ፈልግ

የግራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ ይኖርብናል! የግራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ ይኖርብናል! 

የጋራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ ይኖርብናል!

“ሁሉም ነገር የተሰላሰለ ነው” በሚል መሪ ቃል “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” ሳምንት ከግንቦት 10-16/2012 ዓ.ም ድረስ እየተከበረ እንደ ሚገኝ ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ይህ ሳምንት በቫቲካን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት በበላይነት የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት የተዘጋጀ መታሰቢያ ነው። ዓላማውም ከእዚህ ቀድም የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰባት ካለው ውድመት ለመከላከል ከእዚህ ቀድም የተጀመሩ በጎ ተግባራት ለማስተዋወቅ የተጀመረ የለውጥ ጉዞ ቀጣይ ክፍል ሲሆን “በጸሎት ፣ በማሰላሰል እና የተሻለ ዓለም ለመፍጠር አብረን በመዘጋጀት በአሁኑ ወቅት በምድራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ በጋራ በመዋጋት  የተሻለ የጋራ መኖሪያ መገንባት ይኖርብናል” በሚል ሕሳቤ ለአንድ ሳምንት የሚከበር በዓል ነው።

የቫቲካን ዜና

“ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  የዛሬ አምስት አመት ገደማ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት አምስተኛ አመት ለአንድ ሳምንት ያህል በተለያዩ ምድራችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በመፈጸም እንዲከበር ይህ አሁን መላውን ዓለም እያስጨነቀ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኛ ከመከሰቱ በፊት በቫቲካን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት በበላይነት የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን ለእዚህ አመት የተመረጠው መሪ ቃል ደግሞ “ሁሉም ነገር የተሰላሰለ ነው” የሚል እንደ ሆነ ተገልጿል።

“ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  የዛሬ አምስት አመት ገደማ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ስድስት ምዕራፎችን በውስጥ አቅፎ የያዘ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን የእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት መሪ ሐሳብ የመነጨው ደግሞ እ.አ.አ. በ11ኛው ክፍለ ዘመን በኖረው እና ለተፈጥሮ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ፍቅር ከነበረው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ዘአሲሲ ጥሎት ካለፈው አሻራ ሲሆን እርሱም ምድራችንን በተመለከተ ሲናገር “የጋራ ቤታችን፣ ሕይወታችንን የምናጋራት እህታችን እና እጆቹዋን ዘርግታ የምታቅፈን ውድ እናታችን” በማለት የምድራችንን ውበት ይገልጽ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም “ጌታዬ ሆይ በምትንከባከበን እና በምታስተዳድረን በቀለማት ባሸበረቁ አበቦች እና ዕጽዋት በተሞላችውና ልዩ ልዩ ፍሬዎችን በምታፈራልን እህታችን እና እናታችን ምድር አማካይነት ተወደስ” በማለት የተፈጥሮን ሥጦታዎችን በመመልከት ብቻ የዚህ ስጦታ ፈጣሪ የሆነውን አምላክን ማወደስ እንደ ሚቻል ይገልጽ ነበር። ምድራችንን መንከባከብ ማለት የአምላክ ስጦታን መንከባከብ ማለት እንደ ሆነ አበክሮ ይገልጻል።

ፍጥረታትን የምንከባከብበት ክርስቲያናዊ የሆኑ ምክንያቶች

ከባለፈው መስከረም 25- ጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ድረስ “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር” በሚል መሪ ቃል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቫቲካን ተካሂዶ ማለፉ ይታወሳል። ይህ ሲኖዶስ “የዓለማችን ሳንባ” በመባል የሚታወቀው እና 7.8 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሸፍነው የአማዞን ደን ክልል አዋሳኝ አገሮች ማለትም በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በፔሩ፣ በኤኳዶር፣ በኮሎንቢያ፣ በቬንዙዌላ፣ በጉያና እና በሱሪናም አከባቢ የሚኖሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ትኩረት ባደረገ መልኩ እና የቤተክርስቲያኗን ዓለማቀፋዊነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተውጣጡ የካቶሊክ ቤተክርቲያን ብጹዕን ጳጳሳትን ባካተተ መልኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ታካሂዶ እንደ ነበረ መግለጻችን ይታወሳል።

“አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል ተካሂዶ የነበረው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብጽዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም በተጠናቀቀበት ወቅት አንድ ሰነድ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በእዚህ ሲኖዶስ ማብቂያ ላይ በላቲን ቋንቋ  “Laudato sì’” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬ አምስት አመት ገደማ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ ለንባብ ካበቁት ሐዋርያዊ መልእክት በመቀጠል “አማዞን፣ የቤተክርስቲያን አዳዲስ እርምጃዎች ለተቀናጀ ስነ-ምዕዳር”  በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው የብጽዐን ጳጳሳት ሲኖዶስ ማብቂያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሲኖዶሱ ወቅት ካደረጉዋቸው ንግግሮች እና በወቅቱ ከተደረጉት ውይይቶች እና ንግግሮችን አጠቃሎ የያዘ አንድ አዲስ መጽሐፍ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፣ የእዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማ እና ግብ “ፍጥረትን የምንከባከብበት ክርስቲያናዊ የሆኑ ምክንያቶች” በስፋት የሚተነትን መጽሐፍ እንደ ሆነ መግለጻችን ይታወሳል።

