ፈልግ

“ምግብ ከሁሉም ጋር እንድንጋራው እግዚአብሔር የሰጠን ስጦታ ነው!” “ምግብ ከሁሉም ጋር እንድንጋራው እግዚአብሔር የሰጠን ስጦታ ነው!” 

“ምግብ ከሁሉም ጋር እንድንጋራው እግዚአብሔር የሰጠን ስጦታ ነው!”

አባታችን ሆይ

ክፍል አስራ አንድ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት የጠቅላላ አስተምህሮአችን እኛ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ይሰጠን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የምናቀርበውን፣ "አባታችን ሆይ!" በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ሁለተኛውን ክፍል እንመለከታለን። ይህም በዚህ ጸሎት በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የሚገኝ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያለውን “እንጀራ” ስጠን በሚለው ቃል ይጀምራል።

ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት የሚጀምረው አስገራሚ የሆነ ጥያቄን በማቅረብ ነው። እሱም "የዕለት እንጀራችን ስጠን!" በማለት አንድ ለማኝ ሰው ከሚያቀርበው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በዚህ ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ይህንን አውድ ብዙን ጊዜ እንረሳለን። ይህም እኛ እራሳችንን የማንችል ፍጥረቶች መሆናችንን እና በየቀኑ ራሳችንን በራሳችን አቅም ብቻ መመገብ እንደማንችል እንዘነጋለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ሥፍራዎች እንደተጠቀሰው ብዙ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት የሚጀምረው ከአንድ ጥያቄ ነው። ኢየሱስ ጥርት ያለ ጥያቄዎችን አይጠይቅም። ይልቁንም የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ስብዕና ተጨባጭ በሆነ መልኩ እና በዕለት ተዕለት ችግሮች ውስጥ የሚከሰቱ ክስተቶች ሁሉ ጸሎት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ነፃነት እና ደህንነትን የሚጠይቁ ብዙ ለማኞች ይገኙበታል። አንዳንዱ እንጀራ ይለምናል፣ አንዳንዱ ፈውስን ይጠይቃል፣ አንዳንዱ መንጻትን ይሻል፣ አንዳንዱ ሕይወት እንዲሰጠው ይለምናል፣ ወይም ደግሞ አንድ እርሱ ወይም እርሷ የሚወደው ሰው በሕይወት ይኖር ዘንድ ይማጸናል . . . ኢየሱስ እነዚህን ጥያቄዎች እና እነዚህን ሁሉ ህመሞች ቸል ብሎ አልፏቸው በፍጹም አያውቅም። ስለዚህም ነው ኢየሱስ የዕለት እንጀራ እንድንጠይቅ ያስተማረን። ይህንን ጸሎት ከብዙ ወንዶችና ሴቶች ጋር አብረን በጋራ እንድናደርግ የሚያስተምረን ይህ ጸሎት ዘወትር የሚደረገው ሁል ጊዜም በውስጣችን ከሚጋጨው ጭንቀት ጋር አብሮ የሚመጣ ጩኸት በመሆኑ የተነሳ ነው። በዛሬው ጊዜ ለልጆቻቸው በቂ ዳቦ ባለመያዛቸው የተነሳ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ እናቶች እና አባቶች ስንት ናቸው? ይህን ጸሎት አስተማማኝ በሆነ አፓርታማ ውስጥ ሆነን ሳይሆን በአንድ በከፍተኛ ሁኔታ ብዙ ነገሮች በሚጎሉበት ሥፍራ ሆነን እንደምንጸልይ አድርገን እንውሰድ። የኢየሱስ ቃላት አዲስ ጥንካሬን ይሰጣሉ። የክርስትና ጸሎት በዚህ መልኩ ይጀምራል። የሚጀምረው አንድ የመነነ ሰው በሚኖረው ዓይነት የሕይወት ተመክሮ አይደለም። የሚጀምረው ከእውነታ ነው፣ ከተቸገሩ ሰዎች ልብ እና አካል፣ ወይም ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከጎደሏቸው ሰዎች ልብ የሚመነጭ ጸሎት ነው። በከፍተኛ ደረጃ በክርስቲያናዊ ምሥጢራት የተደገፈ መንፈሳዊ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ የዚህን ጥያቄ ቀላልነት ችላ ሊሉት አይችሉም። “አባት ሆይ ለእኛ እና ለሁላችን አስፈላጊ እና በቂ የሆነ እንጀራ ስጠን”። “እንጀራ” የሚለው ቃል ውሃን፣ መድኃኒትን፣ ቤትን፣ ሥራን . . .ወዘተ ያጠቃልላል።

