በሰሜን አሜሪካ ለሐይማኖት ነጻነት ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ።
የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ምዕመናን ለሐይማኖት ነጻነት በጸሎት እንዲተባበሩ ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል። ከሰኞ ሰኔ 15-22/2012 ዓ. ም. በሚቆየው የጸሎት መርሃ ግብር መላው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ምዕመናኑ በጸሎት እንዲተባበር የጳጳሳቱ ጉባኤ ጥሪውን ማቅረቡ ታውቋል። የማያሚ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ, የሐይማኖት ነጻነት ለተቀሩት ሰብዓዊ መብቶች በሙሉ ዋስትናን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው፣ ለሐይማኖት ነጻነት ለቆሙ ተቋማት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስበዋል።
የቫቲካን ዜና፤
በሰብዓዊ መብት ውስጥ የሐይማኖት ነጻነት የራሱ መሠረት እንዳለው፣ ሰብዓዊ መብት ዋስትናን የሚያገኝበት፣ ሕዝቦች በሰላም አብረው መኖር የሚችሉትም የሐይማኖት ነጻነት ሲከበር መሆኑን በሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሐይማኖት ነጻነት ተንከባካቢ መምሪያ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ አስረድተዋል።
ሐይማኖት፣ ፖለቲካ እና መብት፣
“ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም” በሚል ርዕስ ለአንድ ሳምንት በሚቆይ የጸሎት ሥነ ሥርዓት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን እንዲሳተፉ በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ አደራ ብለዋል። ዴሞክራሲያዊ አገር በምትባል አሜሪካ የሐይማኖት ነጻነት ሲጣስ፣ በክርስቲያኖች መካከል ልዩነት ሲደረግ፣ በተለይም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ የሚደረግ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እንመለከታለን በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ዌንስኪ ገልጸዋል። የፖለቲካ ታዛቢዎች እና የመብት ተሟጋቾች በአጀንዳቸው ስለ ሐይማኖት ነጻነት ቢጠቅሱም፣ ሐይማኖት የአመጽ እና የጦርነት ምንጭ እንደሆነ ይገልጹታል ያሉት ብጹዕ አቡነ ቶማስ፣ እነዚህ ታዛቢዎች ሐይማኖት የግል ምርጫ ብቻ አድረገው በመውሰድ ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን ይዘነጋሉ ብለዋል። ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ማለት የሚያስቡትን መናገር ብቻ ሳይሆን በርካታ ሃሳቦችን የሚያፈልቁ ተቋማትን ለምሳሌ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ቤተ መዛግብትን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሲቪል ማህበረሰብ የሚባሉ ሌሎች ተቋማትን የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የሐይማኖት ነጻነት “ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም” የቆመ መሆኑ ግንዛቤን እንዲያገኝ እና እምነትን በነጻነት መግለጽ የሚቻልበትን መንገድ ለሚያመቻቹ ተቋማት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስበዋል።
የሐይማኖት ነጻነት አያያዝ በሰሜን አሜሪካ፣
እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሐይማኖት ነጻነት በአገራቸው መኖሩን ያስረዱት፣ በኒው ዮርክ ከተማ “Religion for Peace” የተባለ ድርጅት ቃል አቀባይ፣ ወይዘሮ ማዳሌና ማልቴዘ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሐይማኖት ነጻነት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጠ ቢሆንም ተግናራዊ እየሆነ አይደለም ብለው የሐይማኖት ነጻነትን ለማስከበር ጥረት የሚያደርጉ ተቋማትን ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከችግሮች መካከል አንዳንዶችን የገለጹት ወይዘሮ ማዳሌና፣ ጸጥታው የተጠበቀ የአምልኮ ስፍራን ማግኘት፣ ጽንጽን በማስወረድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ የሕክምና ድርጅቶችን መቃወም አለመቻል፣ ከሃይማኖታዊ መርሆዎች ጋር የማይስማሙ አጀንዳዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች መቃወም በይፋ መቃወም አለመቻል የሚሉ እንደሚገኙባቸው አስረድተዋል። ሰሜን አሜሪካ የምትታወቅበት የሐይማኖት ብዝሃነት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ማዳሌና፣ በሰሜን አሜርካ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት፣ ችግረኞችን በመርዳት ረገድ ትልቅ የአገልግሎት ድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ እና ይህም ለአገሪቱ ከፍተኛ ሃብት መሆኑን አስረድተዋል። ወይዘሮ ማዳሌና አክለውም በአገሪቱ የሐይማኖት ነጻነት አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ ሐይማኖቶች ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እየዋሉ መምጣታቸው የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችን እያነጋገራቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
