ፈልግ

የኢየሱስ ቅዱስ ልብ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ 

በፍቅራችን የተቃጠልክ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ሆይ ልባችን በፍቅርህ እንዲቃጠል አድርገግ!

ይህ አሁን የምንገኝበት የሰኔ ወር በወር ደረጃ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ የሚታሰብበት ወር እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊነት የሚከበር በዓል ነው። ከዚህ በመቀጠል የክርስቶስ ቅዱስ ልብ በዓል አከባበር ታሪካዊ መሰረቱን እንደ ሚከተለው እናቀርበዋለን ተከታተሉን።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የኢየሱስ ቅዱስ ልብ

እ.ኤ.አ. በታኀሣሥ 27/1673 ዓ.ም.  ቅድስት ማርገሪት ማርያ አላሎክ በቅዱስ ቁርባን ፊት ተንበርክካ ስትጸልይ ኢየሱስም መጥቶ በደረቷ ላይ ለረጅም ጊዜ አረፈባት፡፡ ለረጅም ጊዜ ሰውሮት የነበረውን የቅዱስ ልቡን ምስጢር ገለጠላት፡፡ ልቡንም እያመለከተ “ልቤ በሰው ፍቅር ተሰብሮ የልቤን የፍቅር ወላፈን ሊገታው ስለማይችል በአንቺ አድርጌ በዓለም ልዘረጋውና ላስፋፋው ግዴታ ነው፡፡ ሰውን በጸጋ ሀብቶች እንዲሞላው በልቤ ከኩነኔ ሊያድናቸው የሚችል ፀጋ ሁሉ አለ፡፡ አንቺ ድኻና ያልተማርሽ ዕውቀት የሌለሽ ብትሆኚም ይህንን ትልቅ ኃላፊነት ልሰጥሽ መረጥኩሽ” እያለ ተናገራት፡፡ የልቡን ፍቅር ለሰው ሁሉ እንድታስታውቅ በዓለም ላይ የቅዱስ ልብ መንፈሳዊነትና ፍቅር እንድታስፋፋ ተማጠናት፡፡

ራሷ ቅድስት ማረገሪታ ስለዚህ ነገር ስትናገር “ይህ መለኰታዊ ልብ በነበልባልና በእሳት ወላፈን ላይ ተቀምጦ ደማቅ ብርሃን ያንፀባርቅ ነበር፣ ቅንነቱም ይታይ ነበር፣ በእሾህ ተከቦም ነበር፣ በላዩ አንዲት ትንሽ መስቀል ነበረች፡፡ በሰዎች እንዲወደድ እና ሰዎችን ከጥፋት  ለማዳን እንደሚፈልግ ዋና ምኞቱ መሆኑን አስታወቀኝ። ልቡ ስለ ሁሉ የፍቅሩን መዝገብ ጸጋዎች ምሕረት ደኀንነትና ጽድቅ ለሰዎች እንዳሳውቅ ነገረኝ፡፡ በእነዚህ ጸጋዎች ለመሳተፍ ቅዱስ ልቡን ማክበር ያስፈልጋል ለሚወዱት ጸጋውንና ቡራኬውን እንደሚሰጣቸው ተስፋ ሰጠኝ፡፡ በዚህ መንፈሳዊነት ሰዎችን በዚህ ጊዜ ከሰይጣን ባርነት ነጻ አውጥቶ ወደ ፍቅሩና ጣፋጭ መንግሥቱ ሊመልሳቸው የሚያደርገው የመጨሻ የሰው ፍቅር ነው” እያለች ትናገር እንደ ነበረ ከታሪኳ እንረዳለን።

ቅዱስ ልብ ሰዎችን ሁሉ ሊወዳቸው፣ ሊያግዛቸውና ሊያድናቸው ሲጥር እነርሱ ግን ስለ ፍቅሩና ስለ ጸጋው ግድዬለሽ በመሆናቸው እጅግ አንዳዘነባቸው ገለጠላት፡፡ “ሰዎችን ብዙ ስለወደዳቸው ስለ እነርሱ ምንም ነገር ያልቀረበ ልቤ ይኸውልሽ፣ ትንሽ የፍቅር ምልክት እንኳ ቢያሳዩኝ ለእነርሱ ባደረኩት ነገር ሁሉ ደስታ በተሰማኝ ነበር፡፡ ብዙዎች መንፈሳዊ ሕይወታቸው በመቀዝቀዙ ያሳዝኑኛል። ከሁሉም ነገር የሚያስከፋኝ ግን እነዚያ በልዩ ጸጋ የተመረጡ ካህናት መነኮሳት እና ደናግል እንደ ማንኛውም ተራ ምእመን ሲመለከተኝ ነው” በማለት እንደ ተናገራት ከታሪኳ ለመረዳት እንችላለን።

“እንግዲህ አንቺ ይህንን ምሥጋና እያቀረብሽ አጽናኚኝ፣ ከሁሉም አስቀድመሽ በቅዱስ ቁርባን ተቀበይኝ፡፡ ቀጥለሽ በወሩ መጀመሪያ ዓርብ በመንፈሳዊነትና ትሕትና በተመላበት ዝግጅት ቅረቢኝ፣ የተቀደሰ ልቤ በሚከበርበት ቀን ደግሞ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል የምስጋና መስዋዕት አቅርቢልኝ” የሚል ጥብቅ መልዕክትና የአደራ መማፀኛ ነገራት። እርሷ ደግሞ ይኸንን የቅዱስ ልብ ፈቃድ ለሰው ልታሳውቅ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ብዙ ችግሮችን እና ግልፅ ተቃውሞዎችን በመቋቋም የለፋችበትን የቅዱስ ልብ መንፈሳዊነት እና እንደ እሳት የሚያቃጥል ፍቅር ቀስ በቀስ በመላው ዓለም በአዳም ልጆች መካከል እንዲስፋፋ አደረገች፡፡