አንድ ክርስቲያን በጸሎቱ አማካይነት እንዲሰጠው የሚጠይቀው እንጀራ “ለእኔ” ብሎ ሳይሆን ነገር ግን “ለእኛ” በማለት ነው። ኢየሱስ የፈለገው በዚህ መንገድ እንዲደረግ ነው። ለእራሳችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ፍጥረት ሁሉ እንጀራን እንድንጠይቅ ያስተምረናል። በዚህ መንገድ ካልጸለይን "አባታችን" ሆይ የሚለው ጸሎት የክርስቲያኖች ጸሎት መሆኑ ያከትማል። እግዚአብሔር አባታችን ከሆነ፣ እጃችንን ይዞ እርሱ ካልወሰደን በቀር በራሳችን ኃይል ብቻ እንዴት በፊቱ ለመቅረብ እንችላለን? እርሱ የሰጠንን የምንበላውን እንጀራ እርስ በእርሳችን የምንሰራረቅ ከሆነ እንዴት ነው እኛ የእርሱ ልጆች ነን ለማለት የምንችለው? ይህ ፀሎት የሌሎችን ስሜት የሚረዳ እና እርስ በእርስ የመተሳሰብ ስሜትን በከፍተኛ ደረጃ አቅፎ ይዟል። በእኔ ረሃብ ምክንያት የብዙኃኑ ረሃብ ይሰማኛል፣ እናም ጥያቄዎቻቸው መልስ እስኪያገኙ ድረስ ጸሎቴን ወደ  እግዚአብሔር ማቅረቤን እቀጥላለሁ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ማኅበረሰቡን፣ ቤተ ክርስቲያኑን በአጠቃላይ ሁላችንንም የሚያስተምረው የሁሉንም ፍላጎቶች ወደ እግዚአብሔር እንድናቀርብ ነው፡ “አባት ሆይ! እኛ ሁላችን የአንተ ልጆች ነን፣ ይቅር በለን!”።

በጸሎት አማካይነት ጌታ እንዲሰጠን የምንጠይቀው እንጀራ አንድ ቀን እኛን ይከሰናል። በአካባቢያችን ላሉት ሰዎች የማጋራት ልምድ የሌለን ከሆነ ይወቅሰናል። ለሁሉም የሰው ልጆች የተሰጠ እንጀራ ነው፣ በምትኩ ግን አንድ ሰው ብቻውን እየበላው ነው፣ ፍቅር ደግሞ ይህንን መቋቋም በፍጹም አይችልም።

በአንድ ወቅት በኢየሱስ ፊት ብዙ የተራቡ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ ማንኛውም ሰው አንዳች የሚበላ ነገር መያዝ አለመያዛቸውን ጠየቀ። አንድ ወጣት ልጅ ያለውን ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ፣ ያለውን ለማካፈል ያልሰሰተ፣ ለሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሳ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አንድ ወጣት አገኘ። ኢየሱስ ይህንን በደግነት የተሰጠውን ገጸበረከት ለሁሉ እንዲበቃ አድርጎ ባረከው። ያ ወጣት ልጅ "አባታችን ሆይ! የሚለውን ጸሎት ትምህርት በሚገባ ተረድቶታል። ያም ምግብ ማለት የግል ንብረት ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።

በዚያ ቀን ኢየሱስ ያከናወነው እውነተኛ ተዓምር ካለን የማካፈል ልምድን ነው። እርሱ ራሱ ባርኮ ያቀረበው እንጀራ እራሱን በቅዱስ ቁርባን ዳግመኛ መስዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት መሆኑን አስቀድሞ ገልጾታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ቅዱስ ቁርባን ብቻ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ለማስታገስ እና የዕለት እንጀራን ለማግኘት በሚያደርገው ጉዞ ሁሉ ረሃብን ማስታገስ ይችላል።

 

ምንጭ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 18/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

30 July 2020, 10:00