የሐይማኖት ነጻነት በሰሜን አሜሪካ ሕገ መንግሥት ጸድቆ የተቀመጠ ቢሆንም በአንዳንድ መልኩ በተግባር አለተገልጸም ያሉት ወይዘሮ ማዳሌና፣ የአምልኮ ስፍራዎችን ከሸባሪዎች ጥቃት ነጻ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ በቴክሳስ ውስጥ በአንድ የባፕቲስት ቤተክርስቲያን ላይ በተሰነዘረው የአሸባሪዎች ጥቃት የ26 ሰውች ሕይወት መጥፋቱን እና በፒትስቡርግ 11 ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ለሞት መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ከሰኞ ሰኔ 15-22/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ የጸሎት መርሃ ግብር ማውጣቱ ለካቶሊካዊ ምዕመናን ብቻ ሳይሆን የሐይማኖት ነጻነት ለሚናፍቃቸው ተቋማት በሙሉ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኝ የሐይማኖቶች ብዝሃነት ለአገሪቱ ከፍተኛ ሃብት ነው ያሉት ወይዘሮ ማዳሌና፣ ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማቱ በችግር ውስጥ ለሚገኙት ድሆች፣ ስደተኞች እና ሕሙማን ተጨባጭ እርዳታን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተው ይህን አስመልክቶ ባሁኑ ወቅት በሚኒስቴር ደረጃ ዕርዳታን የሚያሰባስብ መዋቅር በዓለም ዙሪያ መዘርጋቱንም አስታውቀዋል። በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የእርዳታ ማሰባሰብ እና ማዳረስ አገልግሎትን አስመልክቶ በተደረገው ጥናት መሠረት፣ ከፍተኛ ዕርዳታን በማሰባሰብ የሚታወቀው የነጭ ማኅበረሰብ የወንጌል አማኞች ሕብረት፣ ቀጥሎ የአይሁድ ማኅበረሰብ፣ ቀጥሎም የካቶሊክ ማኅበረሰብ እና በመጨረሻም የሙስሊም ማኅበረሰብ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የሐይማኖት ተቋማት መበራከት ለአገሪቱ ትልቅ ሃብት መሆኑ እየታወቀ፣ ነገር ግን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት መዋላቸው አግባብ አለመሆኑን የሐይማኖት ተቋማት መሪዎችን በማመን በጉዳዩ ላይ የጋራ ውይይት እንዲያደርጉ መገደዳቸውን ወይዘሮ ማዳሌና አስረድተዋል።
በአገሪቱ እያደገ የመጣውን ዘረኝነት ያስታወሱት ወይዘሮ ማዳሌና፣ በጋራ ሆነው በብርቱ መቃወም የሚገባው ማኅበራዊ ችግር በመሆኑ ማኅበራዊ ፍትህን ለማምጣት የጋራ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገው መሆኑን ተናግረዋል። ማኅበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ማድረግ ማለት በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ የተቀመጡ መንፈስዊ መልዕክቶችን በተሳሳተ መንገድ መግለጽ እንዳልሆነ ያስረዱት ወይዘሮ ማዳሌና፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ ኢፍትሃዊ ተግባራትን በሰላማዊ መንገድ መቃወም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የፍትህ እና የእኩልነት ተሟጋች የነበረው ማርቲን ሉቴር ኪንግ፣ “በሰላማዊ ተቃውሞ መካከል ድምጻቸው እንዳይሰማ የተደረጉ ሰዎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
በየቀኑ በአንድ ሀሳብ ላይ ማስተንተን፣
ከሰኞ ሰኔ 15-22/2012 ዓ. ም. በሚደረግ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ምዕመናን በየቀኑ በጸሎት እንዲተጉ፣ ለሐይማኖት ነጻነት ሲሉ የሞቱትን፣ ቅዱስ ቶማስ ሞሮን እና ቅዱስ ጆቫኒ ፊሼርን በማስታወስ፣ በጋብቻ ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል የጣሩት የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ሄንሪ ስምንተኛን እና ሰኔ 22 ቀን የሚከበረው የሮም ከተማ ባልደረባ የሆኑትን ቅዱስ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ ክብረ በዓል በጸሎት በመተባበር እንዲያከብሯቸው ጥሪ መቅረቡ ታውቋል። “ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም” በሚል ርዕስ ለአንድ ሳምንት በሚደረግ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን እንዲሳተፉ ጥሪውን ያስተላለፈው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሐይማኖት ነጻነት ሁሉንም የሐይማኖት ተቋማት እንዲያብቡ የሚያደርግ በመሆኑ የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ ሁሉም ሰው የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ በማለት አሳስቧል።