ፈልግ

ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ዩስጢኖስ ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ዩስጢኖስ 

ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ዩስጢኖስ

በዚህ ዕለት ይህ የእውነተኛ ሃይማኖት ብርሃን ያሳዩንን በመንፈስ

ወላጃችን የሆኑ ብፁሆ አባታችንን አቡነ ያዕቆብ ዩስጢኖስን እናስብ፡፡

በመጀመሪያ የልባቸው ምኞት ቀጥሎ ደግሞ የሕይወታቸው ዓላማ አድርገው በግብር ያዋሉዋትና ያሳዩት ስብከታቸውን እናስተውል፡፡ «የልብ በርና መዝጊያ ቁልፍ ንግግር ነው፡፡ አፌን ስከፍትና ስናገራችሁ ልቤን ከፍቼላችኋለሁ ማለት ነው፡፡ ሁላችሁ መንፈስ ቅዱስ በልቤ ያሳደረውን ታላቅ ፍቅር ልታዩ በአገሬ በነበርኩበት ጊዜ የእናንተ የኢትዮጵያ ክርስቲያን ልጆች ጥሩ ወሬ ደረሰኝ፡፡ ወላጆቼ አባቴና እናቴ ሆይ መርቁኝ፣ አሰናብቱኝ፣ ወደ ተወደዱ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ወንድሞቼ ልሄድ ነው፤ ፍቅሬን እገልጽላቸዋለሁ መንገዱ ረጅም ነው፣ ስንት በረሃና ምድረ በዳ አለ; አንበሶችና ሌሎች ጨካኝ አራዊት ሞልተዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ወንድሞቼ እንደ እሳት የሚያቃጥለኝ ፍቅራቸውን ልግለጽላቸው፤ አንበሶች እና ሌሎች ጨካኝ አውሬዎች የሞሉበት በረሃና ምድረ በዳ አቋርጬ ስሄድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ምናልባት ሁለተኛ ጊዜ ወደ እናንተ ተመልሼ አንገናኝም አንተያይም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እኔ ልሞት የምፈልገው በዚያ ነውና ላያችሁ መጣሁ ከወላጆቼም እያለቀስኩና እንባ እያፈሰስኩ ተሰናብቼ ጉዞዬን ወደ ኢትዮጵያን አቀናለሁ፡፡ መርዛም እባቦችም ጭምር የሞላበት በረሃና ምድረ በዳ አቋርጬ፣ ባሕሮችን ስሻገር እግዚብሔርን «ጌታ ሆይ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዳይ እርዳኝ እነዚያን ወንድሞቼንና እህቶቼን ለማየት አብቃኝ፣ እነርሱን ሳላይ አትግደለኝ´ ብዬ ከጸለይኩ በኋላ በበረሃና በምድረ በዳ በማዕበል የሚታወኩ ባሕሮችን እያሳለፈ ከአንበሶችና ከጨካኝ አውሬዎች መንጋጋ አድኖ ወደ እናንተ በሰላም አደረሰኝ፡፡ በመካከላችሁ እንድገኝ እና እንድንተዋወቅ አድርጐናል፡፡

ሕይወቴን በመሉ ለእናንተ እሰጣለሁ፣ ስለ እናንተ እፀልያለሁ፣ አስብላችኋለሁ፣ የልቤ ሐሳብ በሙሉ ወደ እግዚአብሔርና ወደ እናንተ ነው እያሉ ሊያዳምጣቸው ለተሰበሰበው ሕዝብ የልባቸውን ሐባብ በደንብ አበክረው ገለጡለት፡፡ አንደ እሳት የሚያቃጥላቸውን ፍቅር አሳዩት፤ እርሳቸው ልባቸውን እንደከፈቱለት እንዲሁም ሕዝቡ ልቡን እንዲከፍትላቸው ፈቃዳቸው እንደሆነ ገለጡለት፡፡ በመጀመሪያ ግንኙነት አባታዊ ምክራቸውንና ቃላቸውን አሰሙት፡፡

