ፈልግ

በጣሊያን ብሬሻ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ለሕሙምኝ የሕክምና ዕርዳታ በመስጠት ላይ፤ በጣሊያን ብሬሻ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ለሕሙምኝ የሕክምና ዕርዳታ በመስጠት ላይ፤ 

የጣሊያን ጳጳሳት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት መንፈስዊ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል አሉ።

በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የሐዋርያዊ አስተምህሮ፣ የወንጌል ምስክርነት እና የትምህርተ ክርስቶስ አስተባባሪ ምክር ቤት፣ ያለፉትን ወራት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲኖ ቡልጋሬሊ፣ በዚህ አስጨናቂ የኮሮና ቫይረስ ወቅት ቤተሰባዊ አንድነታችንን ማሳደግ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ባለፉት ወራት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ላደረሰብን ህመም፣ ሽንፈት እና መቅበዝበዝ ትርጉም መስጠት ይቻላል ያለው የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤው በመልዕክቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ በወንጌል አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አባቶች በምዕመናኑ መካከል የዘሩትን ተስፋ በማስታወስ “በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሳ” ባለው መልዕክቱ በሕይወት፣ በሞት እና በስቃይ መካከል ያለውን ጥልቅ ትርጉም በማስተንተን፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ተማሪ፣ ሕጻን፣ ሠራተኛ፣ የቤተክርስቲያን አባት፣ ሐኪም፣ የቤት እመቤት፣ በጎ ፈቃደኛ እና ጸሐፊ፣ በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው እያሳለፈ የሚገኘውን አስጨናቂ ጊዜን ማስታወሱ ታውቋል።

ጊዜው የብርሃነ ትንሳኤው ምስጢር የሚገኝበት ነው፣

በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የትምህርተ ክርስቶስ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲኖ ቡልጋሬሊ፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መልዕክት በመጥቀስ እንደተናገሩት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ዕርዳትን በመፈለግ ጥያቄን የሚያቀርቡ ሰዎች ማድመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አክለውም የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ በመልዕክቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እና ብርሃነ ትንሳኤው ጋር በማዛመድ መንፈሳዊ ትርጉም የሰጠው መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲኖ ቡልጋሬሊ በማከልም “እጅግ አስጨናቂ ለሆነው ለኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ጊዜ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጉባኤ የሰጠው ትርጉም፣ የስርዓተ አምልኳችን እና የክርስትና ሕይወት ልምዳችን ማዕከል መሆኑን ይገልጻል” ብለው ይህንንም ከስቅለተ ዓርብ ጋር አመሳስሎታል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው ስቃይ እና ሞት በኋላ ትንሳኤ አለ፣

ከስቅለተ ዓርብ በኋላ ቅዳሜ ዕለት የጸጥታ ጊዜ መሆኑን ያስታወሰው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መልዕክት፣ ይህ ጊዜ ብርሃነ ትንሳኤውን የምንጠብቅበት ጊዜ መሆኑን አስታውሷል። የጉባኤው መልዕክት በማከልም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ወደ ቀድሞ ሕይወት መመለስ ቀላል እንዳልሆነ አስታውቆ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እና መካነ መቃብር ሁሉም ሰው በሕይወቱ ለውጥን ማምጣት እንዳለበት፣ በዘመናችን በሰዎች ላይ እየደረሰ ላለው ስቃይ ጆሮና ልብን መስጠት እንደሚገባ፣ በሰዎች መካከል መለኮታዊ ፍቅርን በመግለጽ የሰላም፣ የእኩልነት እና የቸርነት ተግባርን ማከናወን እንደሚገባ አሳስቧል።

የተስፋ መንገድ፣

በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መልዕክት ውስጥ መልካም አቅጣጫ እንደተቀመጠ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲኖ ቡልጋሬሊ፣ አማኝ ሆነ አማኝ ያልሆነ ሁሉ በልቡ ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፥ የሕክምና ባለሞያዎች እና የክርስቲያን ማኅበረሰብ በሙሉ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያደረጉትን የቸርነት ተግባር፣ በእያንዳንዱ ሰው በኩል በተግባር እንዲገለጽ የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ አስቸጋሪ ጊዜ ካሳየን የተስፋ ምልክቶች መካከል አንዱ፣ በኅብረት ሆነን ቤተሰባዊንትን ለማሳደግ በምንችልበት መልካም ጎዳና ላይ መሆናችንን ነው በማለት በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የትምህርተ ክርስቶስ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቫሌንቲኖ ቡልጋሬሊ አስረድተዋል።

30 June 2020, 18:47