ቤተክርስቲያን በበኩሏ ይህን አዲስ መንፈሳዊነት በጥንቃቄ በመመርመር ጠቃሚነቱንና አስፈላጊነቱን ከተረዳች በኋላ መልካም እንደሆነ ለደኀንነት ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በይፋ ደገፈችው፡፡ ለቅዱስ ልብ የሚገባው አክብሮትና አምልኮ እንዲሰጥ ወሰነች፡፡ ስለዚህ ለእርሱ በሚሆን ዓመታዊ ክብረ-በዓል ቅዳሴ፣ ጸሎት፣ ራስን ማቅረብ፣ ሊጣንያ፣ የካሳ ሥራ መድባ ለዓለም ሁሉ ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡ ይህም በአጭር ጊዜያት ተሰሚነት እና ተቀባይነት አገኘ፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ ስለ ቅዱስ ልብ ሲናገሩ “የክርስትናን ትምህርት በአጭሩ የያዘ የበለጠ የቅድስና መንገድ እንደሆነ” ገልጠዋል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ ደግሞ “በእርሱ ተስፋ እንድናደርግ ያስፈልገናል፤ ስለ ሰው ደኀንነት እንድንማልድ ያስፈልጋል” በማለት ስለ ኢየሱስ ቅዱስ ልብ መናገራቸው ይታወሳል። እንዲሁም ፒዮስ 12ኛ “ቤተክርስቲያን እና የተለያዩ አገራት ያለ ቅዱስ ልበ ሌላ ተገንና መጠጊያ የላቸውም፡፡ በተለይ በሽተኞችንና ሕመምተኞችን ሊፈውስና ሊያድን የሚችል ይህ መንፈሳዊነት ብቻ ነው፣ ምክንያቱም ቅዱስ ልብ የዓለም ሁሉ ደኀንነት ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ማርገሪታ ስለ ቅዱስ ልበ መንፈሳዊነት ፍሬ አስቀድማ ስትናገር “እንደዚህ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ መንፈሳዊነት ወደ ፍጽምና የሚያደርስ የለም፡፡ ይህ ቀዝቃዞችን ያሞቃቸዋል፤ ሙቆችን ቶሎ ወደ ቅድስና ደረጃና ማዕረግ ያደርሳቸዋል፡፡ እነዚያ ለነፍሶች ደኀንነት የሚጥሩና የሚለፉ በዚህ ሕያው መንፈስዊነት የሚያስደስት ፍሬ ያገኛሉ፤ እነዚያን ልበ ደንዳና ኃጢአተኞችን ሳይቀር ይቀሰቅሳቸውና መንፈሳዊ ሕይወትን ይሰጣቸዋል” ብላለች፡፡

ይህንን በፍቅር የመጣልንን ቅዱስ ልብ በበኩላችን በፍቅር እንቀበለው፤ ለእኛ የሚያስፈልገን መሆኑን ተገንዘበን እኛው ራሳችን ልንፈልገው ይገባል። ልባችን በፍቅሩ እንዲሳብ ምኞታችን እርሱ እንዲሆን ያስፈልጋለ፡፡ በሁሉ ሥፍራ ቅዱስ ልብን ልናገለግልና ልናስደስት፣ በሁሉም እንዲታወቅ እና እንዲከበር ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ በሙሉ እምነት ምሥጋናችንን እናቅርብለት። በተለይ ደግሞ እርሱ በሚፈልገው ስፍራና ቀን በየመጀመሪያው ዓርብ በልዩ መንፈሳዊነት ፍቅራችንን እና አክብሮታችንን ልንገልጽለት ይገባል፡፡ “አንድ ጊዜ ጣፋጭ እና ደግ ወደ ሆነው ልበ ኢየሱስ ከገባን ከእርሱ አንወጣም፤ በእርሱ መኖር ለእኛ ጣፋጭ የሆነ ሕይወት ይሰጠናል” በማለት ቅዱስ አባታችን በርናርዶስ ይናገረናል፡፡ ቅዱስ ቦናቨንቱራ ደግሞ “ቅዱስ ልብ ቤቴ መኖሪያዬ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እርሱ የልቤ ዕረፍት ነው፡፡ በዚያም ከኢየሱስ ጋር አነጋግራለሁ፣ ከዚያም የፈለግሁትን አገኛለሁ” እያለ ይናገር ነበር።

የኢየሱስ ቅዱስ ልብ መንፈሳዊነት ካለን የመንግሥተ ሰማያት ተስፋ ሊኖረን ይችላል፡፡ ያን ጊዜ በእውነት ብፁዓን ልንሆን የሚያስፈልጉንን ጸጋዎች እናገኝ፣ ፍጹማን ክርስቲያኖች እንሆናለን፡፡ «በፍቅራችን የተቃጠልክ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ሆይ ልባችንም ደግሞ በፍቅርህ እንዲቃጠል አድርገው” እያልን መንፈሳዊነቱን አጥብቀን በመከተል ዘወትር እንለምነው!

19 June 2020, 09:12