ማሪያም መግደላዊት
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ሐምሌ 15/2012 ዓ.ም የመቅደላዊት ማርያም አመታዊ በዓል በመከበር ላይ የገኛል። ከሁሉም አስቀድማ ኢየሱስ ከሞት ተነሥቶ ያየችው እና የትንሣኤውን የምሥራች ለሌሎች ያበሰረች መግደላዊት ማርያም ናት፡፡ ኢየሱስ ለእርሱ ለነበራት ፍቅር ሊክሳት ፈልጐ ለእርስዋ ተገለጠላት። መግደላዊት ማርያም ኢየሱስ ከሙታን ይነሣል ብላ ሳይሆን እንደ አይሁዳውያን ልማድ በሬሳው ሽቶ ለመቀባት ብላ ነበር የሄደችው፡፡ ነገር ግን እዚያ እንደ ደረሰች ደስታዋ የነበረ ኢየሱስ ተነሥቶ ጠበቃት፤ ዘለዓለም አላየውም ብላ ተስፋ ቆርጣ ነገር ግን አገኝችው፡፡
ማርያም መግደላዊት በማለዳ ወደ ኢየሱስ መቃብር ሄደች፡፡ መቃብሩ ላይ ተከድኖ የነበረው ድንጋይ ተንከባሎ ጠበቃት፡፡ ከእርስዋ ጋር ደግሞ ሌሎች ሴቶች ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ተገንዘቦት የነበረው የከፈኑን ጨርቅ መቃብሩ ውስጥ በአንድ በኩል አገኙት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስም ለማየትና ለማረጋገጥ እየሮጡ መጥተው ነበር፡፡ ከማርያም መግደላዊት በቀር መቃብሩ ባዶ ሆኖ ስላገኙት በምን ምክንያት እንደሆነ ሳያረጋግጡ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
እርስዋ ግን ብቻዋን እዚያ ቀረች፡፡ የኢየሱስን ሬሳ ስላጣች ቁጭ ብላ ታላቅስ ነበር፡፡ ያጠፉት ወይም የወሰዱት መሰላት በማልቀስ ላይ ሳለች ሁለት መላክት አየች አንዱ በመቃብሩ ግርጌ ሌላው ደግሞ በራስጌ ቁጭ ብለው ነበር፡፡ «አንች ሴት ስለምን ታለቅሽያለሽ?´ ሲሉ ጠየቁዋት፡፡ እርስዋም «ጌታዬን ወሰዱት ወዴት እንዳደረጉት አላወቅሁም´ አለቻቸው፡፡ ይህን ተናግራ ዞር ስትል ኢየሱስ ቆሞ አየችው፡፡ ነገር ግን አላወቀችውም፡፡ ኢየሱስም «አንች ሴት ስለምን ታለቅሽያለሽ?´ ብሎ ሲጠይቃት እርስዋ አትክልት ሠራተኛ መስሏት «ጌታ ሆይ አንተ ወስደውኸው እንደሆነ የት እንዳለህ ንገረኝ´ አለችው፡፡ እርሱም «ማርያም´ ብሎ ጠራት፡፡ እርስዋም ደግሞ «መምህር ሆይ´ ብላ እግሮቹን ለመሳም ተንበርክካ ስትጠጋው «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና አባታችሁ ወደ አምላኬና አምላካችሁም አርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው´ አላት፡፡ ማርያም መግደላዊት ተደስታ በፍጥነት ወደ ሐዋርያት ሄደች፡፡ ኢየሱስም በእውነት እንደተነሳ አበሰረቻቸው(ዮሐ. 20፣1-18)፡፡
