ፈልግ

ለምን ጸሎታችንን አይሰማም? ለምን ጸሎታችንን አይሰማም? 

ለምን ጸሎታችንን አይሰማም

“ጸሎት አድርገን እግዚአብሔር አልሰማንም፣ ለምን አልሰጠንም፣ ስለዚህ ለማይሰማን ነገር ለምን ደጋግመን እንጸልያለን?” እያልን ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ እናጉረመርማለን። ጸሎታችን የማይሰማው እግዚአበሔር ይመስለናል፣ ጥሩ ጸሎት ያደረግንም ይመስለናል። ስለዚህ ሐሳብ ቅዱስ ያዕቆብ ሲናገር “ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና” (ያዕቆም 4፡3) በማለት ይናገረናል። ጸሎታችን ያለ ፍሬ የሚቀረው በበደላችን እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ 

“ለምናችሁ ያለተሰጣችሁ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና”  የሚለውን ቃል ቅዱስ አውጉስጢኖስ ሲተረጉመው “ክፉ ስለሆናችሁ፣ ክፉ ስለለመናችሁ፣ በክፉ ስለለመናችሁ ነው ያልተሰጣችሁ” ይለናል፡፡

ክፉ ስለሆናችሁ፣ በኃጢአት የምንመላለስ ከሆነ እግዚአብሔር አይሰማንም። ምክንያቱም ኃጢአተኛ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ወይም ወዳጅነት የለውም። ነገር ግን እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አይጠላም፤ ይልቁንም ይወደዋል፡፡ ተጸጽቶ ኃጢአቱን በንስሐ አስወግዶ ወደ እርሱ እንዲመለሰ ይጠብቀዋል፣ ከሌላውም በይበልጥ ይፈልገዋል። ከልባችንም ተጸጽተን ብንመለስና ብንለምነው ይሰማናል፡፡ ንጉሥ አንጥያኮስ መዓት ከወረደበትና በተቆጣ በኋላ ክፋቱንና ኃጢአቱን ሳይተው መንገዱን ሳየቀየር እግዚአብሔር እንዲምረው ለመነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ልቡን ተመልክቶ አልሰማውም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱን ሊያስወግድና ከክፋቱ ሊወጣ ሊርቅም ፈጽሞ አልፈቀደም ነበር፡፡ በሆኑም በንጹሕ መንፈስ አይለምንም ነበር፤ ስለዚህ ልመናው ፍሬ አልባ ሆኖ ቀረ፡፡

ክፉ ስለለመናችሁ፣ ብዙ ጊዜ ጸሎታችን የማይሰማው ልመናችን ለመንፈስ የማይጠቅም ወይም የሚጐዳ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ነው፡፡ በአብዛኛው እኛ የምንለምነው ሥጋዊና ምድራዊ ሀብት፣ ገንዘብ፣ ጤና፣ ክብር ሹመት እንዲሁም ከሚመጣብን መከራ እንድንድን እንለምናለን፡፡ በሥጋ ዓይን ተመልክተን መልካምና አስፈላጊ የምንለው ነገር በአንጻሩ በአግዚአብሔር ፊት ክፉና የማያስፈልገን ሊሆን ይችላል፡፡

በክፉ ስለለመናችሁ፣ ጸሎት ማድረግ ወይም መለመን ሰለማንችል ነው፡፡ ኢየሱስ ሐዋርያቱን «አባቴን እስካሁን በስሜ አልለመናችሁትም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ በስሜ ብትለምኑ ይሰጣችኋል´ (ያዕ. 4፣3) አላቸው፡፡ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት ጠበቃችን እና አማላጃችን ነው፡፡

ይህንንም ቤተክርስቲያን ስለምታስምረን “በአንድ ልጅህ … በተወደደው ልጅህ … በኢየሱስ ክርስቶስ …” እያለን ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር እንድናደርስ ትነግረናለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጸሎታችንን በእምነትና በትሕትና እንድናቀርብ ያስፈልጋል፡፡ ምኞታችንና ፈላጐታችን ከእግዚአብሔር መስማማት አለበት፡፡ ስንጸልይ “ይህን የምንለምነውን ፈቃድህን ከሆነ ሰጠን” ማለት ይገባናል፡፡ ካልተሰማልን ደግሞ ሳይሰለቸን ደግመን ደጋግመን በመንፈሳዊነት በትሕትናና በእምነት እንለምን በአጭር ጊዜ እንደሚሰማን አድርገን አንጸልይ።

20 July 2020, 12:56