ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የጴንጤቆስጤ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡

“በአንተ ብርሃን ብርሃንን እናያለን”  (መዝ 36:9)

“በአንተ ብርሃን ብርሃንን እናያለን” የሚለው ጥቅስ እምነታችን በተፈተነበት በዚህ የወረርሽኝ ዘመን በተስፋ ብርሃን ያጽናናናል። የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ምእመናን፣ እንደምታውቁት አገራችን እና ዓለማችን በኮቪድ አሥራ ዘጠኝ ወረርሽኝ የሚሰቃዩበት ወቅት ነው። በዚህ ወረርሽኝ የተነሣ የብዙዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ብዙዎች ተሰቃይተዋል፤ እየተሰቃዩም ነው። እንዲሁም ማኅበራዊ ኑሯችን ባልጠበቅነው ሁኔታ ተቀይሯል። ወረርሽኙን ለመግታት ሲባል መጨባበጥን፣ መሰብሰብን እና ሌሎች ማኅበራዊም ሆነ አካላዊ መቀራረቦችን አቁመናል። እንደልባችን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አልቻልንም። ማስቀደስና መቍረብ ናፍቆናል።

በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉት ዜናዎችም ያስደነግጡናል። ምናልባት “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውከኝ! ለምን ተውከን! (መዝ 22:1)” የሚለው ጸሎት በውስጣችን ይመላለሳል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ይህንን ጩኸት የሚያሰሙ ሰዎች እንደሚኖሩም መገመት አያዳግትም። ይህን የሰቆቃ ጩኸት ከነቢዩ ዳዊት፣ ከነቢዩ ኤርምያስ (ኤር 4:19፣ 20:7-18 ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ )  እና ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰምተነዋል። በዚህም ጌታችን እና ነብያቱ ምን ያህል ለሚሰቃዩ ሰዎች ቅርብ መሆናቸውን ለመረዳት እንችላለን።

ጤና ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉ እሴቶች አንዱ ነው። ለጤና ቅድሚያ መስጠት ቅንጦት አይደለም። በባሕላችንም “ጤና ይስጥልኝ” የሚለው ሰላምታ የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። የሚተዋወቁ ሰዎች ሲገናኙም ከምንም አስቀድመው የሚጠይቁት የጤናን ጉዳይ ነው። “እንደምን ነህ? እንደምን ነሽ?” ከተባለ በኋላ ነው ወደ ሌሎች ጉዳዮች የሚገባው። ወረርሽኝ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሁኔታን የሚገዳደር ከባድ ፈተና ነው።  

የሰው ልጅ እውነትን ይፈልጋል። ለማወቅ ይጥራል። በተፍጥሮ እና በማኅበራዊ ሳይንስ ይተጋል። አሁንም ለዚህ የጤና መታወክ ችግር እና አደጋ መድኃኒትና ክትባት በመፈለግ ላይ ይገኛል። እንደዚሁም ሊፈጠር ለሚችለውና ለተፈጠረው ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መፍትኄ በመፈለግ ላይ ነው። እነኚህ ጥረቶች አስፈላጊ ናቸው። በእነዚህ ትግሎች ውስጥ ገብተን የበኩላችንን ማበርከት ይጠበቅብናል። ይህንን ጥረታችንን በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር ብናከናውን ብርሃንን እናገኛለን።

ይህ እምነታችን የተፈተነበት ወቅት የፍርሃት፣ የመረበሽ፣ የመደናገጥና ተስፋ የመቁረጥ ጊዜ እንዳይሆን በእምነት ብርሃን ነገሮችን መመልከት ይረዳናል። እንደ ሰው ልጅ ማድረግ የሚቻለውን እያደረግን በእግዚአብሔር ጸጋ ደግሞ እንደገፍ። መፍትሔዎች የራቁን ቢመስለንም፣ የሕይወት ምንጭ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ዓይኖቻችንን እናንሣ።  ያልታዩንን ነገሮች በክርስቶስ ብርሃን ማየት እንችላለንና።

