ፈልግ

እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ፣ እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አራት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ብጽዕናን አጸደቁ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ትናንት ሰኔ 12/2012 ዓ. ም. የአራት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ብጽዕና ማዕረግ ማጽደቃቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት የአራት የቤተክርስያን አገልጋዮች ለነበሩት የብጽዕና ማዕረጋቸውን ማጽደቃቸውን አስታውቀዋል። ቤተክርስቲያን የብጽዕና ማዕረግ የምትሰጣቸው አራቱ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፥ ጣሊያናዊት እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ፣ ቨነዙዌላዊው ሐኪም፣ ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ቺስኔሮስ፣ አርጀንቲናዊው ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማሜርቶ ዴላ አሸንሲዮን ኤስኪ እና የሳልቫቶሪያን ገዳማዊ ማሕበር መስራች የነበሩ ጀርመናዊ ካህን አባ ፍራንቸስኮ ማርያ ደላ ክሮቼ መሆናቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ጣሊያናዊት እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ፣ እንደ ጎአርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 20/1939 ዓ. ም. በጣሊያን ሌኮ አውራጃ የተወለደች እና የቅዱስ አንድሬያ እህቶች የሚባሉ የቅዱስ መስቀል ደናግል ማኅበር አባል የነበረች መሆኗ ታውቋል። እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ የተገደለችው እምነቷን በሚቃወሙ ሦስት ልጃገረዶች እጅ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 6/2000 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። ሰይጣናዊ አምልኮን በሚከተሉ ወጣት ልጃገረዶች እጅ የተገደለች እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ ለወላጆቿ አስረኛ ልጃቸው መሆኗ ታውቋል። እህት ማርያ ላውራ ማይኔቲ ወደ አንድ ካህን ዘንድ ለኑዛዜ በሄደችበት ወቅት የተነገራትን መንፈሳዊ ምክር እና የእግዚአብሔርን ጥሪ ተግባራዊ ለማድረግ መላ ሕይወቷን ለእግዚአብሔር ፍቅር ለማስገዛት የወሰነች መሆኑ ታውቋል። በዚህ ውሳኔዋ በመጽናት ለቤተሰቦቿ የምንኩስና ሕይወት እየኖረች ሕጻናትን እና ወጣቶችን እያስተማረች መንፈሳዊ ረዳታቸው ለመሆን የምትፈልግ እንደሆነ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1957 ዓ. ም. ማስታወቋ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 26/1864 ዓ. ም. የላቲን አሜሪካ አገር በሆነችው ቨነዙዌላ የተወለደው ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ሲስኔሮስ፣ ከስድስት ወድሞቹ መካከል የመጀመሪያው ሲሆን፣ በዋና ከተማ ካራካስ የሕክምና ሞያ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ይህን ሞያ ለማሳደግ ወደ ፓሪስ፣ ቤርሊን፣ ማድሪድ እና ኒውዮርክ በመሄድ በከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን የተከታተለ መሆኑ ታውቋል። የሕክምና ሞያ ትምህርቶችን ከጨረሰ በኋላ ወደ ትውልድ አገሩ ቨነዙዌላ የተመለሰው ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ሲስኔሮስ፣ በካራካስ ዩኒቨርሲቲ፣ ሕክምና ፋካልቲ ውስጥ የባክቴሪዮሎጂ ትምህርት መምህር ሆኖ መሥራቱ ታውቋል። ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ሲስኔሮስ በሚያስተምርበት የሕክምና ፋካልቲ ውስጥ ማይክሮስኮፕ ወይም አጎሊ መነጽር ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ማስተዋወቁ ታውቋል። ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ በልቡ ጠንካራ እምነትን በመያዝ በሕክምና ሞያው ለማገልገል የወሰነ፣ በተለይም የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገውን ድሃ ማኅበረሰብ በማገልገል፣ መድኃኒቶችን በነጻ እያደለ ሲያክም የቆየ እና በኋላም “የድሆች ሐኪም” የሚል መጠሪያ የተሰጠው መሆኑ ታውቋል። ለምንኩስና ሕይወት ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ሲስኔሮስ፣ እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1908 ዓ. ም. በመካከለኛው ሰሜን ጣሊያን ክፍለ ሀገር በሉካ፣ ቼርቶሳ ዲ ፋርኔታ መንደር የኖረ መሆኑ ታውቋል። ባደረበት የጤና መታወክ ምክንያት ወደ ትውልድ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ሲሻለው ወደ ሮም በመምጣት በላቲን ኮሌጅ ውስጥ እየኖረ የስነ መለኮት ትምህርቱን የተከታተለ መሆኑ ታውቋል። ሆሴ ግሬጎሪዮ ኤርናንዴስ ሕመሙ ሲደጋገምበት፣ እግዚአብሔር ወደ ዓለማዊ ሕይወት የጠራው መሆኑን በመገንዘብ ወደ የፍራንችስካዊያን ሦስተኛ ዓለማዊ ማኅበር ተቀላቅሎ የኖረ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሕይወቱ እንደ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የኢየሱስን መልክ በሕሙማኑ ስቃይ ሊያውቅ የቻለ መሆኑ ታውቋል።  

ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን ለብጽዕና ማዕረግ ካዘጋጀቻቸው አራቱ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መካከል አንዱ፣ አርጄንቲናዊው ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ አቡነ ማሜርቶ ዴላ አሸንሲዮን ኤስኪ፣ ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል የነበሩ መሆናቸው ሲታወቅ፣ የጵጵስና ማዕረግ የተቀበሉት ከህልፈታቸው ሦስት ዓመት አስቀድሞ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1880 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 11/1826 ዓ. ም. በአርጄንቲና፣ ሳን ሆሴ ደ ፔድራ ቢያንካ ተወልደው በጥር 10/1883 ዓ. ም. ማረፋቸው ይታወሳል። ከአምስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወላጅ እናታቸው እምነትን እና የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ ፍቅር በማስተማር ያሳደጓቸው ብጹዕ አቡነ ማሜርቶ ዴላ አሸንሲዮን ኤስኪ፣ ወደ ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር ገብተው ትምህርታቸውን መከታተላቸው ይታወሳል። ለክህነት አገልግሎት የሚያበቃቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች በፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር ውስጥ ከተከታተሉ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 18/1848 ዓ. ም. የክህነት ማዕረግ መቀበላቸው ይታወሳል። በትምህርት ዓለም ውስጥ አጭር ልምድ ካካበቱ በኋላ፣ በዘመናዊው ዓለም የአርጄንቲና ሕገ መንግሥት ረቂቅ በጸደቀበት ዕለት የአገሪቱ ሕዝብ አንድ እንዲሆኑ በማለት ልብ የሚነካ ጸሎት ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህን ጸሎታቸውን በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት ጁስቶ ሆሴ ኡርቂዛሎዶ በብሔራዊ ጋዜጣ በማሳተም ለመላው የአርጄንቲና ሕዝብ እንዲደርስ ማድረጋቸው ይታወሳል።      

ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን ለብጽዕና ማዕረግ ካዘጋጀቻቸው አራቱ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ሌላው የሳልቫቶሪያዊን ገዳማዊ ማሕበር መስራች የነበሩ፣ ጀርመናዊው ተወላጅ አባ ፍራንቸስኮ ማርያ ደላ ክሮቼ መሆናቸው ታውቋል። ከድሃ ቤተሰብ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 16/1848 የተወለዱት አባ ፍራንቸስኮ ማርያ ደላ ክሮቼ፣ ቤተሰቡን በስዕል ሞያ ሥራው ያግዝ እንደ ነበር ሲታወስ፣ በዚህ ሞያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የትምህርት ቤቱ መምህራን ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉለት መሆኑ ይታወሳል። በትምህርቱ ዓመታት የእስያ አገሮች ቋንቋዎችን ያጠናው ፍራንቸስኮ ማርያ ደላ ክሮቼ፣ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሄድ የካቶሊክ ምዕመናን አንድነት ማኅበር በማቋቋም የቤተክርስቲያኒቱን እምነት ከጥቃት የተከላከለ እና ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ መሆኑ ይታወሳል። በዚህ ዓላማው ሁለት የገዳማዊያን ማኅበራትን የመሰረተው ፍራንቸስኮ ማርያ ደላ ክሮቼ፣ በተለያዩ ዓመታት ወደ ሕንድ፣ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በመጓዝ የምዕመናን አንድነት የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራትን ካከናወነ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 8/1918 ዓ. ም. በስዊዘርላንድ ማረፉ ይታወሳል። ለቅድስና ሕይወት ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት እና ለዚህም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን እንደነበር ከማስታወሻ ደብተሩ የተገኙ የጽሑፍ መረጃዎች አመልክተዋል።  

20 June 2020, 18:55