ፈልግ

በሶርያ ውስጥ ጦርነት ካስከተላቸው ውድመቶች መካከል አንዱ፤ በሶርያ ውስጥ ጦርነት ካስከተላቸው ውድመቶች መካከል አንዱ፤ 

ሚላኖ የሚገኝ የዶን ቦስኮ የዕርዳታ ማዕከል ወደ ደማስቆ የሚዛወር መሆኑ ተነገረ።

በጣሊያን፣ ሚላኖ ከተማ የሚገኝ የዶን ቦስኮ ዕርዳታ መስጫ ድርጅት ከሌላ አጋር ድርጅት ጋር መበተባበር አገልግሎቱን ወደ ደማስቆ ለማዛወር መወሰኑን አስታወቀ። ድርጅቱ ይህን ለማድረግ የወሰነው በዚያው የሚገኘውን የዕርዳታ ተቋሙን ለማስፋፋት መሆኑን አስታውቋል። በሶርያ፣ ደማስቆ ከተማ ውስጥ ዶን ቦስኮ የዕርዳታ ድርጅት አገልግሎቱን የሚያስፋፋበት ጃራማና አካባቢ ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ወዲህ ጦርነቶች የተካሄዱበት እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ መሆኑ ታውቋል። በአካባቢው በሚስፋፋው ተቋም ውስጥ ወጣቶች ገብተው የሞያ ስልጠና የሚወስዱበት፣ የአካባቢው ሕዝብ የሕክምና አገልግሎትን የሚያገኝበት እና የቁምስናው ወጣቶች በእንግድነት የሚስተናገዱበት ማዕከል የሚቋቋምበት መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በሶርያ መዲና ደማስቆ የሚስፋፋው የዶን ቦስኮ ማዕከል ለሶርያ ወጣቶች የሞያ ስልጠናዎችን የሚሰጥ፣ ወጣቶች የደረሰባቸውን ማኅበራዊ ቀውስ ተሻግረው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዝ፣ ለአካባቢው ሕዝብ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል እንደሚሆን የተቋሙ ማኅበራዊ መገናኛ ክፍል ሃላፊ አቶ ስቴፋኖ አሮሲዮ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ታኅሳስ 2018 ዓ. ም. በጦርነት እጅግ የተጎዳውን አካባቢ የጎበኙት አቶ ስቴፋኖ፣ በደማስቆ ከተማ ለሕዝብ አገልግሎት እየሰጠ የቆየ የዶን ቦስኮ ማዕከል የነበረ ቢሆንም የተረጂ ሕጻናት፣ ወጣቶች እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥር ከ1,300 በላይ መሆኑን ገለጸው፣ ይህም ማዕከሉ ማቅረብ ከሚችለው አገልግሎት መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የማዕከሉ ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ስቴፋኖ አስቀድሞ ከነበረበት የደማስቆ ከተማ ማዕከላዊ አካባቢ በመዛወር ጃራማና ወደ ተባለ አካባቢ በመዛወር የሞያ ማሰልጠኛ፣ የወጣቶች ማዕከል እና የጤና አገልግሎቶች የሚሰጥ ሰፊ ማዕከል የሚመሠረት መሆኑን አስረድተዋል። ለረጅም ዓመታት ጦርነት የተካሄደባት ሶርያ በኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛቅ ጉዳት የደረሰባት መሆኑ ሲታወቅ በተጨማሪ የአገሪቱ የገንዘብ ምንዛሪ መቀነስ፣ አስደንጋጭ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ባይመዘገብም ለተለይቶ መቆያ ሲባል የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መቀዝቀዛቸው ነዋሪውን ሕዝብ ከችግር ወደ ችግር የከተተው መሆኑን አቶ ስቴፋኖ አስረድተው የዶን ቦስኮ ማዕከል በሚመሰረትበት የጃራማና አካባቢ የኢራቅ እና ፍልስጤም ስደተኞች መጠለያ ካምፖች የሚገኙበት በመሆኑ በአካባቢው የሚታየውን ችግር የሚያባብሰው መሆኑ ታውቋል።

በጣሊያን፣ ከሚላኖ ከተማ ወደ ሶርያ የሚዛወረው የዶን ቦስኮ ዕርዳታ መስጫ ማዕከል፣ የጃራማና አካባቢ ወጣቶች ሕይወት የሚቀይር፣ ተረጋግተው የሞያ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ እንደሚሆን  አቶ ስቴፋኖ አስረድተው ባሁኑ ወቅት በአካባቢው የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት በሚያግዙ የሞያ ዓይነቶች ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በማዕከሉ ውስጥ በተለያዩ የሞያ ዓይነቶች ሰልጥነው የሚወጡ ወጣቶች በጦርነት የወደመውን አገራቸውን መልሰው ለመገንባት የሚያስችል እውቀት እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸው የማዕከሉ ዋና ዓላማም ይህ መሆኑን አቶ ስቴፋኖ አስረድተዋል።       

24 June 2020, 19:42