በጥንት ዘመን የእምነት ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መነኮሳትና ደናግል በወረርሽኝ ጊዜ በርኅራኄ እና በፍቅር የተጠቁትን ሰዎች እንዳገለገሉና እንደተሰው የሚገልጹ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። በዚህም መሥዋዕትነታቸው ለእግዚአብሔር እና በመልኩ ለተፈጠረው የሰው ልጅ ክብር ሰጥተዋል። ታዲያ አሁንም ይህንን ገድል የሚፈጽሙ የጤና ባለሙያዎችና በማንኛውም ዘርፍ የሚሳተፉ ለጋስ ሰዎች ክብር፣ ምስጋና እና እውቅና ይገባቸዋል። እግዚአብሔር እነርሱን እንደሚባርካቸው እናምናለን። እኛም ከጎናቸው እንሰለፍ። በጸሎታችን እንደግፋቸው፤ እንደ አቅማችን እናግዛቸው።

እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑ የሚታወቀው ለወገን ስንደርስ ነው። ሆስፒታሎች፣ የሕክምና ቦታዎች የሰው ልጅ ሕመምና ስቃይ እንዲቀንስ ወይንም እንዲጠፋ የሚተጉ ተቋማት ናቸው። መሠረታቸው የጥንት የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው። በተለይም በአራተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘናዚያንዙ “ለድሆች ፍቅር” በሚለው መልእክቱ የታመሙትን መርዳት ማለት በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ለተፈጠረው የሰው ልጅ ክብርን መስጠት እንደሆነ ያስተምራል። ሕሙማንን መንከባከብ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሰጠው አደራ እንደሆነ ያሳስባል። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፣ ቅዱስ ባሲልዮስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ቄርሎስ ተመሳሳይ መልእክቶችን አስተላልፈዋል፤ ለሕሙማን መድረስ ትልቅ መንፈሳዊ ተግባር እንደሆነም አስተምረዋል።

ወረርሽኙን ለምግታት ሲባል በቤታችን ተቀምጠናል። ይህ ሁኔታ ትዕግሥታችንን ሊፈታተን ይችላል። ነገር ግን ከአዲሱ ፈታኝ ሁኔታ በእግዚአብሔር ጸጋ በጎ ነገርም ሊወጣ ይችላል። ይህ እንዲሆን ሐሳባችንን መሰብሰብ እና ማሰላሰል ያስፈልገናል። ተረጋግቶ በመቀመጥ፣ በጽሞና እና በጸሎት ብዙ ማትረፍ እንችላለን። ወቅቱን የሕይወትን ትርጉም የምንመረምርበት አጋጣሚ እናድርገው። ለንስሐ፣ ለመለወጥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰላሰል እና ለፈጠራ እንጠቀምበት። ልጆች ሳይሰላቹ የሚማሩበትን መንገድ እንፈልግ።

ቤታችን ፍቅርን የተማርንባት፣ ያደግንባት፣ ማኅበራዊ ሕይወትን የለመድንባት መጠለያችን ናት። ፍቅር የነገሠባት ቤት ትሞቃለች። ልጆችን ታፋፋለች። ውሎዉን ታስውባለች። ለጸሎት ትመቻለች። የወቅቱን ፈተና ለመቋቋም በቤታኝን የፍቅርን ምድጃ እናንድድ። ምክንያቱም ፍቅር የሞትን ያህል ትጠነክራለችና (መሓልየ መሓልይ 8:6)። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ፍቅር ከሞትም እንደጠነከረች እናያለን። በከርስቶስ ትንሣኤ ሞት ድል ተነሣች ተገደለች። እንግዲህ ፍቅርም በቤታችን ተዳፍና እንደሆን፣ አመዱን በማንሣት ፍሙን አቀጣጥለን ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን እናስተናግድባት። ፍቅር አንድነትን ታጠነክራለች። ፍቅር ወደ ጸሎት ትመራለች። “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ” (ማቴዎስ 18፣20) ያለው የክርስቶስ ቃል በእምነት በተስፋ እና በፍቅር በተሰበሰቡ ቤተሰቦች ውስጥ እውን ይሆናል። በፍቅር ቤትና ቤተሰብ የተሳሰሩ ናቸው። ቤተሰብ የማኅበረሰብም የቤተ ክርስቲያንም መሠረት የሚሆነው በመለኮታዊ ፍቅር ሲገነባ ነው።

