ፈልግ

የሰኔ 21/2012 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር የሰኔ 21/2012 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር 

የሰኔ 21/2012 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር

የእለቱ ምንባባት

1.      ሮሜ 5፡12-21

2.    3ኛው ዮሐንስ 1፡1-15

3.    የሐዋርያት ሥራ 16፡1-13

4.    ማቴዎስ 22፡1-22

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ

ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ። “እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ። “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። “ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።

“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም። “ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ግብር ስለ መክፈል

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ። 

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ከሁሉም በማስቀደም መግባታችንን እና መውጣታችንን በጸጋው እየባረከ በሰላም እና በጤና እንድንጓዝ የሚያደርገንን እግዚኣብሔር አባታችን ቅዱስ ስሙ የተባረከ ይሁን፣ ምሕረቱን እየሰጠን እኛም እርስ በእርሳችን ምሕረት አድራጊዎች እንድንሆን የሚመክረን ልጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን፣ በሐዘናችን፣ ተስፋ በምንቆርጥባቸው ጊዜያት ሁሉ ከእኛ ጋር በመሆን የምያጽናናን መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ለእርሱ ይሁን።

የዛሬው ሰንበት የእግዚኣብሔር ቃል በቅዳሚነት የተወሰደው ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች ከጻፈው መልዕክቱ ከምዕራፍ 5:12-22 ላይ የተወሰደ ሲሆን ሞት በአዳም ሕይወት ደግሞ በክርስቶስ እንደተሰጠን የሚገልጸው ነው። በሁለተኛነትም ከሐዋሪያት ሥራ 16:1-13 ላይ የተወሰደው ጢሞቴዎስ ከሐዋሪያው ጳዎሎስና ከሲላስ ጋር ለሐዋሪያዊ ተግባር መሰማራቱን የሚገልጽ ነው። የእለቱ ቅዱስ ወንጌል የተወሰደው ከማቴዎስ ወንጌል 22:1-22 ላይ የተጠቀሰው በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌን የሚገልጸው እና የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚኣብሔርን ደግሞ ለእግዚኣብሔር መስጠት ይገባል የሚለው የኢየሱስ ቃል የሚገኝበት ነው።

በሀገራችንም ይሁን በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሰርግ ግብዣ በሚዘጋጅበት ወቅት ሁሉ እንደየ ባሕሉ እና እንደየወጉ፣ እንደየ አቅማችን የሰርግ ልብስ በመልበስ፣ አምረን እና ደምቀን፣ የሙሽራውን እና የሙሽሪቷን በዓል ለማድመቅ የታችላንን ሁሉ በማድረግ ወደ ሰርጉ ግብዣ መሄድ የተለመደ ነው። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት የሰርግ እንድምተኞች በአብዛኞቹ ተገቢ የሆነ የሰርግ ልብስ የለበሱ ሲሆን ነገር ግን አንድአንዶቹ በተለይም ከጎዳና ላይ የተጠሩ ሰዎች በቂ የሆነ ዝግጅት ሳያደርጉ በስርጉ ግብዣ ላይ መገኘታቸው ተጠቅሱዋል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እና ተገቢ የሆነ የሰርግ ልብስ ያለበሰው ሰው የተዘጋጀለትን የስረግ ልብ አለመልበሱ የጋባዡን ክብር የሚነካ ጉዳይ ነው። የሰርግ ልብስ የልብን መዘጋጀት ያመለክታል። ይሄው በክርስቶስ ማመን እና ከእርሱም ጸጋ የተነሳ ዘወትር ታዛዥ ሆኖ መገኘትን ያሳያል። ሁላችን ራሳችንን እንድንመረምር ክርስቶስ የሰርግ ልብስ ያለበሰውን ሰው ምሳሌ ተጠቅሞ ለእኛ ሲናገር ይደመጣል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዛሬው ቀን ኢየሱስ ለእኔና ለእናንተ ያዘጋጀው ለላው መልእክት ይህ ነው። ጥልቅ የሆነ የልብ ዝግጅት እንድናደርግ፣ ሁል ጊዜም ቢሆን በእግዚኣብሔር ጸጋ እና ክብር የተሞላ ሕይወት እንዲኖርን፣ ከክፉ ነገሮች ሁሉ እንድንርቅ፣ ኅጢኣታችንን በንስሐ እንድናጥብ እና ለኢየሱስ ክብር የተዘጋጀ ሕይወት ይኖረን ዘንድ ጌታ ጥሪ ያደርግልናል።