በልባቸው መንፈስ ቅዱስ የአምላክ እና የባልንጀራን ታላቅ ፍቅር በግብር ሊያውሉት ፈለጉ፡፡ አምላካቸውንና ባልንጀራቸውን እየወደዱ እና እነርሱን እያገለገሉ እንደሚቀድሱ ከተረዱ በኋላ በዚህ ሐሳብ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ እግዚአብሔርን እያገለገሉ ባልንጀራቸውን እያዳኑ ሕይወታቸውን ሊያሳልፉ ወሰኑ፡፡ የወላጆቻቸውንና የአገራቸውን ፍቅር ጥለው ፈተና እና ስቃይን ሳይፈሩ በችግር ያለውን ባለንጀራቸውን ለመርዳት ረጅም አስቸጋራ እና አድካሚ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ስለ ነፍሳት ደኀንነት መከራ የተሞላበትን ሕይወት መረጡ፡፡ ለወላጆቻቸውም  «የኢትዮጵያን ልጆች እንደምወዳቸውና ላድናቸውም እንደምፈልግ እገልጥላችኋለሁ´ ብለዋቸው ነበር እንዳሉትና እንደ ተናገሩትም ደግሞ አደረጉ፡፡

እግዚአብሔርንም በመንገድ ምኞታቸውን ሳይፈጽሙ እንዳይጠራቸው በጥብቅ ተማጽነውት ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ የልባቸውን ምኞት ተቀብሎ ስለ መንግሥቱ መስፋፋት እና ስለ ነፍሳት ደኀንነት ሲል የልባቸውን ምኞት አሠመረላቸው፡፡ ብዙ እንዲሠሩ አደረጋቸው፡፡ በዓለም በተለይ በኢትዮጵያ ብዙ አቆያቸው፡፡ እስከ ዕለት ሞታቸው ድረስ ብዙ መንፈሳዊ ፍሬዎች አፈሩ፡፡ በስንት መከራ መካከል ሐዋርያዊ ሥራቸውን ጀመሩ፤ ነፍሳትን ፍለጋ ከመንደር ወደ መንደር ከከተማ ወደ ከተማ በአግር እየተጓዙ በድካም ሳይበገሩና ተስፋ ሳይቆርጡ ሐዋርያዊ ሥራቸውን በተግባር አሳዩ፡፡ ብዙ ፈተና፣ ውርደት፣ ስደት እና ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜ ተንኰለኛ ነውና እግዚአብሔርን መቃወም እየተተናኰለ በመፈታተን እና በማጨናገፍ ክፉ ሰዎችን መልእክተኞችና መሣሪያ አድርጐ በመጠቀም ሐሳባቸውንና ሥራቸውን ለማክሸፍና ለመደምሰስ ቢነሳም ግን አልተሳካለትም፡፡ አምላክ ከእርሳቸው ጋር ስለነበር ድል ነሱት፡፡ በተቀደሰ ሕይወታቸውና ጸሎቻው፣ ቃላቸውና ስብከታቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ነፈሳት ወደ እውነተኛ ሃይማኖት እና እምነት እንዲመለሱና እንዲከተሉ አደረጉ፡፡ ብዙዎች የአገር ተወላጆችም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሳቸው እንዳለ ከተገነዘቡ በኋላ በታላቅ ፍቅርና ታማኝነት ተከተሏቸው፡፡

«እኔ እዚያው ልሞት ነው የምፈልገው´ ብለው ነበር፡፡ አምላክ የልባቸውን ምኞት አሠመረላቸው፡፡ ስለ አምላክ ክብርና ስለ ነፍሳት ደኀንነት ብዙ ከሠሩ ከደከሙ በኋላ የድካማቸውን ፍሬ ሽልማት ሊቀበሉ ወደ ሰማይ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ከበዋቸው ለነበሩ ውድ ልጆቻቸውም «በእርግጥ እኔ ሥራዬን አልፈጸምኩም፣ ምክንያቱም ጊዜ ስለአጠረኝ ነው፤ እናንተ ግን አትፍሩ አባታችሁ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ «ከቤታችሁ ሐሜት እና ውርደትን አርቁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ በእምነታችሁና በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃን ሁሉ´ አሏቸው፡፡

