ፈልግ

(ከማኅደር የተወሰደ) (ከማኅደር የተወሰደ) 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሴቶችን እና ሕጻናት ደህንነት ለማስጠበቅ በርትታ የምትሠራ መሆኑን አስታወቀች።

በኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእናቶች እና ሕጻናት ደህንነት ጥበቃ ክፍል አስታወቀ። በወረርሽኙ ወቅት በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል “ዝም አልልም” የተሰኘ ግንዛቤ መስጫ መርሃ ግብር መጀመሩን የቤተክርስቲያኒቱ ማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ አስተባባሪ፣ ሃብታሙ አብርደው የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የቫቲካን ዜና፤

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አዘጋጅነት በተካሄደው ስብሰባ ላይ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመከላከል እና ግንዛቤን በማጨበጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተባባሪ ድርጅቶች ተወካዮች መገኘታቸው ታውቋል።

የሕጻናት ደህንነት ጥበቃ መምሪያ እና የስነ-ጥበብ ባለሞያዎች ትብብር፣

አገሪቱ ውስጥ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የተመለከቱ አንዳንድ የስነ-ጥበብ ባለሞያዎች በኅብረት ሆነው “ዝም አልልም” የተሰኘ ግንዛቤ መስጫ መርሃ ግብር መጀመራቸው ታውቋል። በስብሰባው ወቅት የስነ-ጥበብ ባለሞያዎቹ ከቤተክርስቲያኒቱ ሠራተኞች ጋር በመሆን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቤት ውስጥ ቆይታ ወቅት በሴቶች፣ ወጣት ልጃገረዶች እና ሕጻናት ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ በጥልቀት በመወያየት ለችግሩ መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው ታውቋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እያደጉ መምጣታቸውን የተለያዩ መረጃዎች በተጨባች ማስረጃ ሲያመላክቱ ቆይተዋል። ከጥቃቶቹ መካከል በቅርብ የቤተሰብ አባላት በኩል የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር መኖራቸውን መረጃዎች አመላክተዋል።

ያለ ዕድሜ ጋብቻ መጨመር፣

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤት መዘጋቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያለ ዕድሜ ጋብቻ ቁጥር መጨመሩንም መረጃዎች ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የቤተክርስቲያኒቱ ተወካዮች እና ተባባሪ ድርጅቶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለማስቆም በማኅበረሰቡ መካከል ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ እና በተለይም ሕጻናትን ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል አመቺ ሥፍራን በማመቻቸት ጥበቃን ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን ተገንዝበዋል። በመሆኑም ቤተክርስቲያን እና የስነ-ጥበብ ባለሞያዎች በቅርበት ተባብረው በመሥራት፣ ችግሮችን በማቃለል  መልካም ውጤት ለማምጣት መስማማታቸው ታውቋል።

ግንዛቤን መፍጠር እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተወጣጡ እና የስነ ጥበብ ባለሞያዎች የተስማሙባቸው የሥራ ድርሻዎች፣ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅተው አውደ-ጥናቶችን በማካሄድ ግንዛቤን መፍጠር እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ወገኖች፣ ቤተሰቦች በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ እውቀት እንዲኖራቸው ለማገዝ መስማማታቸው ታውቋል። በተጨማሪም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ምዕመናኖቻቸውን በግብረ ገብ፣ በማህበራዊ እና የዕውቀት እሴቶች በመታገዝ መልካም ማኅበረሰብን ለመፍጠር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ መቅረቡ ታውቋል። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሕጻናት ጤና አጠባበቅ እና ደህንነት ጥበቃ መምሪያ ለሴቶች እና ለሕጻናት የሚሰጠውን ማኅበራዊ አገልግሎት በበላይነት ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ሃላፊነት የተሰጠው መሆኑ ታውቋል። ለመምሪያው ከተሰጡት የሥራ ድራሻዎች አንዱ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት በአገሪቱ በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ማዘጋጀት እንደሆነ ታውቋል። የስነ-ጥበብ ባለሞያዎቹም በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ እያደገ የመጣው ጾታዊ ጥቃት ይቆም ዘንድ ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል መልዕክቶችን በማስተላለፍ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ድጋፍ እንዲያደርጉ በማለት ለብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አደራቸውን አቅርበዋል።

02 July 2020, 08:13