ፈልግ

መልካሙን ገድል ተጋድያአለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ መልካሙን ገድል ተጋድያአለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ 

መልካሙን ገድል ተጋድያአለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ

የሰኔ 15/2012 ዓ.ም አስተንትኖ

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሉ ደቀ መዝሙሩና ተማሪው ለነበረው ጢሞተቴዎስ «እኔ ግን መስዋዕት ለመሆን ተቃርቤአለሁ ከዚህ ዓለም የምሄድበት ጊዜ ደርሷል፣መልካሙን ገድል ተጋድየአለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፡፡ ይህንንም አክሊል ቅን ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያን ቀን ይሰጠኛል፡፡ ይህንንም ለእኔ ብቻ ሳይሆን የእርሱን መገለጥ ለሚወድዱ ሁሉ ይሰጣቸዋል” (2ኛ. ጢሞ. 4፣6-8) እያለ ጻፈለት፡፡ ባጭሩ ሞቱ እንደቀረበ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የስብከቱና ያካሄደው ከፍተኛ ውጊያ ከሰይጣን ከሥጋ ፍትወት ከዓለም አታላይነት ጋር ያደረገው ጦርነት ሸልማት አክሊል ይጠብቀው እንደነበረ አስታወቀው፡፡ የዚህን ቃል ምስጢር አንድ በአንድ እናስተውለውና እናስተንትነው፡፡

እኔ ወደ መጨረሻዬ መስዋዕት ለመሆን ተቃርቤአለሁ፣ የዕረፍት ጊዜዬ ደርሶአል፣ እንደሌላው ሰው ሁሉ ወደ ሕይወቴ መጨረሻ ደርሼ ልሞትም ተቃርቢያለሁ ማለቱ ነው፡፡ ግን ሞት አያስፈራኝም ይላል፡፡ ሁል ጊዜ ተዘጋጅተው እንደሚቆዩ እንደዚህ ያለ ጥሩ መንፈስ በእኛ ላይ ይገኛል ወይ? ሞት ሲመጣብን እንዴት አድርገን እንቀበለዋለን?

መልካሙን ገድል ተጋድየአለሁ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ወታደር ከሆነበት ዕለት ጀምሮ ስለ እርሱ ባለው ኃይልና ችሎታ ሁሉ ከመዋጋት ዕረፍት አላደረገም፡፡ ሁልጊዜ ትጉሕና ታማኝ ወታደር ሆኖ ተገኘ፡፡ ክርስቶስ ባሳየው መንገድ ቀጥ ብሎ ተጓዘ፡፡ ጨካኝ የክርስቶስ ጠላት እና በምእመናኑ ላይ ስደት ቀስቃሽ የነበረው ሰው አሁን ደግሞ ጽኑ እውነተኛና ሐቀኛ ሐዋርያ ሆነ፡፡ እነዚያ በሐቀኛ ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ይጠራጠሩ የነበሩ «እኔስ ሐዋርያ አይደሁምን? እናስተስ በእግዚአብሔር ጸጋ የሥራዬ ፍሬ አይደላችሁምን?”(1ኛ. ቆሮ. 9፣1) «እኔ ነፃና ከዚህ ሃይማኖት ውጭ በነበርኩ ጊዜ ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እንድስብ ባርያ ሆንኩ ከአይሁዳውያን ጋር አይሁዳዊ ከነዚያ በኦሪት ሕግ ሥር ከሚኖሩት ጋር እንደ እነርሱ ሆንኩ፡፡ ከበሽተኞች ጋር ተመሰለኩ ሁሉንም ስለ ወንጌል ትምህርት ያደርግሁት ነው” (1ኛ ቆሮ. 9፣22) እያለ ይመልስላቸው ነበር፡፡

ስለ ክርስቶስ ለመስበክ ብዙ መከራና ስቃይ ተፈራረቀበት፡፡ «ብዙ ጥረት አድርጌ፣ ታግዬ፣ ታስሬና ተሰቃይቼ ወደ ሞት ደርሻለሁ፣ ሰላሳ ዘጠኝ ጅራፍ አምስት ጊዜ በአይሁዳውያን ተገርፌአለሁ፣ ሶስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፣ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፣ ሶስት የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፣ አንድ ቀንና ሌሊት በባሕር ላይ ነበርኩ፣ በጉዞዬ ብዛት የወንዝ የጐርፍና የሽፍቶች አደጋ ደርሶብኛል፣ አይሁዳውያን ወገኖችና አረማውያን አደጋ ጥለውብኛል፣ እንዲሁም በከተማ እና በበረሃ በባሕርም አደጋ ደርሶብኛል፣ እንዲሁም ከሐሰተኞች አደጋ ደርሶብኛል፤ ብዙ ሥራና ድካም ነበረብኝ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፣ በረሃብና በውኃ ጥም ተጨንቄአለሁ፣ ብዙ ጊዜም የምግብ እጦት፣ ብርድና መራቆትም ደርሶብኛል” (2ኛ. ቆሮ. 11፣23) ይላል።

ይህን ሁሉ መከራ ስለ ክርስቶስ ተሸክመው ወንጌልን ለመስበክና ለማስፋፋት ሲል ብርቱ ተጋድሎ አደረገ፡፡ ስለዚህ «መልካሙን ገድል ተጋድየአለሁ፣ ሩጫዬንም ጨርሼአለሁ” እያለ ማውሳቱ ሐቅ ነው፡፡ እኛስ በሕይወታችን እንደዚህ ብለን ልንናገር እንችላለን ወይ? ስለ ክርስቶስ መልካሙን ገድል ተጋድየአለሁ በመንገዱ ተመላልሼ የሰጠኝን ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ በመወጣት ፈጽሜአለሁ ለማለት እንችላለን ወይ? አንደ ጊዜ የተቀበለውን ሃይማኖት የክርስቶስ እምነት በጽናት ያዘው፡፡ ስለ እርሱ ኖሮ ስለ እርሱ ሞተ፡፡ እኛስ በሃይማኖታችን በእምነታችን እንደዚህ ብለን ልንመካ አንችላለን ወይ?

በእውነት ወደን፣ አክብረን፣ በጽናት እንይዘዋለን? ስለ እርሱ መከራና ሞት እንቀበላለን? እነዚያ በሕይወታቸው ዘመን ጥሩ ውጊያ የተዋጉ የሕይወታቸውን መንገድ በጣም ጥሩ አድርገው የፈጸሙ ሃይማኖታቸውንና እምነታቸውን ያከበሩ በሞታቸው ወቅት እግዚአብሔር በተስፋና በደስታ ልባቸውን ይሞላቸዋል፡፡ ከዚህ ዓለም እንደገና በደስታና በተስፋ ይሰናበታሉ፡፡ ይህ ለቅዱስ ጳውሎስ በሞቱ ጊዜ የተሰማው ሰማያዊ ደስታና ተስፋ ለእኛም እንዲሰማን ከፈለግን በሕይወታችን ዘመን ዘወትር እርሱን እንምሰል፤ በእርሱ መንገድ በመመላለስ እርሱ የሚያደርገውን እናድርግ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

22 June 2020, 18:27