እኚህ ታላቅ መንፈሳዊ የእግዚአብሔር ሰው የእውነተኛ ሃይማኖትን ብርሃን ስላሳዩን እናመሰግናቸው፤ እንደ እርሳቸው በልባችን የአምላክንና የባልንጀራን ፍቅር እናሳድር፣ አብነታቸውን እንከተል «ተዋደዱ፣ በሃይማኖታችሁ ጽኑ፣ ጠንክሩ የሚል ምክራቸውን ሰምተን እንከተል፣ አጥብቀንም እንያዝ በሰማይ ሆነው እንዲጠብቁ «አባ ጸልዩን´ በማለት ዘወትር እንለምናቸው፡፡

የሕይወታቸው ታሪክ

እ.አ.አ. ጥቅምት 8 ቀን 1800 ዓ.ም. ሳንፈለ ኢጣሊያ ተወለዱ፡፡ ጥቅምት 13 ቀን 1818 ዓ.ም. ወደ ማኀበረ ልዑካን ላዛሪስት ገዳም ናፖሊ ገቡ፡፡ ሰኔ 18 ቀን 1820 ዓ.ም. ማዕረገ ክህነት ተቀበሉ፡፡ በሀገራቸው (ናፖሊ ኦሪያ) የክህነት ሥራ ፈጸሙ፡፡ በየጊዜው በማኀበራቸው የተማሪዎች የተመካሪያን ተማሪዎችና የመነኮሳን አለቃ ሆነው ተሾሙ፡፡

መጋቢት 10 ቀን 1839 ዓ.ም. የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ያዕቆት የኢትዮጵያና የአካባቢዋ ሐዋርያዊ መስተናብርና ሊቀ ካህናት ብለው ሰየሙዋቸው፡፡ ጥቅምት 29 ቀን 1839 ዓ.ም. ወደ ዓድዋ ገቡ፡፡ ከዚያም ከባልሥለጣኖች እና ሕዝብ ጋር ከተዋወቁ በኋላ የአገሩን ቋንቋ ልማድና ባሕል በማጥናት ሐዋርያዊ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ ከዓድዋ ወደ ጐልዓ እና ዓሊቴና ተሻገሩ፡፡ በትግራይ ብርቱ መከራ ስለገጠማቸው ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር እንዲዛወሩ ግድ ሆነባቸው፡፡

ሐምሌ 6 ቀን 1847 ዓ.ም. በምጽዋ በብፁዕ አቡነ ማስያስ እጅ የጵጵስና ማዕረግ ተቀቡ፡፡ በኤርትራ ክፍለ ሀገር በተለይ የነበሩቸውና የሠሩባቸው መንደሮች ሓላይ፣ ሔቦ፣ ዓደፈኒዕ፣ ኣኹሩር እና ዓዲቀንዲ ናቸው፡፡

ሐምሌ 31 ቀን 1860 ዓ.ም. በዓስካራ (ዓሊገደ፣ ሊደለ፣ ባሕሪ) በጻድቃን ሞት አረፉ፡፡ አስክሬኖቸውን ከሞቱበት ቦታ በማንሳት በሔቦ ተቀበሩ፤ እስካሁንም አጥንታቸው በሔቦ ቤተክርስቲያን ውስጥ አርፎ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ. ጥቅምት 26 ቀን 1975 ዓ.ም. (በአገራችን አቆጣጠር ጥቅምት 16 ቀን 1968 ዓ.ም.) ቤተክርስቲያን ቅድስናቸውን ለዓለም ሁሉ አወጀች፡፡

26 June 2020, 18:20