የሐምሌ 26/2011 ዓ.ም ዘክረምት 5ኛ ሰንበት የቅ. ወንጌል አስተንትኖ
“አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!”
የዕለቱ ምንባባት፥
1. ቲቶ 3፡ 1-15
2. 1ጴጥ 4፡ 6-11
3. ሐዋ 28፡ 1-16
4. ማር 6፡ 47-56
የእለት ቅዱስ ወንጌል
ኢየሱስ በባሕር ላይ በእግሩ ሄደ
በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሎአቸው ጮኹ፤ ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሮአቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤ የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር።
በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ። ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
በቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት የዛሬው ሰንበት ሰንበት ዘክረምት 5ኛ በመባል ይታወቃል። በነዚህ ጊዜያት ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በቃሉ አማካኝነት የተለያዪ ትምህርቶችና መልዕክቶች አስተላልፎልናል በትምህርቶቹ መኖርና ወደ ተግባር መለወጥ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው፡፡ ዛሬም እንደ ወትሮው የማስተማር ስራውን ሳያቃርጥ ወደርሱ ሊያቀርበን ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ጳውሎስ ወደ ቲቶ በጻፈው መልዕክቱ ቲቶ 3፡ 1-2 ላይ እንድንገዛ እንድንታዘዝ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጅን የማንሳደብ የማንከራከር ገሮች ለሰው ሁሉ የዋህነትን የምናሳይ እንድንሆን ያሳስበናል፡፡
በ1ጴጥ 4፡ 6-11 ላይም ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር የሚያገለግልም ቢሆን እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል እያለ ይመክረናል፡፡ ይህንን ፈጽመን እንደሆንን የተዘጋጅልን ሽልማት መንግስቱን መውረስ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ተነግሮናል ታዲያ ይህ የሕይወት ጉዞ ቀላል አይደለም ብዙ ፈተና ብዙ መሰናክል አለው ነገር ግን እርሱ ከእኛ ጋር ስለሚሆንና ስለሚያግዘን ሁልጊዜ አይዞአችሁ አትፍሩ እያለ ያበረታታናል፡፡
በዛሬውም የወንጌል ክፍል የክርስቶስ ተከታይ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በጀልባ ሲጋዙ የደረሰባቸው ችግር የሚዳስስ ነው በዚህ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደርሶ አይዞአችሁ አትፍሩ ብሎ ሲያበረታታቸው እናያለን፡፡ ታሪኩም እንደዚህ ነው አንድ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያስተምር ሕሙማንን ሲፈውስና ሌሎችንም ተአምራት ሲያደርግ ከዋለ በኃላ ደቀ መዛሙርቱን ከገሊላ ባሕር ማዶ ወደ ጌንሳሬጥ በታንኩዋ ማልውትም በትልቅ ጀልባ ተሳፍረው እንዲሻገሩ አዘዛቸውና እርሱ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ጫፍ ወጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የጌታን ትእዛዝ አክብረው በታንኩዋ ወደ ባሕር ማዶ ለመሻገር ተነሡ፡፡
እንደምናውቀው በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ የረቀቁ የተለያዪ የመጓጓዣ ዘዴዎች አሉ፡ በአየር በየብስ እና በባሕር ላይ የሚደረጉ ጉዞዎች አሉ፡፡ በማናቸውም መንገድ የሚደረጉ ጉዞዎች የተለያዩ ችግሮች ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
