ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ኢትዮጲያ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ኢትዮጲያ 

ለአንድ ወር ሲከናወን የቆየው የፀሎት መርሃ ግብር ማጠቃለያ መድረክ ላይ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ያደረጉት ንግግር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የተከበራችሁ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተከበራችሁ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባላት፣ የሥራ አመራር ኃላፊዎች፣ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያወያን፣ በሆስፒታል፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በሃገር መከላከል ሥራ ላይ ያላችሁ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሆስፒታል እና በለይቶ ማቆያ የምትሠሩ የተወደዳችሁ ልጆቻችን እንዲሁም የቫይረሱ ተጠቂ የሆናችሁ ሁላችሁ የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን።

በእኛ ዘመን ብዙ ክፉ ፈተናዎችን አይተናል። ሁሉም በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ምሕረት እና ቸርነት፤ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት እንደ አመጣጣቸው ተመልሰዋል። በዘመናችን ካጋጠሙን ክፉ ፈተናዎች አንዱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው።  ይህ ወረርሽኝ ዓለምን አስጨንቋል፤ የዓለም ሕዝቦች ያለወትሯቸው የቤቶቻቸውን በሮች ቆልፈው እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። ከተሞቻቸው ተዘግተው የተወረረ ከተማ ሆነው ጨለማ ውጧቸው ከርመዋል። ባላሥልጣኑም፣ ባለሀብቱም፣ ገበሬውም፣ የተማረውም፣ ያልተማረውም እጅ እንዲሰጥ አድርጓል። ወትሮ ትልቅ ነን ብለው በዓለም ትልቅነታቸውን ሲያውጁ የነበሩ ታላላቆች ጭንቀታቸውን ሳይደብቁ በሕዝባቸው ፊት ከዓይኖቻቸው ዕንባ እያፈሰሱ ፈጣሪያቸውን ሲማጸኑ ተስተውለዋል። ለወትሮው ፈጣሪውን የረሳ ዓለም ወደ ፈጣሪ መጮህን የሙጥኝ ብሎ ከርሟል።

እኛም  ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ በኋላ ሀገራችን አቅሟን አውቃ፣ ድህነቷን ተረድታ፣ ማድረግ የምትችለውን ጥንቃቄ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ ጸሎት አተኩራለች። የሃይማኖት አባቶችም መንግሥትም መልስ የሚገኘው ከፈጣሪ መሆኑን ተረድተን። የአንድ ወር የጸሎት እና የንስሃ ጊዜ አውጀን በጸሎት እና በንስሃ በእግዚአብሔር ፊት ቆመን የእግዚአብሔርን ፊት ስንፈልግ፣ ስንሻ ቆይተናል። በዚህ አንድ ወር በእውነት ሀገራችን እኢትዮጵያ ራሷን ፈልጋ አግኝታለች። ወደ ቀድሞው እውነተኛ ማንነቷ፣ የጸሎት ባህሏ እና ክብሯ ተመልሳለች። ዘማሪው ዳዊት “እግዚአብሔር ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” እንደሚለው ብቻዋን ስትዳክር የነበረችው ሀገራችን ወደ ፈጣሪዋ ተመለሰች። ከቤተ መንግሥት እስከ ገዳም፣ እስከ ቤተሰብ በጸሎት በአንድነት ፈጣሪዋን ለመነች።

ከመሪዎች ከሃይማኖት አባቶች ከምእመናን አይኖች እንባ ፈሰሰ፤ የህጻኑም የአዋቂውም ጉልበቶች እና ልቦች ወደ እግዞአብሔር ተንበረከኩ። በአደባባይም በግልም ኃጢያቶቻችንን በጌታ ፊት ተናዘዝን። ኢትዮጵያ ወትሮም ትዘረጋቸው የነበሩትን እጆቿን ከኃጢአት አጥባ ወደ እግዚአብሔር ዘረጋቻቸው። ራሷን ለእግዚአብሔር አስገዛች። የሃይማኖት ልዩነት ሳያግዳት ለወትሮው ነፍሳችንን ሲያስጨንቅ የነበረው የዘር የብሔር ልዩነት እና ግድግዳ ሳያግዳት በአንድነት ወደ ፈጣሪዋ ጮኸች። በየእምነት ተቋማቱ እግዚኦታ ጎረፈ፤ ከእምነት ከእግዚአብሔር ቤት ርቀው የነበሩ ልቦች ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ በቤቱ ተስፋ ቆርጦ ተጨንቆ የተቀመጠው ሕዝብ ሀገር ፊቷን ወደፈጣሪ ማዞሯን ካየ በኋላ የሰላም እንቅልፍ መተኛት ጀመረ።

·        የሃይማኖት አባት በጉጉት በተስፋ የሚደመጥባት ሃገር ሆነች።

·        የመንግስት ባለሥልጣን የሚመክረውን ምክር በጥሞና የምናዳምጥባት ሃገር ሆነች።

·        ሽማግሌዎች የሚደመጡባት ሃገር ሆነች። የተጣሉ የተለያዩ ወገኖች ታረቁ። ባለትዳሮች ፍቅራቸውን አጠናከሩ።

·        መልካም እጆች የተጎዱትን ለመደገፍ ተዘረጉ። ወጣቶች ለማገልገል ተፍ ተፍ አሉ።

·        እግዚአብሔር ምድራችንን ጎበኘ በረከት ፈሰሰ።

·        እግዚአብሔርም ይህንን ጩኸት በእርግጥ ሰምቷል። በእርግጥ ፊቱን ወደ እኛ መልሷል። ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው የትንሣኤው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ልጆቹን ሸፍኗል።

