ፈልግ

ማንም ሰው ከሚወደን በላይ እግ/ሔር አባታችን ይወደናል ማንም ሰው ከሚወደን በላይ እግ/ሔር አባታችን ይወደናል 

ማንም ሰው ከሚወደን በላይ እግ/ሔር አባታችን ይወደናል!

አባታችን ሆይ ክፍል ስምንት

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

“አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን አስተምህሮ ዛሬም እንቀጥላለን።  የእያንዳንዱ ክርስቲያን ጸሎት የሚጀምረው ምስጢራዊ በሆነ መልኩ የእግዚአብሔርን አባትነት በመግለጽ ነው። የእግዚአብሔር አባትነት ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ወላጆቻችንን በማሰብ፣ ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት “ጥርት ባለ መልኩ” እና ግልጽ በሆነ መንገድ ማወቅ ይኖርብናል። ይህንንም በተመለከተ ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁጥር 2779 ላይ እንዲህ ይላል የልቦቻችን ንጽሕና ከግላዊ እና ባሕላዊ ታሪክ በሚመነጭና  ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት  አቅጣጫ በመወሰን ከአባትነት ወይም እናትነት ምሳሌዎች ጋር የተያያዘ ነው” ይለናል።

ማናችንም ብንሆን ፍጹም የሆኑ ወላጆች አልነበሩም፣ እኛም ብንሆን በተራችን ፍጹም የሆንን ወላጆች ወይም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ልንሆን አንችልም። ማነኛውንም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት የምንመሰርተውና የምንኖረው  የእኛን አቅም ውስንነት እና የራስ ወዳድነት መንፈስ ከግምት ባስገባ መልኩ በመግለጽ ሲሆን በዚህ ምክንያት የተነሳ እነርሱን የግላችን አድርገን ለመያዝ ወይም ሌሎችን ለመጫን በሚፈልጉ ምኞቶች የተበከሉ ናቸው። ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ የፍቅር መግለጫዎች ወደ ቁጣ እና ጥላቻ የሚቀየሩት።

ለዚያም ነው ታዲያ እግዚአብሔር "አባት" መሆኑን በምንነጋገርበት ወቅት የእኛን መልካምነት ይመኙልን የነበሩትን የወላጆቻችንን ምስል በማሰብ ከዚያ ባሻገር መሄድ የሚገባን በዚሁ ምክንያት ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር እኛ "በሰማያት ያለኸው" አባታችን በማለት ኢየሱስ እንድንጠቀምበት የሚጋብዝ አገላለጽ ነው። ይህ ፍቅር ደግሞ ፍጽምና ወይም ምልአት ያለው እኛ በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የጎደለን ዓይነ ፍቅር ነው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለዘለዓለም ለመወደድ የሚያስችላቸውን ቦታ ለማግኘት ተግተው እየፈለጉ የሚገኙ ቢሆኑም ቅሉ፣ ነገር ግን ይህንን ፍቅር አለጋኙትም። በዓለማችን ውስጥ እጅግ ብዙ የሚባሉ ጓደኝነቶች እና ፍቅሮች ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ እንደ ሚገኙም ይታወቃል።

የእኛ ፍቅር ደካማ መሆኑን ለማሳየት በማሰብ ነቢዩ ሆሴዕ ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና” (ት. ሆሴዕ 6:4) በማለት የተናገረውም በዚሁ ምክንያት ነው። የእኛ ፍቅር ብዙን ጊዜ እንዲህ ነው - ጠብቀን ለመቆየት የሚያስቸግረን ቃል ኪዳን፣ ቶሎ የሚመጣ እና ከዚያን ቶሎ በኖ የሚጠፋ ዓይነት ፍቅር፣ ልክ ጠዋት ፀሐይ ስትወጣ ማታ የነበረውን ጠል በፍጥነት እንደ ሚያስወግድው የእኛም ፍቅር ብዙን ጊዜ እንዲሁ ይሆናል።