በአጠቃላይ በማናቸውም ጉዞ የእግዚአብሔር ቸርነትና ረደኤት ካልጠበቀን ብዙ ችግርና አደጋ ይደርሳል፡፡ በተለይም የባሕር ላይ ጉዞ እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከወንጌሉ ሲነበብ እንደሰማነው የጌታችን ደቀ መዛሙርት በታንኩዋ ተሳፍረው ሲጋዙ ከባድ አውሎ ነፋስና ማዕበል ከወደፊታቸው ተነስቶ ከባድ አደጋ ላይ ሊጥላቸው እንደነበረ ሰምተናል፡፡ ጊዜው ደግሞ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ስለነበረና በዚያን ሰዓት ከአደጋ የሚታደጉ ወይም የሚረዱ ሰዎችን ማግኘተ እጅግ አስችጋሪ በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተጨንቀው ነበር፡፡ በማዕበሉ የሚረጨው ውኃ ታንኩዋይቱን ሊሞላት ስለደረሰ ታንካዋ ለመስጥም ተቃርባ ነበር፡፡ ጌታ ግን የነበሩበትን ችግር ተመልክቶ በባሕሩ ላይ በእግሩ እየተራመደ ወደ እነርሱ ቀረበ፡፡ እነርሱ ግን አላወቁትም እንደውም የባሕሩን ማዕበል ያስነሳው ምትሓት ክፉ መንፈስ መስሎአቸው ነበር በዚህም የተነሳ ፈርተው ይጮሁ ጀመር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በችግራቸው ጊዜ ደርሶ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ አትሩፍ! አላቸው፡፡ ጌታችን በችግራችን ጊዜ ሁሉ ሁላችንንም አይዞአችሁ! እኔ ነኝ አትሩፍ!” ይበለን፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ወደ ማዶ በታንኩዋ ለመሻገር የተነሱት በጌታ ትእዛዝ መሠረት ነበር፡፡ የጌታን ታእዛዝ በመፈጸም አንዳንድ ችግር እንካ ቢያጋጥመን ጌታ ስለሚደርስልን ችግር ላይ አንወድቅም፡፡ ጌታ ከችግር ሁሉ ይጠብቀናል፡፡ ብቻ በጌታ ሕግና ትእዛዝ መሠረት ለመኖር መቻል አለብን፡፡
የዚህ ዓለም ኑሮ የዚህ ዓለም ሕይወት እንደ ባሕር ላይ ጉዞ ነው እንደዚሁም ብዙ ውጣ ውረድ የሞላበት ነው ኃዘንና ደስታ የሚፈራረቅበት ነው፡፡ በዓለም ውስጥ ከሚደርሰው ችግር መከራና ውጣ ውረድ ለመዳን የምንችለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና እሱን በመማጠን ብቻ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከተከተልንና በእርሱ መንገድ ከተጉአዝን በችግራችን ጊዜ ሁሉ እርሱ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ አትፍሩ!” ይለናል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር እምነታችንን ይጽናልን! ያጠንክርልን!
ጌታችን በባሕር ላይ በእግሩ እየተራመደ ሲመጣ አይቶ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በባሕሩ ላይ እየተራመድሁ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ና!” አለው፡፡ ጴጥሮስም ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በባሕሩ ላይ መራመድ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ “እሰጥም እሆን?” በማለት ስለ ተጠራጠረና እጅግም ስለፈራ ወዲያውኑ መስጠም ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ! አድነኝ!” ብሎ ጮከ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርህ?” አለውና ወደ መርከቡ አስገባው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ታንኩዋው በገባ ጊዜ ወዲያውኑ ነፋሱ ጸጥ አለ ማዕበሉም ቆመ፡፡
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ቅዱስ ጴጥሮስ በጌታ ላይ በነበረው ጠንካራ እምነት በባሕሩ ላይ እንደ ጌታ በእግሩ መራመድ ችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን “እሰጥም እሆን?” ብሎ በመጠራጠሩ መስጠም ጀመረ፡፡ ከሚደርስብን ችግር ሁሉ ለመዳን እምነት ያስፈልገናል፡፡ በሙሉ እምነት እግዚአብሔርን መለመን አለብን፡፡ ተጠራጥረን እግዚአብሔርን የምንለምነው ልመና ውጤት አይኖረውም፡፡
በመጽሐፍ ቅዱሳችን ያቺ 12 ዓመት ሙሉ ደም ሲፈሳት ትሰቃይ የነበረችውን ሴት በቅጽበት ልትድን የቻለችው “የልብሱን ጫፍ ብቻ ብነካ እድናለሁ” ብላ በጌታ ላይ በነበራት ታላቅ እምነት ነበር፡፡ እውነተኛ እምነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ከዚህች ሴት መመልከት እንችላለን ስለዚህ እኛም በጌታ ላይ ያለን እምነት የጸና እንዲሆን የእርሱ ድጋፍ ከእኛ ጋር ነው ይህም ሁል ጊዜ በመስዋዕተ ቅዳሴ ስጋውና ደሙን በመካፈል እናገኘዋለን ታዲያ ለዚህ ታላቅ ምስጢር ስንቀርብ የታጠበ ማንነት ቅን ልቦና ይዘን የፍቅር ሰው ሆነን ልንቀርብ ይገባል በዚህ ጊዜም ጌታችን አይዞአችሁ! እኔ ነኝ አትፍሩ! እያለ ያበረታታናል፡፡ ክብር ሁሉ ለእርሱ ይሁን አሜን!!
ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛው የስርጭት ክፍል።