ሁልጊዜም ቢሆን ቸልተኝነት የሚታየው እና የሚመጣው ከእኛው ከሰዎች በኩል ነው እንጂ እግዚኣብሔር ሁሌም መሐሪ እና ይቅር ባይ ቁጣው የዘጌየ በምሕረት የተሞላ ነው። ርሰዕ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአንድ ወቅት የእግዚኣብሔርን ማሐሪነት እና የእኛን ግድየለሽነት በተመለከተ እንዲህ ብለው ነበር “እኛ ነን እንጂ እግዚኣብሔርን ማረኝ ብለን መጠየቅ የምንሰለቸው፣ እግዚኣብሔር ግን በፍጹም ምሕረትን ለእኛ ከማድረግ ሰልችቶ አያውቅም” ማለታቸው ይታወሳል። የእግዚኣብሔር ልብ የምሕረት ልብ ነው፣ እግዚኣብሔር የጸጋ እና የበረከት አምላክ ነው፣ ሁል ጊዜ መዘጋጀት እና የእርሱን ክብር ተላብሰን መኖር ያስፈልገናል። በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ የተጠቀሰው የአዳም እና የሔያዋን ታሪክ ይሄኑ የሚያጠናክር ነው። አታድርጉ የተባሉትን ባደርጉ ጊዜ የእግዚኣብሔር ክብር ራቃቸው፣ እግዚኣብሔርን ሸሹ. . .

እግዚኣብሔር ከእኛ የሚጠብቀውን መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ ልባችንን ከኃጢኣት የማናነጻ ከሆነ እግዚኣብሔር ብዙ ይታገሰናል ነገር ግን በሰርጉ ግብዣ ምሳሌ ላይ እንደ ተጠቀሰው በቂ ዝግጅት የማናደርግ ከሆነ ራሳችን በሰራነው ኃጢኣት ተጠላልፈን የምንወደቀ ራሳችን ነን ““ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና” (ማቴዎስ 22:13)። ይህ ቃል የሚያስረዳን በኃጢኣታችን ተጸጽተን ንስሐ የማንገባ ከሆነ፣ ለእግዚኣብሔር የተገባ ሕይወት ይማንኖር ከሆነ የሚጠብቀንን ከባድ የሆነ ቅጣት የሚያሳይ ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በቀጣይነት የምናገኘው ፍሬ ሐስብ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር” የሚለው ቃል ነው። ፍሪሳዊያን የሮማዊያንን አገዛዝ በብርቱ የሚቃወሙ ጠንካራ ብሔርተኞች ነበሩ፣ በአንጻሩም የሂሮድስ ወገኖች የተባሉትና ጥላቻ ያተረፉት የሂሮድስን ሮማዊ አገዛዝ ይደግፉ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ፈሪሳዊያን ኢየሱስን በሚናገረው ቃል ጠልፈው ለመያዝ የሂሮድስ ወገኖችን እርዳታ ስላስፈለጋቸው በሽንገላቸው ወደ ወጥመዳቸው እንዲገባ ካመቻቹ ቡኃላ “ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” በማለት ድንገተኝ የሆነ ጥያቄ ሰነዘሩለት። “መክፈል አይገባም” ብሎ ቢመልስ ኖሮ የሂሮድስ ወገኖች በሮማዊያን እንደራሴዎች ፊት ለፊት ከሰውት በመንግሥት ተቃዋሚነት የሞት ፍርድ ባስበየኑበት ነበር፣ መክፈል ይገባል ብሎ ቢመልስ ደግሞ ለገዛ ወገኖቹ ታማኝ እንዳልሆነ በመቁጠር በሕዙቡ ዘንድ ልያጥላሉት ምክንያት ፈልገው ነበር።

ነገር ግን የሰውን ልብና ኩላሊት ሳይቀር መርምሮ የሚያውቀው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ተንኮላቸውን፣ ወጠዳቸውን ጠንቅቆ በአምላክነት ኃይሉ ስለተረዳ በሳንቲሙ ላይ ያለው ምስል የቄሳር በመሆኑ የተነሳ የቄሳርን ለቀሳር የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር መስጠት ይገባል በማለት ይመልስላቸዋል።

የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር መስጠት ይገባል የሚለው ቃል እኛ ዛሬ ሁላችን በሕይወታችን ልንተገብረው የሚገባን ትሕዛዝ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚኣብሔርን ለእግዚብሔር ብሎ መናገሩ የሚያሳየው በቄሳር እና በእግዚኣብሔር መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት እንዳለ እና ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል ሁሉ የእግዚኣብሔር ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ የተለየ መሆኑን ለማመልከት ነው።

ከዚህ የኢየሱስ ቃል ዛሬ እኛ ምን እንረዳለን? በሕይወታችን ስንት ጊዜ ነው የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር የዓለምን ለዓለም ሰጥተን የምናወቀ ስንት ጊዜ ነው? ስንት ጊዜ ነው የዓለምን ነገሮች እና የእግዚኣብሔርን ነገር መለየት አቅቶን ስንዘበዝብ የምንገኘው?

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እየታየ የሚገኘው ትላቁ ፈተና ይሄው ጉዳይ ነው፣ የዓለምን እና የእግዚኣብሔርን ነገሮች በጣም አቀላቅለናቸው፣ እግዚኣብሔርን በማይገባው ስፍራ አስቀምጥነው። ዛሬ እኔ እና እናንተ ሕይወታችንን በመፈተሽ የተኛው የቄሳር የተኛው ነገር ደግሞ የእግዚኣብሔር መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል።

ኢየሱስ የቀሳርን ለቄሳር ብሎ መመለሱ አዎንታዊ የሆነ እድምታ አለው። ይህም እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር በምንኖርበት ወቅት ሁሉ ለማሕበራዊ ዋትና የበኩላችንን አስተዋጾ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ፣ ክርስቲያን እንደ መሆናችን መጠን ክርስቲያናዊ እሴቶችን የተላበሱ አስተዋጾ ለማኅብረሰቡ እና ለሀገር ማበርከት እንደ ሚገባ፣ ሰላም እና ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የየበኩላችንን ማድረግ እንድሚኖርብን፣ ለሌሎች የተገባውን ነገር ለራሳችን ጥቅም ማዋል እንደ ሌለብን፣ የሚያሳስብ ትልቅ መልእክት ያዘለ አነጋገር ነው። በአንጻሩም የእግዚኣብሔርን ለእግዚኣብሔር መስጠትም ተገቢ እንደ ሆነ ኢየሱስ ይናገራል። በእነዚህ ሁለት ሀረጎች መካከል ያለው ግንኙነት የሚያሳየው ኢየሱስ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚገባቸውን መስጠት እንዳለብን የሰዎችን ሀቅ መንካት እንደ ሌለብን የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳስይ መልኩ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለብን ይገልጻል። እዚህ ጋር ባልነጀራህን  እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ እግዚኣብሔር አባትህንም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነብስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደድ የሚለውን ያሰማል። ባልንጀሮቻንን የምንወደ ከሆነ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ እንሰጣቸዋልን እንጂ አንነጥቃቸውም፣ እግዚኣብሔርን የምንወደ ከሆነ ደግሞ እርሱን በሕይወታችን እናከብረዋለን ማለት ነው።

በመንፈሳዊ ሕይወታችን እየጠነከርን እንድንሄድ፣ የእግዚአብብሄርን ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር መስጠት የምንችልበትን ጸጋ ከልጇ ዘንድ እንድታሰጠን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት ልንማጸን ይገባል።

ምንጭ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት 

 

27 June 2020, 11:10