እኛ ሰዎች በሕይወታችን ዘመን ስንት ጊዜ ነው በዚህ ዓይነት ደካማ እና ተቆራራጭ በሆነ መልኩ የወደድነው? ለመውደድ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን ወዲያው ድክመቶች እና ውስንነቶች ያጋጥሙናል፡ በጸጋ ዘመን ውስጥ በነበርንበት ወቅት ገቢራዊ ለማድረግ ቀላል መስሎ ታይቶን የነበረውን ቃል ኪዳን ለመጠበቅ አቅሙ ያንሰናል። እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንኳ ሳይቀር በዚህ ረገድ ፈርቶ እና ሸሽቶ ሄዶ ነበር። ከመጀመሪያው የሕይወት ዘመናችን ጀምሮ በጉዞዋችን ላይ ስንፈልገው የነበረውን ታላቅ እና ውድ የሆነ ሀብት ፍቅርን ሙሉ በሙሉ ማግኘት ተቸግረን እርሱን እየፈለግን እንኖራለን።

ይሁን እንጂ ከዚህ ለየት ያለ “በሰማይ የሚኖር አባታችን” ፍቅር አለ። ይህ ፍቅር ለሁሉም የሰው ልጆች ተደራሽ መሆኑን ግን ማንም ሊጠራጠረው አይገባም። እናት እና አባቶቻችን እኛ በምንፈልገው መጠን በሚገባ ወደውን የነበረ ባይሆንም እንኳን በሰማይ የሚኖረው እግዚአብሔር በዚህ ምድር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሊወዱን ከሚችሉት በላይ የሚወደን እግዚኣብሔር በሰማይ ይገኛል። በዚህም ረገድ ነቢዩ ኢሳያስ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን በፍጹም አረሳችሁም። እነሆ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጫችኋለሁ” (ት. ኢሳያስ 49፡15-16)። ሁሉም ምድራዊ የሆኑ ፍቅሮቻችን ቢደናቀፉ እና በእጃችን ላይ ከአቧራ በቀር ምንም ነገር ሳይቀር በኖ ቢጠፋ እንኳን ሁል ጊዜም ቢሆን ለእኛ የሚሰጥ ልዩ እና ታማኝ የሆነው የእግዚኣብሔር ፍቅር አለ።

በፍቅር ረሃብ ውስጥ ሁላችንም የምንፈልገው ያልተፈጥረውን ነገር ሳይሆን ይልቁንም አባት የሆነውን  እግዚኣብሄር የማወቅ ግብዣ ነው። ለምሳሌ ያህል ቅዱስ አጎስጢኖስ የመጣው መንፈሳዊ ለውጥ በዚሁ መንገድ ነበር የተከሰተው፣ ወጣቱና ብሩህ የንግግር ችሎታ የነበረው አጎስጢኖስ በፍጥረታት መካከል ምንም ዓይነት ፍጡር ሊሰጠው ያልቻለውን ነገር ፈለገ፣ አንድ ቀን ግን እይታውን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ የማየት ብርታት አገኘ። በዚያን ቀን እግዚኣብሔር መሆኑን አወቀ።

"በሰማያት ውስጥ" የሚለው አገላለጽ ርቀትን ለማሳየት የተቀመጠ አገላለጽ ሳይሆን ነገር ግን ሥር ነቀል ልዩነት ያለው ሌላ ገፅታ መኖሩን ለማሳየት የተቀመጠ ነው።

ስለዚህ መፍራት የለብንም! ማንም ሰው ቢሆን ብቻውን አይደለም። በምድር ላይ ያለው አባትህ በችግርህ ምክንያት የረሳህ ቢመስልህና በዚህ የተነሳ አንተ በእርሱ ቅር የተሰኘህ ብትሆንም የክርስትና እምነትን መሠረታዊ ልምድ ግን አልተነፈገህም፣ ይህም አንተ በጣም ተወዳጅ የሆንክ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህ ነው፣ በሕይወት ውስጥ እርሱ ለአንተ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ሊያጠፋ የሚችል ምንም ነገር የለም።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 13/2011 ዓ.ም “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

 

09 July 2020, 15:41