ምንም እንኳን ዛሬም ቫይረሱ በሀገራችን ወገኖቻችንን እያጠቃም ቢሆን ተስፋችንን ህልማችንን አላጠቃም። የምናሸንፍበት ጉልበት ኃይል ከመለኮት እንደሆነ በማወቃችን እና ስለዚህም በጸሎት እንድንበረታ እግዚአብሔር ዕድል ስለሰጠን ከቫይረሱ ጋር የጀመርነውን ጦርነት በድል እንደምንወጣው እርግጠኞች ሆነናል። ሀገራችን ይህንን ጦርነት ንጹህ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እንደምታሸንፍ እርግጠኛ ብትሆንም ጥንቃቄ ግን እንዳይሳነን እጅ መታጠብ፣ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ቤት መቀመጥን፣ አካላዊ መራራቅን እና ሌሎችም የሚነገሩንን የጥንቃቄ ዘዴዎች በማስተዋል እንድንተገብር እንዲሁም ደግመን ወደ ነበርንበት ኃጢአት እንዳንመለስ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የጸሎት የንስሃ ተግባራትን መፈጸም ኃጢአትን በመጸየፍ መልካም የሆነውን የማድረግ ትግላችን ይቀጥላል።

የሚያምርብን፣ ከክፉ የምንጠበቀው፣ የምንድነውም በቤተ መንግሥትም ሆነ በሕዝብ መሃል እግዚአብሔርን ስንፈራ፣ ሀገራዊም ሆነ ማሕበራዊ ቤተሰባዊ ውሳኔዎችን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አጣጥመን ስንሄድ፣ ንጹህ እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር ስንዘረጋ እና ስንጸልይ፣ በዘረኝነት ትብታብ ሳንተበተብ ሁሉም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ እና ወንድሜ ነው ብለን አምነን በፍቅር ስናቅፍ፣ ስለሀገራችን በጋራ በእውነት እና በፍቅር ስንወያይ፣ በሃይማኖት አክራሪነት ጨለማ ውስጥ ሳንወድቅ ለሁሉም ሃይማኖቶች እኩል ክብር ስንሰጥ፣ ሕይወትን ከጽንስ እስከ ተፈጥሮ ሞት ስንንከባከብ፣ ፍትሕን እውነትን ሳናዛባ ስንፈጽም፣ ድሆችን ሳንበድል፣ ተፈጥሮን ስንንከባከብ፣ የተጎዳን ስንረዳ ነው፤ እግዚአብሔር ለፈጠረን ዋነኛ ዓላማ ስንቆም ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህሙማንን ሲፈውስ፣ ኃጢአተኞችን ይቅር ሲል “ዳግመኛ ኃጢአትን አትሥራ በሰላም ሂድ” እያለ ያሰናብታቸው ነበር። ለእኛም ይህንን ወረርሽኝ ከሀገራችን አስወግዶ ነጻ ሊያደርገን “ዳግመኛ በኢትዮጵያ ላይ ግፍን አትፈጽሙ፣ፍርድን አታጓድሉ፣ ደሃን አትበድሉ፣ ዘረኞች አትሁኑ። ኃጢአትን አትሥሩ” ይለናል። ለዚህ እንበርታ በእውነተኛ ማንነት ለመኖር ቁርጥ አቋም ይዘን እንቁም።

በዚህ የጸሎት ወር ሕዝብን እንድናጽናና ተስፋ እንድንሰጠው የተዘጉ የአምላክ ስፍራዎችን በቴለቪዥን አማካኝነት ጸሎታችን፣ ትምህርታችን፣ በየቤቱ እንዲደርስ ላደረጋችሁት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ አመራሮች እና ሠራተኞች፣ ይህንን የአንድ ወር ንስሃ ያስተባበራችሁ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ ሃላፊዎች፣ በተለይ ቀሲስ ታጋይ እና የቅርብ ረዳቶቻቸው፣ የየቤተ እምነቱ የሚዲያ ኃላፊዎች ከልብ እናመሰግናለን።

እነዚህ የጸሎት እና የአስተምህሮ ፕሮግራሞች በቀጣይም ወረርሽኙ እስኪጠፋ እና ቤተ እምነቶች ለሕዝብ እስኪከፈቱ ቤተሰባዊ ትብብራችን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በቴሌቪዥን የማስተላለፉ ተግባር እንዳይቋረጥ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተስፋችን ጽኑ ነው።

ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የረመዳን ወር ጾም እየጾማችሁ ትገኛላችሁ፤ እናንተም የምታደርጉትን ጾም እና ጸሎት ፈጣሪ ይቀበላችሁ።

ምሕረቱ እና ቸርነቱ ዘለዓለማዊ የሆነ የአባቶቻቸን አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ። ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ ትውልዱን ሁሉ ይጠብቅ። አሜን!

07 May 2020, 09:42