አፍሪካ እና አውሮፓ ተባብረው ሰብዓዊ ክብርን እንዲያስጠብቁ፣ ኅብረትንም እንዲፈጥሩ ጥሪ ቀረበ።
የአፍሪካ እና የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ሆነው፣ ሁለቱ አህጉራት ሕዝብን ያማከለ ፍትሃዊ እና ሃላፊነት ያለበት ወዳጅነት እንዲፈጥሩ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ይህን ጥሪ ያቀረቡት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መጭው ጥቅምት ወር 2020 ዓ. ም. ሊካሄድ በታቀደው 6ኛ ለመሪዎች ጉባኤ መሆኑ ታውቋል።
የቫቲካን ዜና፤
የጋራ መሠረት ያላቸው ሁለቱ አህጉራት በመልክዓ ምድር አቀማመጥ ቅርበት ያላቸው ፣ አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቤተሰቦች እና በማኅበረሰቦች መካከል፣ በተለይም ለችግር ተጋላጭ በሆኑ አቅመ ደካሞች ላይ ከፍተኛ ጭንቀትን ያስከተለ መሆኑን ብጹዓን ጳጳሳቱ አስረድተዋል። የአውሮፓ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት እና የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚዬም በጋራ ሆነው፣ የሁለቱ አህጉራት መሪዎች በሚያደርጉት 6ኛ ጉባኤ ላይ፣ ወደ ፊት ሁለቱ አህጉራት ሊኖራቸው የሚገባውን ወዳጅነት በማስመልከት ሃሳባቸውን ለማቅረብ መወሰናቸው ታውቋል።
አውሮፓ እና አፍሪካ የአንድነት አንቀሳቃሽ ናቸው፣
የአውሮፓ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆነሪች እና የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚዬም ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከለንቱባ ወይድራዎጎ፣ በዋና መቀመጫቸው ብራሴልስ እና አክራ ሆነው የአውሮፓ እና የአፍሪካ ፖሊሲ አውጭዎች ለጉባኤው በሚያደርጉት ዝግጅት ምስጋናቸውን ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ጉባኤው ከመምጣቸው በፊት ዝግጅታቸው መሠረታዊ በሆነው ሰብዓዊ ክብር፣ ሃላፊነት እና አንድነት ላይ እንዲሆን ብለው ከዚህም በተጨማሪ ለድሆች የተለያዩ አማራጮችን ማመቻቸት፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ጥበቃን እና እንክብካቤን ማድረግ እና ማኅበራዊ ጥቅምን ማስቀደም በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲሰጡባቸው በማለት ሃሳባቸውን ገልጸው፣ አፍሪካ እና አውሮፓ ከተባበሩ ሁሉ አቀፍ ትብብርን የሚያሳድግ እቅድ መዘርጋት እንደሚችሉ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል። የአውሮፓ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆነሪች በበኩላቸው የአውሮፓ አገሮች ሃላፊነት ሰላምን እና ብልጽግናን ቅርባችን ከሆኑት የአፍሪቃ አገሮች ጋር መጋራት ነው ብለዋል።
ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ፣ ሃላፊነትን መውሰድ እና ኅብረትን መፍጠር፣
ከመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ “በቀኑ ፍትህ ያብባል፣ ሰላምም ይበዛል” የሚለውን ጥቅስ በመውሰድ የመልዕክታቸው አርዕስት ያደረጉት ሁለቱ ብጹዓን ካርዲናሎች በሁለት አህጉሮች መካከል ያለውን የፖለቲካ እና ኤኮኖሚ ግንኙነቶችን ጨምሮ ሌሎች ግንኙነቶችን እንዲያሳድጉ፣ በተለይም ፍትሃዊ እና ኃላፊነት የተሞላበት አጋርነት፣ ሰዎችን ማእከል የደረገ ግንኙነት እንዲኖር በማለት ሃሳባቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካና የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት አክለውም “ለሰው ልጆች ልማት ፣ ለሥነ-ምህዳር ፣ ለሰላም፣ ከቦታ ቦታ ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ደህንነት ትኩረትን የሚሰጥ አጋርነት እንዲኖር ያስፈልጋል ብለዋል።
ለችግር የተጋለጡ አቅመ ደካማ ማኅበረሰብ አሳሳቢነት፣
የሁለቱም አህጉራት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስቀድሞም ቢሆን የነበረውን የግለሰቦች ፣ የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ ጭንቀቶችን እንደምትጋራ የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲታከልበት ድህነት፣ ረሃብ፣ የመሠረታዊ የሆኑ ማኅበራዊ አገልግሎቶች መጓደል፣ ሙስና ፣ አመጽ ፣ የሽብር ጥቃቶች፣ ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የሃይማኖት ማህበረሰቦች ላይ የሚደርስ ስደት እና መከራ፣ የተፈጥሮ ሃብት ብዝበዛ እና በአካባቢ ላይ ውድመትን ማስከተል እየተስፋፋ ሊመጣ እንደሚችል አስረድተዋል። የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚዬም ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከለንቱባ ወይድራዎጎ በበኩላቸው የአፍሪካ አገሮች በራሳቸው ኤኮኖሚ እድገትን ማምጣት እንዲችሉ የዕዳ ጫናቸው ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝላቸው በማለት ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ከ25 ዓመታት በኋላ አሁንም የተስፋ ምልክት ናት፣
ሁለቱ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ባወጡት መግለጫው “የአፍሪካ ቤተክርስቲያን” የሚለው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ድህረ-ሲኖዶስ ሐዋርያዊ መልዕክት የሰጠው ተስፋ ከ25 ዓመት በኋላም የሚያበረታታ እና በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማሸነፍ ኃይል የሚሰጥ መሆኑን አስታውሰዋል። የሁለቱ አህጉራት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚደንቶች፣ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆነሪች እና ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከለንቱባ ወይድራዎጎ የጋራ መልዕክታቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት እንደገለጹት፣ የሰብአዊ ክብር መርሆዎች እና እሴቶች፣ አንድነት ፣ ለድሆች የሚቀርቡ አማራጮች፣ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደረግ ፍትሃዊ ክፍፍል፣ ሁለ ገብ የሰው ልጅ ልማትን ማስፋፋት፣ ተፈጥሮን ሃላፊነት ባለው መንገድ መጠቀም እና ማስተዳደር፣ ማህበራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ እነዚህ በሙሉ ትክክለኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ለማድረግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።