ አገልግሎት በማበርከት ላይ መሆናቸውን ያስታወሱት አባ ባጃት ከዕርዳታ ማቅረብ አገልግሎት በተጨማሪ በሐዘን እና በመከራ ውስጥ የወደቁትን ሕዝቦች በማጽናናት፣ መንፈሳዊ ድጋፋቸውንም በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሶርያዊያን ራሳቸውን የሚመግቡት ምንም አቅም የላቸውም ያሉት የባብ ቱማ ፍራንችስካዊያን ገዳም አስተዳዳሪ አባ ባጃት ካራካች፣ የእርዳታ ጥሪያቸው በስቃይ ላይ ለሚገኝ የአካባቢያቸው ሕዝብ የዕለት እንጀራን በማቅረብ ተስፋቸው ይሆናል ብለዋል። 

07 July 2020, 17:03