ቤት ይህንን የመሰለ ልዩ ስፍራ ካላት፣ መጠለያ የሌላቸው ወገኖች እንዴት ይኖሩ ይሆን? በሐሳብ እና በተግባርስ እንዴት ከጎናቸው መቆም እንችላለን? በተቀናጀ መልኩስ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን? ለጎዳና ተዳዳሪዎች ሰው እና ማኅበረሰብ ያልሰጣቸውን ማን ይሰጣቸዋል? የከዋክብት፣ የፀሐይ እና የጨረቃ ውበት የሚታወቀው መጠለያ ላለው ነው። መጠለያ የሌለው ግን የሚጋፈጠው ከሐሩር እና ከብርድ ጋር ነው። ተፈጥሮን ለማድነቅም መቻሉ ያጠራጥራል። መጠለያ የሰጠንን አምላክ ስናመሰግን መጠለያ ለሌላቸው እንድናስብ ያስፈልጋል። ያልደረስንላቸው ወገኖች ሰብአዊ ክብር አላቸው። በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጥረዋል። “ለእነኚህ ለታናናሾቹ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።” (ማቴዎስ 25:40) የሚለው ክርስቶስ ለእነርሱ በተለየ መልኩ ቅርብ መሆኑን ነግሮናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑትን ወገኖቻችንንስ እንዴት እንድረስላቸው? ሁሉም የሚቻለውን ይወጣ፤ የሚሰጠው የሌለው የሚመስለው እንኳ ቢኖር ጊዜውን ማካፈል አይችልም ብንል እራሳችንን እንበድላለን። የሰው ልጅንም ማኅበረሰባችንንም እንጎዳለን።

      እንዲሁም አንድ መጽናናት የሚያሻት፣ የረሳናትና በጣም የምንበድላት እናት አለችን፤ የእርሷ እና የድሆች እንባ ወደ ሰማይ ይጮኻል። እርሷ እናታችን ምድር ነች። “ድሃን የሚንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል” (ምሳሌ 17:5) ተብሎ እንደ ተጻፈው፣ እርሷንም የሚበድል ፈጣሪዋን ያስቀይማል። ብፁዕ ወወቅዱስ  ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በሚለው መልእክታቸው በቁጥር ፪ ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል፣

በኃጢአት በቆሰለው ልባችን ውስጥ ያለው ሁከት ደግሞ በአፈር፣ በውሃ፣ በአየርና በሁሉም የሕይወት ዓይነቶች ውስጥ በሚታዩ የሕመም ምልክቶች ይንጸባረቃል። ለዚህም ነው ጫና የበዛባትና የተራቆተች ምድር ራስዋ፣ እጅግ ከተረሱና ከተበደሉ ድሆቻችን መካከል አንድዋ የሆነችው።

በእርግጥም ምድር እየተሰቃየች ነው። ከበፊቱ የበለጠ የተሰቃየችው በሰው ልጆች ስግብግብነትና ትዕቢት ነው። ሰው ለራሱ ብቻ የሚያስብ ፍጡር ሆነ። ሰው ባለዐደራ መሆኑን ረስቶ እንደፈለገ ምድርን በዘበዘ። ሆኖም በአንድ አንድ አገር ስለእርሷ ክብር ሁሌ ይነሣል። የልደት በዓልም ሆነ የጋብቻ፣ የትምህርት ምረቃም ሆነ ልዩ ክብረ በዓል ሲከናወን ስለእርሷ ክብርና ፍቅር ዛፍ ይተከላል። እንዲያውም በልደት በዓል፣ በዓመቱ ቁጥር ልክ ነው ዛፍ የሚተከለው። እኛም ዘንድ ይህ ልምድ ቢዘወተር ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። የሠርግ በዓል በዛፍ ተከላ ቢታጀብ ምድራችንን ይለውጣል፤ የጤናም ምክንያት ይሆናል።

ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የሁላችንም ቤት” ብለው የሚጠሯትን ምድርን እንድንንከባከብ ዘወትር አበክረው በአደራ ጭምር ያስታውሱናል። የአካባቢ እንክብካቤ ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀውን ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ለመላው ዓለም ካበረከቱም እነሆ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን “የውዳሴ ለአንተ የአካባቢ እንክብካቤ ሳምንት” በሚል ከግንቦት 8 እስከ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. አክብረናል። መላው ዓለምም ይህ ሐዋርያዊ መልዕክት ወቅቱን ያገናዘበ እጅግ ጠቃሚ ሰነድ መሆኑን በመመስከር እየተጠቀመበት እና ምስጋናውንም እያቀረበ ይገኛል።