እዚህ ላይ ማሰብ የሚገባን የኢየሱስን መነሣት ብቻ አይደለም የእርስዋን ታላቅ ፍቅር ኢየሱስን ሁል ጊዜ መፈለጓንም ማየት አለብን፡፡ ኢየሱስ በሕይወቱ እያለ እስሰዋ ታፈቅረውና በትጋት ትከተለው ነበር፡፡ ከኢየሱስ ሌላ ምንም አትፈልግም ነበር፡፡ ኢየሱስ የልቧ ምኞትና ፍላጐት ነበር፡፡ የልቧም ደስታ እርሱ ብቻ ነበር፡፡ ራሱ ኢየሱስም ብዙ እንደምታፈቅረው ሲመሰክር “ብዙ ስላፈቀረችው ብዙ ኃጢአት ተትቶላታል” (ማቴ 27፣55፣ማር. 15፣40፣ሉቃ. 8፣12 ) ብሏል፡፡
ይህች ሴት በፊት እውቅ ኃጢአተኛ ነበረች፡፡ በዚህ ክፋ ሥራዋ ነበር በኢየሱስ እግር ሥር ወድቃ በልቧ ተጸጽታ ብዙ አንበታ ከኢየሱስ “ኃጢያትሽ ተሰርይቶልሻል” (ሉቃ. 7፣47) የሚል የምሕረት ቃልን ስትሰማ ሕይወቷ ተለወጠ፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከኃጢያት ወደ ጽድቅ ተሸጋገረ፡፡ መጀመሪያ በኃጢአት ተጠምዳ ነበር በኋላ ግን በኢየሱስ ፍቅር ተጠመደች፡፡ ዓለምን ናቀች በጥብቅ አስሮ ይዟት የነበረውን የሰይጣን ሰንሰለት በጣጥሳ ጣለችው፡፡ ከታላቅ ኃጢአተኛነት ወደ ታላቀ ቅድስነት ተሻገረች፡፡ ኢየሱስ እንዴ ካገኘችው በኋላ እስከ መጨረሻ ድረስ ተከተለችው፡፡ «ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት አልተወውም” (መኃልየ መኃልይ 3፣4) በማለትቀ እስከ ሞቱ ድረስ ተከተለችው፡፡ ሞቶም አልረሳችውም፡፡ «ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና” (መኃልየ መኃልይ 8፣6) ይላል መኀልየ መኀልይ፡፡
ታላቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ “በኃጢአት ቀዝቅዛ የነበረች በኋላ በፍቅር እየተቃጠለች ሄደች፡፡ ሁሉም ሐዋርያት ከመቃብሩ ሲመለሱ እርስዋ ብቻዋን እዚያ ቀረች፡፡ ያጣችውን ልታገኝ ቆየች፣ እያለቀሰች ፈለገችው የወሰዱት መስሏት በፍቅሩ ተስባ ትፈልገው ነበር´ እያለ ይናገርላታል፡፡
ማርያም መግደላዊት በኢየሱስ ፍቅር እንዴት እንደተቃጠለች እንመልከት፡፡ ሕይወታችንን ከእርስዋ ጋር እናነጻጽረው፡፡ እኛ እንደ እርስዋ ኢየሱስን እንወደዋለን ወይ? ከሁሉም አብልጠን እንከተለዋለን ወይ? በሙሉ ልባችን እናገለግለዋለን ወይ? እንደ እርስዋ ዋና ሐሳባችንና ፍቅራችን ኢየሱስ ነውን? የልባችን ምኞችና ደስታ እርሱ ነውን? የጠፋብን እንደሆነ ከልባችን አዝነን በፍጥነት ተጸጽተን እንፈልገዋለን? እንደማሪያም መግደላዊት ጽናት አለንን? እርስዋ ክፋ ተግባሯን በቆራጥነት ትታ ከነበረችበት የኃጢአት ኑሮ ብድግ ብላ ተነስታ ቅድስት ሆነች። እኛም ከክፋ ተግባራችን፣ ዝንባሌያችን እንደዚህ ወስነን እንነሳለን ወይ? እንግዲህ የዛለ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲበረታ በእውነት እንጠንከር፣ ሕሊናችንን እንመርምር፡፡
አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን