ፈልግ

የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የንግደት ሥፍራ፤ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የንግደት ሥፍራ፤  

ወደ ሉርድ እመ ቤታችን ቤተ መቅደስ የሚደረግ ጉዞ በነሐሴ ወር የሚጀምር መሆኑ ተገለጸ።

ሕሙማንን ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚያደርስ የመንፈሳዊ ጉዞ አገልግሎት፣ በነሐሴ ወር የሚጀምር መሆኑን የጉዞ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ጀምሮ፣ በተለያዩ ሕመሞች የሚሰቃዩ ሰዎችን በፈረንሳይ ወደሚገኝ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በማድረስ የሚታወቀው ድርጅት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አቋርጦት የነበረውን መንፈሳዊ ጉዞ ከመጭው ነሐሴ ወር ጀምሮ የሚጀምር መሆኑን አስታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

መንፈሳዊ ጉዞ አስተባባሪ ድርጅቱ የመጀመሪያውን ንግደት የጀመረው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ መሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1947 ዓ. ም. አውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ መረጋጋትን ያገኘበት፣ መዕመናንም እምነታቸውን መግለጽ የጀመሩበት ወቅት መሆኑ ሲታወስ መንፈሳዊ ጉዞ አስተባባሪ ድርጅቱ በራሱ ሠራተኞች እገዛ ሕሙማንን ወደ ቅዱስ ሥፍራዎች ማድረስ መጀመሩ ይታወሳል።

የ2020 ዓ. ም. የንግደት ቀናት መርሐ ግብር፣

መንፈሳዊ ጉዞ አስተባባሪ ድርጅቱ ከ73 ዓመት በፊት፣ ከነሐሴ 14-17 ድረስ ያደረገው ንግደት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተባበረው ታሪካዊ ንግደት መሆኑ ሲታወስ፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳያቋርጥ መንፈሳዊ ጉዞን ሲያስተባብር መቆየቱ ይታወሳል። በመጭው ነሐሴ ወር የሚጀምረው ይህ መንፈሳዊ ጉዞ፣ በዓለማችን የሚገኙ የሕክምና ተቋማት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጠቁት ሕሙማን የሕክምና ዕርዳታን በማቅረብ ላይ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1947 ዓ. ም. እንደተደረገው፣ ከነሐሴ 14-17 ቀን የሚደረግ እና በቀጣይ ወራትም ማለትም በመስከረም፣ ጥቅምት እና ታኅሳስ እንደሚደረግ በመርሃ ግብር የተቀመጠ ጉዞ መሆኑን አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

ንግደቱ በመንፈሳዊ ስሜት ይጀምራል፣

በፈረንሳይ ወደሚገኝ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞ ለመጀመር በታላቅ ምኞት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ጽሕፈት ቤቱ፣ ለሕሙማን በሚደረጉ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች እና ጸሎቶች የሚታገዝ መሆኑን አስረድቷል። ለሕሙማን የሚሰጥ ይህ ሐዋርያዊ አገልግሎት በመንፈሳዊ ጸጋዎች የተሞላ አገልግሎት መሆኑን ያስረዱት፣ የጉዞ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ አንጀሊኖ፣ ይህን ጎዞ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መልስ ለመጀመር በጉጉት ሲጠበቅ የቆዩት እንደሆነ አስታውሰው አገልግሎቱ በ1930ቹ በብጹዕ አቡነ አሌሳንድሮ ራስቴሊ መጀመሩን እና ከዚያን ጊዜ ወዲህ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የታነጹ ቤተ መቅደሶችን መሳለም ለሚፈልጉ ሕሙማን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ ካህናት እና በጎ ፈቃደኞች፣ በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መንፈሳዊ ተጓዦን አገልግሎት ሲያበረክት መቆየቱን አስረድተዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወቅት የሚደገም ጸሎት፣

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቤርናዴት መገለጿ ሕይወት ለዕለታዊ መንፈሳዊ ጉዞ ትልቅ ብርታትን እንደሚሰጥ ያስረዱት ብጹዕ አቡነ አንጀሊኖ “ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ በናፍቆት ስንጠብቀው የቆየ የተስፋ እና የፍቅር ጉዞ ነው” በማለት ገልጸውታል። “ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚደረግ ንግደት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደ ፊትም የተስፋ ጎዞ ነው” ብለው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለማችንን እያሰቃየ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት ወደ ቤተ መቅደሷ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ የተስፋ ጉዞ እንደሆነ አስረድተው “ይህ መህፈሳዊ ጉዞ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ሕመም እና ስቃይ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግር ስር በማቅረብ የመማጸኛ ጸሎታችንን የምናቀርብበት ጉዞ ይሆናል” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ፓውሎ አንጀሊኖ አስታውቀዋል።             

18 June 2020, 19:29