ፈልግ

የቅዱስ ልበ ኢየሱስ የመጀመሪያ ተስፋ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ የመጀመሪያ ተስፋ 

የቅዱስ ልበ ኢየሱስ የመጀመሪያ ተስፋ

«እኔ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጉአቸውን ጸጋዎች እሰጣቸዋለሁ»

ቅዱስ ልብን በታላቅ ፍቅር ተነሳስተው ሊያከብሩት ለሚመጡ ሰዎች «እኔ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጉአቸውን ጸጋዎች እሰጣቸዋለሁ» እያለ ለሕይወታቸው የሚጠቅምና ለዘለአለም ዋሰትና የሚሆን መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚሰጣቸው ያረጋግጣል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅድስት ማርጌሪታ አላኮክ ይህን ትልቅ ተስፋ ለሰው ሁሉ እንድታበስር ነገራት፡፡ ቅዱስ ልብ በፍቅራችን የተቃጠለ ስለሆነ እንድንድን ይፈለጋል፡፡የዘለዓለማዊ መንግስቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን ከፍ ያለ ምኞት አለው፡፡ ከዚህም እንድንደርስ ገና በሕይወታችን ሳለን የሚያስፈልጉንን ጸጋዎች ወስኖልናል፡፡ በተከበረች ሞቱ ያገኘነው ደኀንነት እንዳይጠፋብን በጸጋ ላይ ጸጋ ሊሰጠን ፈለገ፡፡ «እኔ ለኑሮአቸው የሚያስፈልጉአቸውን ጸጋዎች እሰጣቸዋለሁ» በማለት ብሩህ ተስፋ ሰጠን፡፡ የቅዱስ ልብ ወዳጆች ከሆንን ገና በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅራችንን ከፍ ያለ ዋጋ እንቀበላለን፡፡

በዚህ ረጅምና አስቸጋሪ የሆነ የሕይወት ጉዞአችንና መንገዳችን በጸጋዎቹ ብርሃን ይመራናል፣ በችግራችንና በፈተናም ጊዜ ይረዳናል፣ ለኑሮአችን የሚሆን ጸጋን ይሰጠናል፡፡ ዓለምን ንቀው ከዓለም ሐሳብ ተለይተውና ርቀው በሙሉ ልባቸው ለእግዚአብሔር በቅንነትና በታማኝነት አገልገሎት ለሚሰጡ ሰዎች ለተመረጠ ኑሮአቸው የሚያስፈልገውን ጸጋ ይሰጣቸዋል፡፡ በዓለም ላይ እየኖሩ እግዚአብሔርን ለሚያገለግሉ ደግሞ ለዚህ ኃይለኛ የዓለም ኑሮ ማሸነፊያ የሚሆን ጸጋ ይሰጣቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በእነዚህ ጸጋዎች እየተረዳን በጥሩ ኑሮ ሊኖርና የጽድቅ ፍሬ ሊያፈራና ከኃጢአትም ሊርቅ ይችላል፡፡

ቅዱስ ልብ ለኑሮአችን የሚሆን እርዳታ ከመለገስም ሌላ ታማኝ ክርስቲያኖች እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ለደኀንነት ብቻ ሳይሆን ለቅድስናም ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ይረዳናል፡፡ በንቃት ቆርጠን እንድንነሳ ይገፋፋናል፡፡ መንፈሳውያን ክርስቲያኖች እንድንሆን እጅግ አድርጐ ይጠቅመናል፡፡ ይህ ጸጋ መንፈሳችንን ያነቃቃልናል፣ በመከራችንና በችገራችን ጊዜ ይረዳናል፣ በሐዘናችን ጊዜ ብርታትን ይሰጠናል፡፡ በፈተና ጊዜ መንፈሳዊ መመከቻ ጋሻ ለሕይወታችን ተስፋና ብርሃን ይሆነናል፡፡

እውነተኛ የእግዚአብሔርንና የባልንጀራችንን ፍቅር በውስጣችን ያሳድርልናል፣ በመንፈሳዊነት እንድንኖርና እንዳንሞትም ይረዳናል፡፡ «እኔ ለኑሮአቸው የሚሆንና የሚያስፈልጋቸውን ጸጋ እሰጣቸዋለሁ» የሚለውን የተስፋ ቃል መሠረት በማድረግ ተደስተን ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ መጨረሻ የሌለውን ምስጋና እናቀርብለት፡፡ በተለይ ግን ለዚሁ እንደምድጃ ለጋለ መለኮታዊ ፍቅሩ ጥልቅ የሆነውን ምስጋናችንን ልናቀርብለት ይገባል፡፡ በፍቅራችን ብድር በመመለስ እንካሰው፡፡ የተባረከና የተቀደሰ ልቡ ከሁሉ በላይ የፍቅራችንን መነሻና ምንጭ መሆን አለበት፡፡ የፍቅራችን  እንቀስቃሴ ወደ እርሱ የማያቋርጥ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡

በእያንዳንዱ የወር መጀመሪያ ዓርብ ይህን ልባችንን በመንፈሳዊ ደስታ የሚቀሰቅስ ተስፋውን እያሰብን በፍቅሩ እንበርታ፡፡ ይህን የትምህርትና የፍቅር ትልቅ ቀን በተለየ መንፈሳዊነት እንትጋ፡፡ የመጀመሪያ ዓርብ ወዳጆች በነገሮች ሁሉ በፍቅራችን የተቃጠለ ቅዱስ ልበ ኢየሱስ መሪያችን እንዲሆን ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ፡፡

08 June 2020, 12:31