ፈልግ

የሐምሌ 05/2012 ዓ.ም ዘክረምት 2ኛ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ የሐምሌ 05/2012 ዓ.ም ዘክረምት 2ኛ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ  

የሐምሌ 05/2012 ዓ.ም ዘክረምት 2ኛ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.    2ኛ ጢሞ 4፡ 1-22

2.   2ጴጥ 1፡ 12-18

3.   ሐዋ 23፡10-35

4.   ሉቃ 6፡1-19

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የሰንበት ጌታ

በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኀብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካካል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። ሰዎቹ ግን በቊጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ

ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፤ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።

የቡራኬና የወዮታ ስብከት

ኢየሱስም አብሮአቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፣ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር (ሉቃስ 6፡1-19)።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እግዚአብሔርን መምሰል የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል በሚል ልዩ ምክር ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞ 4፡8 ላይ ያለውን ይተርክልናል፣ በተጨማሪም ይህ ቃል የታመነና ሁሉም ሰው ሊቀበለው እንደሚገባ ያስተምረናል። ይህንንም በማድረግ በሰላም፣ በፍቅር፣ በቃልና በኑሮ በእምነትና በንጽህና ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ክርስቲያናዊ ጉዞአችንን በትጋት እንድንቀጥል ይመክረናል። እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን “የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምጽ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን ብሎ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛው መልዕክቱ በምዕራፍ 1፡17-18 ላይ ያለውን ሲነበብልን ሰምተናል ለዚህ ጥሪም ምላሽ እንድንሰጥ ተጋብዘናል፡፡

ቃሉን በጥሞና እንድናዳምጥና የሕይወታችን መመሪያ እንድናደርገው በቅዱስ መንፈሱ ያነቃቃናል። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ስለ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወይም ሐዋርያት መጠራት መሾምና ለስብከተ ወንጌል ትምህርት መላካቸውን ይተርክልናል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከው” ዮሐ 3፡16 ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንደተናገረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው የሰውን ልጅ በትምህርቱ በተአምራቱና በሞቱ ለማዳን እንደ ሆነ ያስረዳናል። የማዳን ስራውን የጀመረውም የሰውን ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የሚያወጣውን የቅዱስ ወንጌል ቃል “የእግዚአብሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ በወንጌልም እመኑ” ማር 1፡15 እያለ በማስተማር ነበር። ወንጌልን የማስተማር ስራ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለማካሄድ ለሰው ልጆች የሕይወት መመሪያ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋርና እርሱም ከዐረገ በኃላ ይህን ስራ በምድር ላይ የሚያስቀጥሉ ደቀ መዛሙርትን መምረጥ ማሰልጠንና እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ መላክ ነበረበት፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው ደቀ መዛሙርት በዓሣ ማጥመድ በግብርና ሥራ በቀረጥ መሰብሰብ በመሳሰሉ የሥራ መስክ የተሰማሩ ስለነበሩ ዓሣ አጥማጆች የነበሩትን ጴጥሮስንና እንድሪያስን ያዕቆብና ዮሐንስን “ከኃላዬ ተከተሉኝ ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኃለሁ” ማር 1፡17-20 እያለ ነበር፡፡ ይህ አባባል ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣውና ደቀ መዛሙርቱን የመረጠው የሰውን ልጅ የፍቅር የሰላም የእምነት የተስፋ የበጎነትና የርኅራኄ ምንጭ በሆነው በወንጌል ቃል ለመያዝና ለመምራት መሆኑን በግልጽ ስለሚያመለክት በእውነት ዓሳ በመረብ እንደሚሳብ በፍቅር የሚስብ አነጋገር ነው፡፡

እኛም የጌታን ዝናና አለኝታነት ለሌሎች እንድናበስር ተጠርተናል፣ እያንዳንዳችን ደቀ መዝሙሮች ነን፣ በዛሬው ማህበራዊ ኑሮአችን የጎደለብን የክርስቶስ ፍቅር ለማወጅ የተጠራን ደቀ መዝሙሮች ነን፣ ታዲያ ይህ ፍቅር ወሰን ወገን ጎሳና ዘር የለውም፡፡ ሁሉንም በአንድ በመመልከት ለዚህ ፍቅር መጋበዝ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ወንጌልን እንዴት እንደሚያስተምሩ ሕሙማንን እንዴት እንደሚፈውሱና መከራም ሲደርስባቸው በጥበብ እንዲያሳልፉ በትዕግስትና በትህትና እንዲያስተምሩ አሰልጥኖአቸዋል፡፡

