ፈልግ

ወጣት ስደተኞች በሊብያ ወጣት ስደተኞች በሊብያ  

የወጣቶች ስደት በሀገራችን ኢትዮጵያ

መግቢያ

ክፍል አንድ

ከዚህ በመቀጠል ወቅታዊውን የወጣቶች ሁኔታ የምያንጸባርቅ ትምህርት አዘል መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ። ሐሳቤን በሚገባ ለማስረዳት እና ለማስረጽ ይረዳኝ ዘንድ እንደ መንደርደሪያ ሐሳብ የምጠቀመው ባለፈው አመት ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 17/2011 ዓ.ም ድረስ በቫቲካን የተካሄደው 15ኛው የብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ከተጠናቀቀ በኋላ የዚህ ጉባሄ ማጠቃለያ ሐሳብ በላቲን ቋንቋ “Christus Vivit” በአማርኛው “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርእስት የተዘጋጀ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 16/2011 ዓ.ም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ተፈርሞ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህ መልዕክቴ በዚሁ በድህረ-ሲኖዶስ ምልከታ ለወጣቶች እና ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅዱስነታቸው በዓለም ዙሪያ የሚታየው ስደት መዋቅራዊ ክስተት እንጂ ድንገተኛ አደጋ አይደለም። በአንድ ሀገር ወይም በተለያዩ ሀገሮች መካከል ሊከሰት ይችላል። የቤተክርስቲያኗ ትኩረት በተለይም ከጦርነት፣ ከአመፅ፣ ከፖለቲካ ወይም ከሐይማኖት ስደት፣ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰቱትን እና ከባድ የሆነ ድህነት በሚሸሹ ሰዎች ላይ ያተኮረ ነው፣ ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው። በአጠቃላይ ፣ እነሱ ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ዕድሎችን እየፈለጉ ናቸው። ለወደፊቱ የተሻለ ሕይወትና ሕልም አላቸው እናም ይህንን ለማሳካት የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች መፍጠር ይፈልጋሉ” (Christus Vivit ቁ.92) በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐዋርያዊ ቃለምዕዳናቸው ላይ ባሰፈሩት ሐረግ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

እንዲሁም “የወጣቶች ስደት” በሀገራችን በኢትዮጵያ “እንዴት ይታያል?” ቤተክርስቲያኗ በመንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያ እንዴት ይህንን የወጣቶችን ስደት እንዴት ትመለከታለች? የወጣቶች ስደት በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ክስተት እንደሆነ እናምናለን፣ በአገሪቷም የወጣቶች ስደት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታዎች እይታ ስንመለከት እጅግ አስፈሪ ነው። ምክንያቱም በወጣቶች ላይ የሚታየው የመሰደድ  ፍላጎትና ስሜት እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጅ በተለይም ዓለማችን በአሁኑ ወቅት እየተከተለች የምትገኘው የካፒታሊዚም ርዕዮተ ዓለም ስንገመግም በዓለም ዙሪያ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ኢ-ፍትሃዊ እንዲሆን የበኩሉን አሉታዊ አስተዋጾ አበርክቷል። በተላይም በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የቀድሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቤንዲክቶስ 16ኛ እ.አ.አ. በ2007 ዓ.ም ላይ  ተካሂዶ በነበረው 94ኛው የዓለም አቀፉ ወጣት ስደተኞች ቀን በማስመልከት ባስተላለፉ መለዕክት “በዓለም ዙሪያ ሰፊው የግሎባላይዜሽን ሂደት እንቅስቃሰ ፍላጎት ጎልቷል፣ እንዲሁም ብዙ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው እና ከአገራቸው ርቀው እንዲኖሩ ተገዷል” በማለት አበክረው መናገራቸው ይታወሳል። እንደ እርሳቸው አገላለጽ፣ ወጣቶች በተሰደዱበት በየተኛውም አከባቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጉዳይ አሳስቧቸው እንደ ነበረም መግለጻቸው ይታወሳል።

ዛሬ ለዚህ ጹሁፍ ዋና ዓላማ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ የታዬው “ይህን በቀጣይነት እየተካሄደ የሚገኘው የወጣቶች ስደት በኢትዮጵያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህንን ችግር እንዴት መቅረፍ ትችላለች?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል ማለት ነው።  ምክንያቱም በሀገራችን የወጣት ስደተኞች የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ብዙዎቹን ሰለባ ማድረጉ እና እያደረገም እንደ ሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን በተቻለ መጠን በተለይም ወጣቶች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ምክንያት በወጣቶች ላይ እይደረሰ የሚገኘውን በደል እንዴት መቀነስ ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያስችል ዘንድ አንዳንድ አቅጣጫዎችን መመልከት ተገቢ ይሆናል።

ሁላችን እንደምናውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አከባቢ ድሃ በመባል ከታወቁ ሀገራት ተርታ ትሳተፋለች። ፈጣን የሆነ የሕዝብ ብዛት በየጊዜው ታስመዘግባለች፣ በአንጻሩ በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ወጣቶች በቂ ድጋፍ አያገኙም፣ የተማሩ ስራ-አጥ፣ ገጠር ያሉት ወደ ከተማ ስራ ፍለጋ፣ ብዙዎች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ለመጓዙ ይገደዳሉ። ስለሆነም ትኩረታችን በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የወጣቶች ስደት ፅንሰ-ሀሳብ መሠረተ በማድረግ የወጣቶች ስደት ሁኔታዎችና ፍላጎቶች ለማየት እንሞክራለን፡ በአገሪቱ ውስጥ ይበልጥ የወጣቶች ስደት በድሃ ሕብረተሰብ መካከል እጅግ የከፋ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህ አኳሓን ቤተክርስቲያን በምታምነው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ አይካድም፣ ቢሆንም ወጣቶች ምን ያህል ችግሩን እና መዘዙን ይገመግሙታል በማለት ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ስለሆነም እኛም የበለጠ በዚህ ሐሳብ ትኩረት በመስጠት መገምገም እና በተመሳሳይ የወጣት ስደተኞች ተግዳሮቶችን በመለየት በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን። በቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ጥበቃ ውስጥ፡ የወጣት አገልግሎቶችን በፍቅር እንድንመለከት የቤተክርስቲያን አስተምሮ ያስገድዳል። ስለዚህ  በሐዋርያዊ የሆነ እንክብካቤ እና ማህበራዊ ጣልቃ-ገብነትን ወደ ተግባር ለማሻገር ትሞክራለች። ስለሆነም በሀገራችን ይህ የቤተክርስቲያንቷ የምታደርገው ሐዋርያዊ እንክብካቤ  (pastoral care) እንቅስቃሴ አማካኝነት በወጣት ስደተኞች ላይ እንዴት ጠንክራ መሥራት ግዴታ እንዳለባት ትገነዘባለች፣ በመሆኑም የእነዚህ ችግሮች መነሻ ምክንያቶችን ለይታ ማወቅ ይኖርባታል። ቤተክርስቲያኗ የሁሉም ሰው ቁርጠኝነትና መልካም እገዛ የሚትሻ እንደሆነ እናምናለን። ስለዚህ በሚቀጥለው ሳምንት ጽሑፌ የወጣት ስደተኞች ፍልሰት መንስኤ እና መዘዝ እንመለከታለ፣ እስከዚያው ድረስ ቸር ሰንብቱ። 

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ ኤርሚያስ ኩታፎ

22 May 2020, 13:30