በሀገራችንም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ችግኞችን በመትከል እና በመንከባከብ እንድንተጋ የመኖሪያ አካባቢያችንንም በማስዋብ ምድርን እንድንጠብቅ አብነት በመሆን ዘወትር ያሳስቡናል። በዘንደሮው ክረምትም “አረንጓዴ አሻራ” በሚል መሪ ቃል በየመኖሪያ አካባቢያችን እና በምንችልበት ስፍራ ሁሉ ችግኞችን እንድንተክል ጥሪ አስተላልፈውልናል። እንግዲያውስ መምህሩን ሰምቶ ለመተግበር እንደሚፈጥን ትጉህ ደቀ መዝሙር ዛሬ ነገ ሳንል፣ የክረምቱም ጸጋ ሳያልፈን፤ በመጪዎቹ የክረምት ወራት ብዙ ዓይነት ዛፎችን ተክለን እናታችንን ምድርን ብናጽናናት በረከትን እና ፈውስን እናገኛለን።  

የመንፈስ ቅዱስን ብርሃን እንጠይቅ። ታላላቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችን እናስታውስ። ዓለም ሲፈጠር በውሃ ላይ ሰፍፎ የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ይህንን ወረርሽኝ አስወግዶ የፍጥረትን ዝማሬ የምንዘምርበትን ጸጋ ይስጠን። ሕይወት ሰጪ መንፈስ ቅዱስ ሕሙማንን ይፈውስልን። የቃል ሥጋ መሆን ምክንያት የሆነው ጰራቅሊጦስ ወደ ፈዋሹ ወደ መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቅርበን። በበዓለ ሃምሣ በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ኃይሉን፣ ጽናቱን፣ ብርሃኑን እና ፍቅሩን ያፍስስልን። በተስፋ እንመላለስ፤ በተስፋ ድነናልና (ሮሜ 8:24)::

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤” (2ቆሮ1:3) ብሏል። ይኸው መልእክቱ ለእኛም ትልቅ ትርጉም አለው። ልዑል እግዚአብሔር መጽናናቱን እና ፈውሱን ለቤተ ክርስቲያናችን ፣ ለመላ አገራችን እና ለመላው ዓለም ያምጣልን!

ጌታ ሆይ፣ በጨለማም ብንገኝ “አንተ የሕይወት ምንጭ ነህ፤ በአንተ ብርሃን ብርሃንን እናያለን (መዝ 36:9)”።

መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. (ማርች ሃያ ሰባት 2020) ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለሮም እና ለመላው ዓለም ምእመናን መልእክት አስተላልፈው ነበር። በመልእክታቸውም የእምነት ኃይል ከፍርሃት ነፃ አውጥቶ ተስፋን እንደሚሰጠን ገልጸዋል። “ለምን ትፈራላችሁ፣ እምነት የላችሁምን” (ማቴዎስ 8:26) የሚለውን የክርስቶስን ቃል እየጠቀሱ የዓለምን ምእመናን በሙሉ ለጌታ ዐደራ ሰጥተዋል። የክርስቲያኖች ረዳት እና የሕሙማን ፈውስ አንዲሁም በማዕበል ውስጥ የምታበራ ኮከብ የሆነችውን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ጠይቀዋል።

“ጌታ ሆይ! ዓለምን ባርክ፣ ለሰውነታችን ጤናን ስጠን፣ ልባችንን አጽናና። “አትፍሩ አልከን”፤ ነገር ግን፣ በእምነት አልጠነከርንም፣ ስለዚህም እንፈራለን፤” ጌታ ሆይ፣ አንተ ግን ለማዕበል አሳልፈህ አትሰጠንም። በድጋሚ፣ “አትፍሩ በለን” (ማቴዎስ 28:5)፤ እኛም፣ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ስጋታችንን በሙሉ በአንተ ላይ እንተዋለን፤ ምክንያቱም አንት ስለእኛ ግድ ይልሃልና” (1 ጴጥሮስ 5:7)፡፡ አሜን፡፡

የጰራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ

ብጽዕ ካርዲና ብርሃነየሱስ

ሊቃነ ጳጳስት ዘካቶሊካዊያን

የኢትዮጲያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባሄ ፕሬዚዳንት

ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

05 June 2020, 10:29