በእውነት ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ይህን መመሪያ በትክክለኛ ሁኔታ በተግባር ተርጉመውታል። እኛም በጌታችን ስም የሚደርስብንን መከራ እስከ መጨረሻ ለመታገል ጥበቡን እንዲለግሰን ልንማጸነው ይገባል። ልክ ደቀ መዛሙርቱን ወንጌልን እንዲያስተምሩ ወደጠፉት በጎች ወደ እስራኤል እንዲሄዱ እንደ መከራቸው ሁሉ እኛም በአካባቢያችን በቀዬአችን በፍቅር በአንድነት በህብረት በመተሳሰብ በመተባበርና በመተጋገዝ መኖር ያልቻሉትን በቃሉ አማካኝነት አጥምደን ወደ ፍቅር መረብ እንዲገቡ ወደ ህብረቱም እንዲመጡ በመጋበዝ ለማስተማር ነው ለዚህ እያንዳንዳችን ሃላፊነት አለብን፡፡

ወደ ጠፉት በጎች የሚለው ሐረግ በእውነት ሊተኮርበት የሚገባ ነው። ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ከሙሴ ጀምሮ በየጊዜው ነቢያትን እያስነሳ ሲያስተምራቸው የዓለም መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ እስራኤላዊት ከሆነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሕሙማንን እየፈወሰና እንደ አልአዛር ያሉ ሙታንን እያስነሳ አስደናቂ ተአምራቱን ሲያሳያቸው የዓለም ቤዛ መሆኑን አምነው ሊቀበሉት ባለመቻላቸው እውነትም የጠፉ ናቸው፡፡ ጌታችን ግን እንደ እስራኤል ያለ ብዙ ሕዝብ ይቅርና አንድ ስው እንኳን እንዲጠፋበት አይፈልግም፡፡ ለዚህ ነው በሉቃስ ወንጌል 15፡1-31 የተነገሩ ሶስት ምሳሌዎች ማለትም 1ኛ/ መቶ በግ ያለው ሰው አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ትቶ አንዱን ሊፈልግ የሄደውን ሰው ምሳሌ፥ 2ኛ/ ዐሥር ብር ያላት ሴት አንዱ ቢጠፋባት አጥብቃ እንደምትፈልገው፥ 3ኛ/ ሁለት ሌጆች ያሉት አባት አንዱ ጠፍቶ ከቆያ በኋላ ተመልሶ ሲመጣ እንደተደሰተ፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሦስቱ የጠፉባቸውን ሲያገኙ ደስ እንዳላቸው እንደዚሁ የጠፉት እስራኤላውያን እንዲመልሱ እና እንዲድኑ ፈልጎ ነው ደቀ መዛሙርቱን ወደ እነርሱ የላካቸው፡

አስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ጠፉት በጎች ወደ እስራኤል የተላኩት ልክ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ እያሉ እንዲያስተምሩ ነበር፡፡ በእርግጥ መንግስተ ሰማይ በክርስቶስ ሕይወት ወደ ምድር መጥታለች፡፡ ሐዋርያትም ይህን ሕይወት ለመኖር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሌሎችም ይህን ሕይወት እንዲኖሩ አስተምረዋል፡፡ ይህ ሕይወት የሚገኝበትን አራቱ ወንጌላትን፡ የሐዋርያት ሥራና መልእክታትን ጽፈውልን አልፈዋል፡፡ የወንጌል ሰባኪያንም ሁልጊዜ ሲያስተምሩ የሚያስተላልፉት መልእክት ሰዎች ይህን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት እንዲኖሩ ነው፡፡ እኛም የተጠራነው ለዚሁ ነው፡፡

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ሥራ ቃሉን በመስበክ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በሥራቸው ሕሙማንን መፈወስ፡ ሙታንን ማስነሳት ለምጻሞችን ማንጻት አጋንንትን ማውጣት ነበር፣ ሥልጣን የሰጣቸው እርሱ ነውና፡፡

በመጨረሻም የዓለም ቤዛ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ በኃላ ወንጌልን እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ በመሄድ እንዲያስተምሩ ለመረጣቸው ደቀ መዛሙርት ሥልጣን ሲስጥ ይህ ሥልጣን የሚያስከትለውን ኃላፊነት በማሳወቅ ነበር፡፡ ከዚህም ኃላፊነት ዋናውና ወሳኙ በእርሱ ምክንያት እንደሚጠሉ በግልጽ በማስረዳት የሚደርስባቸውን ችግር ግርፋትና ሥቃይ በጽናት ችለው ወንጌልን እየሰበኩ በብቃት በመወጣት ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በዘመናቸው የተቻላቸውን ካስፋፉ በኋላ ለተከታዮቻቸውም ሁሉ እንደዚሁ ተመሳሳዩን ድርጊት በትጋት በመፈጸማቸው እነሆ የመንግሥተ እግዚአብሔር ማስፋፊያ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓለም ላይ ከጸረ ክርስቶስ ኃይሎች ጋር በመታገል ላይ ትገኛለች፡፡

ለዚህ ሥራ ሁላችንም ተጋብዘናል፣ ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚረዳን ኃይል ክርስቶስ ትቶልናል እርሱም ሥጋውና ደሙ ነው፣ ዘወትር በመስዋዕተ ቅዳሴአችን እናገኘዋለን፣ ስለሆነም በእርሱ ተመርተን የመንግስቱን ሥራ እንድንስራ በጸጋው ይደግፈን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን። አሜን!

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

11 July 2020, 17:27