“እናታችን የሆነችው ምድራችን። ምድራችንን እየገጠማት ያለውን ተግዳሮት በተመለከተ ክርስቲያናዊ የሆነ እይታ” በሚል አርዕስት በጥቅምት 13/2012 ዓ.ም ይፋ የሆነው መጽሐፍ  በአሁኑ ወቅት በአከባቢያችን ላይ እየደርሰ የሚገኘውን ከፍተኛ ውድመት በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና እንዲሁም የቁስጢንጢንያው የኦርቶዶክስ የውህደት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ፓትሪያርክ በርተሌሜዎስ በአሁኑ ወቅት አከባቢያችንን ወይም ምድራችን እየገጠማት የሚገኘውን ፈታኝ ሁኔታ አስመልክተው ክርስቲያኖች ሁኔታውን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምር በማሰብ በጋራ እና በትብብር መሥራት እንደ ሚኖርባቸው የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። በተለይም ደግሞ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምድራችንን በተመለከተ “የወደፊቱ የምድራችን እና በምድራችን ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን” በተመለከተ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ ለመፍታት እና መፍትሄ ለማበጀት በጋር ተቀራርበው የሚሰሩበት እና ለምድራችን አስፈላጊ የሆነ እንክብካቤ ማደረግ እንደ ሚገባ የሚያሳስብ መጸሐፍ መሆኑም ተገልጹዋል።

የእግዚኣብሔር ፍቅር የሁሉም መዕክል ነው

ፍጥረት የእግዚአብሔር ፍቅር ፍሬ ነው፣ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ እና ከሁሉም በላይ ለፍጥረታቱ ጠባቂ አድርጎ የሾመው የሰው ልጅ ለምድራችን ተገቢውን ጥበቃ በማደረግ ምድራችን የሰው ልጆች በተስፋ የሚኖሩባት ሥፍራ ትሆን ዘንድ የማድረግ ኃላፊነት በሰው ልጆች ላይ የተጣለ መሆኑን የሚያትቱ ጽሑፎች ተካተውበታል። በዚህም ምክንያት ትርጉም ባለው መልኩ አከባቢያችንን እና በአጠቃላይ በምድራችን ላይ እየደረሰባት ካለው ውድመት ለመከላከል የሰው ልጆች አንድነት በመፍጠር እና በተቀናጀ መልኩ ተግባራቸውን ማከናወን እንደ ሚገባቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተደጋጋሚ ማውሳታቸውን የሚገልጸው ይህ መጽሐፍ በሰው እና በፍጥረት መካከል ያለው በፍቅር ላይ የተገነባው ግንኙነት ከተቋረጠ የሰው ልጅ ከፈጣሪው የተሰጠውን ጸጋ ትርጉም ባለመረዳቱ የተነሳ ከፈጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት ይናጋል የሚሉ የቅዱስነታቸው ሐሳቦች የተጠቀሱበት ጹሑፎች ይገኙበታል። የተፈጥሮ ሐብትን በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ ለማስገባት በሚደረገው ኃላፊነት የጎደለው ሐብት ለማጋበስ የሚድረገው ሩጫ ብዙዎቹ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚከናወኑ በመሆናቸው የተነሳ ዓለማችንን እና የሰውን ልጅ ራሱ ሊያጠፉ የሚችሉ ክስተቶች በመሆናቸው የተነሳ ከአሁኑ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ እና መፍትሄ እንዲበጅላቸው ቅዱስነታቸው በተደጋጋሚ ያቅረቡትን ሐሳብ አቅፎ የያዙ ክፍሎችም በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሰዋል።

ቀድም ሲል እንደ ገለጽነው “ሁሉም ነገር የተሰላሰለ ነው” በሚል መሪ ቃል “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በላቲን ቋንቋ “Laudato Sì” ሳምንት ከግንቦት 10-16/2012 ዓ.ም ድረስ እየተከበረ እንደ ሚገኝ ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ይህ ሳምንት በቫቲካን ሁለንተናዊ ሰብዓዊ እድገት በበላይነት የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት የተዘጋጀ መታሰቢያ ሲሆን ይህንን ሳምንት በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ አሁን በኮቪድ -19 ወረርሽኝ በተዋጠው የጋራ ቤታችን ለሆነችው ምድራችን እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።

22 May 2020, 20:20